በእንተ ርእስየ

Thursday, November 17, 2016

የመጨረሻው ዘመን ሰው

ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሔር አምሳል ነው ይህም በነፍሱ እግዚአብሔርን ይመስላል፡፡ የተፈጠረውም ከሳበት ባህርይ ነው ይህም ከአራቱ ባህርያተ ስጋ እና ከሶስቱ በህርያተ ነፍስ ነው፡፡ አራቱ ባህርያት የሚባሉ መሬት፣እሳት፣ነፋስ እና ውሃ ሲሆኑ ባህርያተ ነፍስ የሚባሉ ደግሞ ነባቢት (መናገር)፣ሕያዊት (መኖር-መተንፈስ)፣ለባዊት (ልቦ-ማስተዋል፣ማሰብ) ናቸው፡፡ ነፍስ እና ስጋ ሁል ጊዜ ይጣላሉ፣ይቀዋወማሉ፣የበላይ መሆን ይፈልጋሉ ያሸነፈ እንደፈለገው ይነዳል፣ይገዛል፡፡ እንደ ሰው ለእግዚአብሔር የሚሆነው ስጋውን ለነፍሱ ካስገዛ ነው ስጋው የሚያሸንፈው ከሆነ ግን ለዚህ ዓለም ብቻ ይሆናል፣ስለዚህች ዓለም ብቻ ያስባል፣ስለ ነፍስ የሚያስበውንም ሆነ የሚያተምረውን አካልም ሆነ ማኅበር፣ድርጅትም ሆነ ተቋም ይቃወማል፡፡ መጨረሻ ላይ የዚህ ዓለም ገዢ ለሆነው ለሰይጣን ይገዛል፡፡
እንግዲህ ከዚህ የተነሳ የሰው ልጅ የራሱን ሀሳብ ማለትም ስለ ስጋ ብቻ በማሰቡ ጠባዩ በየጊዜው እየተቀያየረ መጥቷል፡፡ በህርይው ግን አልተቀየረም ምክንያቱም ባሕርይ አይቀየርም ባህርይው ሰው ነውና፡፡ አንዳንድ ጊዜ የባሕርይ ለውጥ እናምጣ ይላሉ የዓለም ሰዎች፡፡ እንደ ሃይማኖት አስተምህሮ ግን የባሕርይ ለውጥ ማምጣት አይቻልም ይህን ማድረግ የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ የባሕርይ ለውጥ ማለት ከሰው ወደ እንሰሳ ከእንሰሳ ወደ ሰውነት ወይም ወደ ሌላ መቀየር ማለት ነው፡፡ ይህን በመጽሀፍ ቅዱስ ተጽፎ የምናገኘው ነው፡፡ የሰው ልጅ ማምጣት የሚችለው የጠባይ ለውጥ ነው፡፡የመጨረሻ ዘመን ሰዎችም ጠባያቸው ይቀየራል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ከሰው የማይጠበቀውን ሀሳብ ሲያስቡ፣ሲሰሩ፣ስናገሩ ምን ሆነው ነው እንላለን ይህ ግን የመጨረሻ ዘመን ሶወች ስለ ሆኑ ነው፡፡ ሰዎች ስልጣኔ እየመሰላቸው ከሰው የምይጠበቀውን ነገር ሲያደርጉ እናያለን ግን አትደነቁ የመጨረሻ ዘመን ሰዎች ናቸው፡፡ ብዙ ማለት ይቻላል ግን ከዚህ ቀጥሎ የመጨረሻ ዘመን ሰዎች ምን አይነት ጠባይ እንደሚኖራቸው አነግራችኋለሁ ስሙኝ፡፡
ስለ መጨረሻ ዘመን ሳይንስ ከመላምት ውጪ ተጨባጭ ነገር የለውም ምክንያቱም የመጀመሪያውን መች እርግጠኛ ሆነና እኛ በሃይማኖት ዓይን የምናስብ ግን የዓለም መጀመሪያ እንዴት እንደ ሆነ እና መጨረሸዋም እንዴት እንደሚሆን እናምናለን እናውቃለን፡፡ የዓለም መጨረሻ ማለት ሰማይ (ታችኛው) እና ምድር (የምድር አካለትም ጨምሮ) እድሜያቸው የተገደበ ስለ ሆነ እነዚህ እና በውስጧ ያሉ አልፈው አድሱሲቷ ሰማይ የምትገለጥበት ማለት ነው፡፡ይህ ከመሆኑ አስቀድሞ ግን በዓለም መጨረሻው ዋዜማ ላይ የሚኖሩ ሰዎች የራሳቸው ጠባይ ይኖራቸዋል፡፡ ጌታችን ስለ መጨረሻው ዘመን የተናገራቸው ነገሮች አሉ ይህም በማቴዎች ወንጌል ምእራፍ 24 ነው፡፡ የዓለም መጨረሻ በዚህ ጽሑፍ ማንሳት ይከብዳል ምክንያቱም ስለምሰፋ ለአሁኑ ግን የመጨረሻ ዘመን ሰዎች ምን አይነት ጠባይ እንደሚኖራቸው ነው የምነግራችሁ ከዚያ ተነስተን እኛም ከነሱ እንድንለይ እና በሚሆኑ ነገሮች እንዳንደነቅ ለማሳሰብ ነው፡፡
የመጨረሻው ዘመን ከተፈጥሮ ውጪ ስለሚሆን የሚያስጨንቅ ነው የሚሆነው ነገሮች በሙሉ እንደተጠበቁት አይሆንም ለዚያ ዓለም የሚመቹ ደግሞ ሕገወጥ የሆኑ ነገሮች፣ሀሳቦች፣ንግግሮች እና ድርጊቶች ናቸው፡፡ ከዚያ ውጪ የሆነ ተቀባይነት አይኖረውም፣አይወደድም፣እንዳልሰለጠነ እና እንደ ኋለቀር ይፈረጃል፡፡ ነገሮች በሙሉ ፋሽን ይሆናሉ ፋሽን ማለት አድስ፣የማይቆይ፣ ቶሎ የሚጣል፣የጥንቱን የሚጥል (የሚያስቀር)፣በተለይ ደግሞ ባህል እና ሃይማኖትን የሚያጠፋ ነው፡፡ በዚህ መኃል የሰዎች መሠረታዊ አኗኗርም ሆነ ሌላው ነገር ስለሚለወጥ ሰዎች ይጨነቃሉ ምክንያቱም ከተፈጠሩበት ዓላማ ውጪ ለሆነው ነገር ይጋለጣሉና፡፡ የሰው ልጅ ደግሞ ይህን ማወቅ ይጠበቅበታል፡፡
የመጨረሻው ዘመን ከማስጨነቁም በላይ የሰዎች ጠባይ ክፉኛ ይቀየራል፡፡ ሰዎች ስለ ራሳቸው ጥቅም ብቻ ያስባሉ በቡድን ስራ መሃልም የሚያሳስባቸው የአብሮ ማደግ፣የሀገር እድገት ሳይሆን የሚያሳስባቸው የራሳቸው ጥቅም ብቻ ነው የሚሆነው ይህን ሲያደርጉ ልዩ ትኩረት የሚያደርጉት እውቀት፣ጥበብ፣መንፈሳዊ እድገት ላይ ሳይሆን ገንዘብ ብቻ ይሆናል፡፡ ገንዘብ የሚወዱ እና ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉ፡፡ እኔ፣የእኔ ማለትን ብቻ የሚወዱ ይሆናሉ አንድም ጊዜ የእኛ፣እኛ ማለትን አይወዱም፡፡ ሰው ገንዘብ የሚወድ ከሆነ ደግሞ ለሰውም አይደለም ለእግዚአበሔርም አይሆንም አምላኩ ገንዘቡ ስለ ሆነ ባልንጀራውን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፡፡ ገንዘብ ከመውደዳቸውም የተነሳ ከስራው ይልቅ ገንዘብን ብቻ ያስባሉ የገንዘብ ማግኛ መንገዶች የተባሉትን ሕገ ወጥ በሙሉ ስርቆትን፣ሙስናን፣ዝርፍያን፣ማጭበርበርን ወዘተ ይጠቀማሉ በውስጣቸውም በዚህ ምድር ለዘላለም የመኖር ያህል ይቆጥራሉ ግን አይኖሩም፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ባላቸው ነገር ይመካሉ የሌላቸውንም እንዳላቸው፣ የማያውቁትንም እንደሚያውቁት ነው አንድም ጊዜ አናውቅም አይሉም፡፡ የሚመካ ቢኖር በእግዚአበሔር ይመካ የሚለውን ወደ ጎን በመተው በገንዘብ፣በሀብት፣በዘመድ፣በራሰቸውም የሚመኩ ይሆናሉ፡፡ከትምክህትም አልፈው ትዕቢተኞች ይሆናሉ ያላቸውን በማየት የሌላቸውን ደግሞ እንዳለቸው በማድረግ ይተብታሉ፡፡ ትዕቢት ደግሞ ሳጥናኤልን ከሰማይ የጣለ ልዩ ኃጢአት ነው፡፡ ሰው ትዕቢተኛ መሆኑን አያውቅም ከባድ የሚያሰኘውም ይህ ነው የትዕቢት ጠባዩ መጣል ብቻ ነው፡፡ የመጨረሻ ዘመን ሰዎችም ገንዘብ የሚወዱ፣ራሰቸውን የሚወዱ፣ትምክህተኞች እና ትዕቢተኞች ይሆናሉ፡፡
ሌሌቹ የመጨረሻ ዘመን ሰዎች ደግሞ በራሳቸው ስለማይተማመኑ ይሳደባሉ፡፡ ስድባቸው ደግሞ ሰውን ብቻ አይደለም የማያውቁትን እግዚአበሔርን፣ቅዱሳንን በድፍረት ይሳደባሉ አንዴ ልቦናቸውን ስላጡ ምንም አይመስላቸውም አንደ ትልቅ ነገር ይቆጥሩና ስድባቸውን የቃላት አጠቃቀምን ጉዳቱን እያሰቡ ይዝናናሉ፡፡ ስድብ ነው የሚቀናቸው ለታላቃቸው ፣ለወላጆጃቸው እንኳን አይታዘዙም ከእግዚአብሐየርም ይሁን ከሰው ለሚደረግላቸው ነገር ማመስገን አይሆንላቸውም ማማረር፣አለመጥገብ ነው፡፡ አይ የመጨረሻ ዘመን ሰው፡፡
ሌሎቹ የመጨረሻ ዘመን ሶወች ቅድስና የላቸውም ድንግልናን እንደ ነውር ያዩታል በድንግልና የሚኖር ወንድ እና ሴት በነሱ ዘንድ እንደ ኋለ ቀር፣ ያልሰለጠነ፣ያልዘመነ ወዘተ ይታያል፡፡ በማንኛውም መልኩ የሚያስቡትም፣የሚያወሩት ሆነ የሚያደርጉት ከዝሙት ጋር የተገናኘ ነው፡፡ የሚመጣው ማንኛውም ፋሽንም ቢሆን ቅድስናን ከሚያጎድፍ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በመጨረሻው ዘመን ሰዎች ዘንድ ዝሙት እንደ ስልጣኔ ይቆጠራል ለዚህ እኮ ነው አደጉ የተባሉ እነ አሜሪካ እና ደቡብ አፍሪካ ግብረ ሰዶምን ያጸደቁት በሀገራችንም ቢሆን እኮ አሉ፡፡ በትዳር ላይ የሚባልግ ህዝብ የበዛበት ዘመን ላይ አይደለም እንዴ ትዳር ለዝሙት ብቻ የሆነበት ዘመን ላይ እኮ ነን ግን ጋብቻ እንዲህ አልነበረም፡፡ በዘመናችን ፍቺ ለምን እንደበዛ ያውቃሉ የጋብቻን ዓላማ ስለ ሳተ እኮ ነው፡፡ ቅድስና ስለ ሌላቸው ደግሞ በምንም መልኩ ፍቅር አይኖራቸውም፡፡ ቅድስና ሰው የተፈጠረበት ዓላማ ነው እንዲሁም ፍቅር፣ጥልን እንጂ ዕርቅን አይሰሙም ይህ ነው እግዲህ የመጨረሻ ዘመን ሰው፡፡
የመጨረሻው ዘመን ሶዎች ከስራ ይልቅ በማውራት፣በወሬ፣ሀሳብ በመስጠት፣ሀሳብ በማቅረብ ያምናሉ፡፡ ወሬ ለእነሱ ስራ ነው ለስራ ከተሰጠው ሰዓት ይልቅ ለስብሰባ የሚውለው ሰዓት ይበልጣል፡፡ በዚህ ቢያቆሙስ አብዛኛውን ጊዜያቸውን ስለ ሰው በማውራት ያሳልፋሉ- ሐሜት፡፡ ስለ ሰው ማውራት ደግሞ ስለ ራስ ካለማወቅ እና ካለመመልከት የተነሳ ነው፡፡ አንድም ሰውን ማማት ማለት ስጋውን ያላ ካራ ደሙን ያለ ዋንጫ መጠጣት ነው፡፡ የመጨረሻ ዘመን ሰው ደግሞ በዚህ ብቻ አያቆምም ድፍረቱ ከባድ ነው ልክ ሕዝበ እስራኤል በበረሃ እያሉ እግዚአብሔርን እንዳሙት እነሱም እግዚአበሔርን ያማሉ፡፡ እግዚአብሔር የሚችለውን አይችልም የሚሉ ሰዎች የበዙበት ዘመን፡፡ ይህ እግዚአብሔርን ማማት ነውና፡፡ ስለዚህ የመጨረሻ ዘመን ሰዎችም ብዚ ጊዜያቸውን ሲጠጡም፣ሲበሉም በሁሉም ቦታ ስለ ሰው በማውራት ያሳልፋሉ- ሐሜተኛች፡፡
በዚህ ብቻ መች ይበቃል የመጨረሻ ዘመን ሰው ጠባይ ራሳቸውን የማይገዙ ናቸው፡፡ ልባቸው የፈቀደውን በሙሉ ያደርጋሉ ኃጢአትም ይሁን ሌላም፡፡ ከዚህ የተነሳ ጨካኞች እና መልካም የሆነውን የማይወዱ ናቸው፡፡ ሰውን በጭካኔ መግደል፣በመርዝ መበረዝ፣ መቅናት፣የማይቆይ ፍቅር፣ ሰውንም ሆነ እግዚአብሔርን የሚክዱ፣ጠንቋይ እና አስጠንቋይ የሚሆኑ፣ለሚሰሩት ነገር የሚቸኩሉ፣በትዕቢት የተነፉ በአጠቃላይ መልካም የሆነውን በሙሉ የማይወዱ ሰዎች ናቸው፡፡
የሚገርመው ደግሞ የመጨረሻ ዘመን ሰዎች የእግዚአበሔርን ሕግ ከማክበር ይልቅ፣ፈቃዱን ከመፈጸም ይልቅ ተድላ ደስታ የሚወዱ ናቸው፡፡ መጨፈር፣መዝናናት፣መጠጣት፣መዝፈን፣ዝሙት መፈጸም ወዘተ ወይም ቅዱስ ጳውሎስ የተናገራቸውን የስጋ ፍሬዎችን የሚፈጽሙ ብቻ ይሆናሉ፡፡ እንዲሁም እነዚህ የመጨረሻ ዘመን ሰዎች መልክ እንጂ ምንም የላቸውም፡፡ ለምሳሌ ሃይማኖት አለን ይላሉ ነገር ግን የሃይማኖት ነገር አይሰሩም፣ ክርስቲያን ሆነው ይዘሙታሉ፣በዘር ይከፋፋላሉ፣ሙስና ይሰራሉ ወዘተ በአጠቃላይ መሆን የሌለባቸውን ሆነው የሚገኙ ሰዎች የሚበዙበት ዘመን ነው የመጨረሻው ዘመን፡፡
ለብዙዎቻችን የሰው ጠባይ ሲቀየር፣ሲለዋወጥ እና ከሰው የማንጠብቀውን ነገር ስንመለከት ሊገርመን ይችላል ነገር ገን ይህ ሁሉ ቀድሞ ስለ ተነገረን ማድነቅ ወይም ግራ መጋባት አያስፈልግም ይልቁን ቅዱስ ጳውሎስ ስለ መጨረሻው ዘመን ሰዎች ጠባይ ከዘረዘረ በኋላ የነገረንን ምክር እና ትምህርት መስማት ብቻ ነው የሚያዋጣው፡፡ ይህም ከነሱ መራቅ፣መለየት፣ህብረት አለመፍጠር፣አለመተባበር ነው (2ጢሞ.3፡1-10)፡፡ በመጨረሻም ተጨንቀው ምድርን ከምያስጨንቁ ከመጨረሻው ዘመን ሰዎች እግዚአብሔር አምላክ ያድነን አሜን፡፡  
ህዳር 2009 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment