በእንተ ርእስየ

Friday, October 27, 2017

ሕይወተ ወራዙት ክፍል 9/17- በአማርኛ



ክፍል ዘጠኝ
.... የቀጠለ....ስለ ድንግልና
መላ ዘመንን በድንግልና ለመኖር መመረጥን የሚጠይቅ ቢሆንም እስከ ጋብቻ በንጽሕና ለመቆየት ግን ለሰው ሁሉ የታወጀ ነው፡፡ ዘፀ. 34፡28፣ 1ነገ. 19፡8፡፡ በድንግልና መኖር የማይቻል ነው የሚሉ አሉ፤ ነገር ግን ሀሰት ነው ፈጣሪ የማይቻለውን ባልሰጠ (ባላዘዘ) ነበር፡፡ ሩካቤ ሥጋ እንደምንተነፍሰው አየር፣ እንደምንጠጣው ውኃ እና እንደምንመገበው መብል መቁጠር የለብንም፡፡ እነዚህን ያለገኘ ይሞታል፤ ሩካቤ ሳይፈጽም ቀርቶ የሞተ የለም ነገር ግን ብዙ ሊፈተን ይችላል፡፡ ይህን ለማሸነፍ ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት እና እስከ ጋብቻ ምንም አልፈጽምም ብሎ አቋም መያዝ (መወሰን) ያንጊዜ መንፈስ ቅዱስ ያግዘናል፡፡
ባሁኑ ጊዜ ሳይንስ (የስነ ልቡና ትምህርት) ዝሙትን (sex) በፊት ያልነበረውን መሠረታዊ ፍላጎቶች ውስጥ አካቶ ታገኛላችሁ፡፡ ይህ ዓለም ዝሙትን ለማስፋፋት ምን ያህል እንደምትጥር ያሳያል (Maslow hierarchy ማየት ይቻላል):: ከዚህ የተነሳ ያለ ሩካቤ ስጋ መኖር አይቻልም የሚሉ ሰዎች ከግትር አቋማቸው እና ድክመታቸው ተነስተው ነው፡፡ የጤና ጉድለትም ይመስላቸዋል፡፡ ይህ በዝሙት መሸነፍን ያሳያል፡፡ ዮሐ. 14፡12‹‹በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱም ደግሞ ያደርጋል፡፡ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል፡፡›› ሰው ድንግልናውን ለመጠበቅ ዝንባሌ ሲኖረው መንፈስ ቅዱስ ይደግፈዋል፡፡ ገላ. 5፡23፣ ፊል. 4፡13 ‹‹ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ፡፡››
ድንግልናን መጠበቅ በኛ ዘምን የተጀመረ አይደለም፡፡ ነገር ግን አዳም ከመሳሳቱ በፊት ለሰባት ዓመት ከሁለት ወር የኖረው በድንግልና ነው፡፡ ኖኅም ቢሆን ለጋብቻና ለፍሬ የበቃው ለአምስት መቶ ዓመታት በደንግልና ከኖረ በኋላ ነው፡፡ ከጋብቻ በፊት ድንግልናን ማጣት አይፈቀድም... ፡፡
መታጨት፣ ማጨትና ማግባት በድንግልና ሊደረጉ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ነውረኛ ያሰኛል፡፡ 2ሳሙ. 13፡12-14፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ እስራኤላዊ ሚስት አግብቶ ድንግልና ባያገኝባት ሚስቱን መክሰስ ይችል ነበር፡፡ ዘዳ. 22፡13-19 በድንጋይ ተወግራ እንድትሞት ይላል (ዘዳ. 22፡20-24)፡፡ ምክንያቱም ለሌላ ወንድ ድንግልናዋን ያስረከበች ሴት ከባሏ ጋር መኖር አትችልም፤ ሕሊናዋ የቀድሞውን ያስባልና ለእውነተኛ ባሏ የሚፈለገውን ፍቅር ልትሰጠው አትችልም፡፡ በሀገራችን የሚነገረውን ልንገራችሁ ‹‹አንዲት ሴት ድንግል ሳትሆን ከመጣች ባሏ ከእርሷ ጋር ምግብ መብላት እንኳን ያስጠለዋል›› ይባላል፡፡ ሌላውን የባልና ሚስት ኑሮ ትተን ማለት ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ በመካከላቸው ያለው ፍቅር ይቀንስና ከትዳራቸው ውጭ መሄድ ይጀምራሉ በመጨረሻም ባሁኑ ጊዜ የፍርድ ቤት ዶሴ ላጨናነቀው ፍቺ ይደረጋሉ፡፡
በድንግልና ማግባት እንዳለብን መጽሐፍ ቅዱስ ይመክረናል፡፡ 1ቆሮ. 7፡28 ላይ ‹‹ድንግሊቱም ብታገባ ኃጢአት አትሠራም፡፡›› ለወንዱም በ1ቆሮ. 7፡36 ላይ ‹‹ዳሩ ግን ማግባት ወደሚገባው ዕድሜ በደረሰ ጊዜ ስለ ድንግልና ያፈረ ሰው ቢኖር የወደደውን ያድርግ›› ይላል፡፡ ይህ ማለት ከፈለገ ያግባ ካልፈለገ ደግሞ አያግባ በድንግልና ይኑር ማለት ነው፡፡ ዛሬ ብዙዎች ትዳርን አይፈልጉም ግን ከማንኛውም ሰው ጋር ዝሙት ይፈጽማሉ፡፡ አይ ኢትዮጵያ! ከጣሊያን ወራራ እና ከግራኝ በፊት የነበበረው መልኳን እግዚአብሔር ያምጣልን፡፡ አሜን፡፡ ዛሬማ ዝሙት አንዱ መተዳደሪያ ሆኗል፤ ግብረ ሰዶምም በሌሎች ዓለማት ተጀምሮ በሀገራችንም በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወንዶች እና ሴቶች በዚህ እንደሚኖሩ ግልጽ ነው፡፡ ወንጌሉን ባንሰማ እንኳን የሀገራችን ባህል ይፈቅዳል ወይ? በፍጹም ማንኛውም ብሔር ወይም ጎሳ ጋር ሂዱ በጣም የተጠላ ነው፡፡ ከጋብቻ በፊት ዝሙትን መፈጸምን ያመጣነው ከአሕዛብ እና ከውጭው ዓለም እንጂ የኛ የኢትዮጵያውያን ባህል አልነበረም፡፡ ለዚህ እኮ ነው ዛሬ ጋብቻ ክብር የሌለው፣ የጋብቻ መስፍርትም መልክ፣ ቁንጅና የሆነው፤ ለዝሙት ብቻ፡፡ መጨረሻው ፍቺ፡፡
ድንግልናን ጠብቆ መኖር የሚያስፈልገው የግድ ለመመንኮስ ብቻ ሳይሆን ዘግይተው ማግባትም እንደሚችሉ ኃጢአት እንደማይሆንባቸው ይገልጻል፡፡ የድንግልና ሕይወት፣ የንጽሕና፣ የቅድስናና የታማኝነት ምሳሌ ሆኖ በጽኑ ቃል ኪዳን መገኘትን የሚያመለክት በመሆኑ ልዩ ክብር አለው፡፡ እዚህ ላይ ለመጻፍ ይከብዳል እንጂ ብዙ ነገር እነግራቸዋለሁ፡፡ በድንግልና ያልተጋቡ ሰዎች እድሜያቸውን በሙሉ ሳይተማመኑ ይኖራሉ፡፡ ምክንያቱም እሷም ብትሆን እስከ ትዳር መታገስ አቅቷት ድንግልናዋን ለሌላ ሰው በማስረከቧ አሁን ከእሷ ጋር ያለው ባሏ አያምናትም፡፡ ምክንያቱም ማስተማመኛ የለውም እሷም እንዲሁ፡፡ ሌላው ደግሞ ሁለቱ ተጋቢዎች በእጮኝነት ዘመናቸው ሳይታገሱ ቀርተው ዝሙት ፈጽመው ድንግልናቸውን ቢያጡ፣ ገና ድንግልናቸውን ሲያጡ ፍቅራቸው ይቀንሳል፡፡ ይህ ለብዙዎች አይታወቅም፤ የድንግልና ዋጋ ብዙ ነውና፡፡ ከዚያ በተለያዩ ምክንያቶች የጋብቻ ጊዜያቸውን ያራዝመሉ በተለይ ወንድዬው፡፡ ከብዙ ጭቅጭቅ በኋላ ጋብቻ ቢፈጽሙ እንኳን ደስታ የለውም፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር የሰጣቸው ፀጋ ያለጊዜው እና ያለቦታው ጠፍቷልና፡፡ ወንድሞች እና እህቶች ነገን በደስታ ለመኖር ድንግልናችንን እንጠብቅ፣ ለታዳጊ ወንድሞች እና እህቶችም በደንብ እንምከራቸው፡፡ አዳራ ዛሬ መልካም መስሎ የሚታይ ስሜት ነገ ጸጸት ስለሚያስከትል ከወዲሁ እናስብበት፡፡ ‹‹በእጅ የያዙት ወርቅ እንደ መዳብ ይቆጠራል››
በእጮኝነት ደረጃ ያሉ ዛሬ ደግሞ በጓደኝነት ደረጃ! ያሉ ወጣቶች ከጋብቻ በፊት ጥንቃቄ ካለማድረግ የተነሳ ዝሙት ካልፈጸሙ ወደፊት የማይጋቡ ይመስላቸዋል፡፡ በነገራችን ላይ በክርስትና የእጮኝነት ጊዜ እንጂ የጓዳኝነት ጊዜ የሚባል ነገር የለም፡፡ ይህ እራሳችን የፈጠርነው ነው፡፡ አንድ ሰው በአንድ ጊዜ አንድ እጮኛ ብቻ ይኖረዋል ብዙ ጓደኞች ግን ሊኖሩት ይችላል፡፡ባሁኑ ጊዜ አሕዛብ እና ክርስትና ያልገባቸው ዝሙትን አንደ ፍቅራቸው መገለጫ ይጠቀሙበታል፡፡ ግን ገና ሲፈጽሙ በተለያየ መልኩ ፍቅራቸው ይሻክራል መንፈስ ቅዱስ ይለያቸዋልና፡፡ በተለይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ ወጣቶች አብረው እስካሉ ምንም አይመስላቸውም፤ ተመርቀው የተለያየ ቦታ ሲደርሳቸው መጠባበቅ የለም፡፡ ድንግልናቸውን ያለ ጊዜ አጥተዋልና ምንም አይመስላቸውም፡፡ እና ወንድሞች እና አህቶች እጮኛችሁ ‹‹ካንቺ ጋር ወሲብ እንዳደርግ የከለከልሽኝ ስለማትወጂኝ ነው›› ብልሽ አትስሚው እሱ እግዚአብሔር ያዘጋጀልሽ ወንድ አይደለምና አስተምሪው ወይም ተይው፤ የማይወድስ አንቺ ሳትሆኚ እሱ ነውና፡፡ ሴቷም ወንዱን አፍ አውጥታ ባትናገረውም የዝሙት ጥያቄ ካለቀረበላት ወደ ጋብቻ ገብተው የባልን ግዳጅ ሁሉ የማይፈጽም  ይመስላታል፡፡ ግን አይደለም ወንድሜ እንደዚያ አይነቷን ሴት አትቅረብ ለትዳር አትሆንህም፤ እስከሚዋሀዳት ድረስ አስተምራት ባታውቅ ነው አንተም እሷም ከነክብራችሁ ወደ ትዳር ብትገቡ ቅዱስ እግዚአብሔር በጋብቻችሁ የስጋን ድንግልና ብታጡ እንኳን የነፍስ ድንግልናችሁን ጠብቆላችሁ በፍቅር ትኖራለችሁ፡፡
ከጾታ ምድቦች በተለይ ካህን ድንግሊቱን እንጂ ጋለሞታይቱን (ፈት የሆነችውን) ማግባት አይችልም፡፡ ዘሌ. 21፡10-14፡፡ በዝሙት ሲዘሉ ከኖሩ በኋላ ከማግባት ድንግልናን ጠብቀው ከቆዩ በኋላ ማግባት ለሕሊና፣ ለጤና፣ ለተሳካና መልካም ትዳር እንዲሁም ለመንፈሳዊ ሕይወት ምቹና የተሻለ ነው፡፡ 1ቆሮ. 7፡38 ‹‹ድንግልን ያገባ መልካም አደረገ፡፡›› ይላልና፡፡
ከጋብቻ በፊት ድንግልናን መጣል የበለጠ ሴሰኛ ያደርጋል
ያላዩት አገር አይናፍቅም እንደሚባለው ዝሙትን የማያውቁ ሰዎች ዝሙትን እንደቀመሱት አይሆኑም፡፡ ያላገቡ ሰዎች ስለወደፊት ትዳራቸው በማሰብ ድንግልናቸውን ይጠብቃሉ፤ እንዲህ በማለት ባሌ ደስተኛ የሚሆነው በድንግልና ቢያገኘኝ ነው፣ ለራሳቸው ክብረ ተክሊል እንዳይቀርባቸው በመስጋት፣ ወይም ስማቸው እና ለክብራቸው ሲሉ እንጂ ድንግልናቸውን ለመጠበቅ አስበው አይደለም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሴቶች እና ወንዶች ገና ትዳር ይዘው ድንግልናቸው ሲፈርስ ሴሰኞች ይሆናሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሴቶች እና ወንዶች ከሴት ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት አይፈጽሙ እንጂ ከላይ ያየነውን ግብረ አውናን ወይም ሴጋ ሲፈጽሙ ይኖራሉ፡፡
በእጮኝነት እያለህ ያጨሃትን ሴት ሳታገባት አትድረስባት፡፡ ድንግልናዋ ቢያጓጓህ ብትደርስባት በሁለት መንገድ ራስህን ጎድተሃል፡፡ የመጀመሪያው አመንዝራ ትባላለህ፣ የራስህንም ክብር ታጣለህ ሁለተኛው እርሷንም ካንተ ወጥታ ለማመንዘር እንዲመቻት አድርገሃልና በራስህ ጠንቅ አመጣህ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም እርሷ አንተን የምትፈራበት አንተም እርሷን የምትጠብቅበት ምንም ምልክት የለህም፡፡ በገዛ እጅህ አፍርሰሃልና፡፡ ማግባቷ የድንግልናዋን ያህል ጥበቃ ሊያደርግለት መቻሉን አትርሳ፡፡

1 comment:

  1. የመድኃኒት ንግድ ሥራዬን ለማስፋፋት በተጠቀምኩበት ብድር ለመርዳት ሚስተር ቤንጃን ከሚያስፈልጓቸው በላይ አልፈዋል ፡፡
    እነሱ ለመስራት ወዳጃዊ ፣ ባለሙያ እና ፍጹም ዕንቁዎች ነበሩ ፡፡ እኔ ለማነጋገር ብድር የሚፈልግን ማንኛውንም ሰው እመክራለሁ ፡፡ Lfdsloans@outlook.com.WhatsApp ... +19893943740.

    ReplyDelete