በእንተ ርእስየ

Wednesday, October 25, 2017

ሕይወተ ወራዙት ክፍል 3/17-በአማርኛ



ክፍል ሦስት
ሕልመ ሌሊት ኃጢአት ነውን?
ሕልመ ሌሊት እንደ ኃጢአት እንዲቆጠር እና እንዳይቆጠር የሚያደርጉ የተለያዩ ሁኔታዎች አሉ፡፡ አጋንንት የሰውን ልጅ በተኛበት ክፉ ክፉ ሕልም በማሳየት ይፈትኑታል፡፡ የዝሙት መልእክት ያላቸውን በሕልም ያሳዩታል፡፡ ለምሳሌ የተራቆተች ሴት ገላ፣ እንደ ወንድ እና ሴት አለሌ ወዘተ...፡፡ በዚህ መልኩ የተከሰተ ሕልመ ሌሊት ክፉ ሕልም ይባላል፡፡ መጽሐፈ መነኮሳት ‹‹ሠይጣናት የሰውን ልጅ ቀን ቀን ክፉ ሀሳብ በማሳሰብ እና በማሠራት በሌሊት ደግሞ ዝሙት የሞላበትን አስጸያፊ ሕልም በማሳየት ይዋጉታል፡፡›› ይላል፡፡ በዚህ መልኩ ሰይጣናት ያቀረቡለትን ረቂቅ ፈተና ከመቃወም ይልቅ ደስ እያለው የሚያጣጥም ማለትም ከመጸጸት እና ከመቆጨት ይልቅ በደስታ ስለ ዝሙት የሚያሰላስል፣ የሚዳራ፣ የሚዘል፣ ወደ ዝሙት ከሚያመሩ ማናቸውም ነገሮች የማይሸሽ ሰው እነዚህ ነቅቶ ሳለ ያልተቃወማቸውን ተግባራት በሕልሙ በሚፈጽማቸው ጊዜ በተግባር እንደፈጸማቸው ያህል ኃጢአት ሆነው ይቆጠሩበታል፡፡ የህንንም መጽሐፈ መነኮሳት እንዲህ በማለት ይገልጸዋል ‹‹በቀን ነቅቶ ሳለ ኃጢአትን ወዶ የሚቀበልና ገልጾ የማይናዘዛት ለዚያ ሰው የረከሰች ሀሳቡ፣ ሕልሙ፣ ኃጢአት ሆን ትቆጠርበታለች››፡፡
ከሥራ ብዛት ሕልም ይታያል (መክ. 5፡3)፡፡ እንዲሁም ከምኞት ብዛትም ሕልም ሊከሠት ይችላል፡፡ ክፉ ምኞት በሕልምም ቢሆን ማርከሱ አይቀርም፡፡ ይሁ 1፡8 ‹‹እያለሙ ሥጋቸውን ያረክሳሉ››
ነፍስ እንደ ሥጋ አትተኛም እንቅልፍም በእርሷ ዘንድ የለም፡፡ ስለዚህ ነፍስ በእንቅልፍ ልቤ ነው በማለት ማመከኘት አትችልም፡፡ ነፍስ ከረከሠ ሕልም ምክንያት ከተጠያቂነት ነጻ መሆን የምትችለው ሥጋ ከእንቅልፍ ውጭ በሚሆንበት ጊዜ ተግባረ ዝሙትን በመቃወምና በመጥላት ከእግዚአብሔር ጋር መሆኗን ስተመሰክር ብቻ ነው፡፡
ሌላው ሕልመ ሌሊት እንደ ኃጢአት የሚያስቆጥረው ሁኔታ አብዝቶ መመገብ ነው፡፡ ጾም ለጽድቅ ሁሉ መሠረት እንደሆነ እንደዚሁ አብዝቶ መመገብ የኃጢአት ሁሉ መሠረት ነው፡፡ ሰው ሁሉ ለቁመተ ሥጋ ያህል መመገብ ያሸዋል፡፡ መዝ. 103፡15 ‹‹እህልም ጉልበትን ያጠነክራል›› ነገር ግን በልክ መሆን አለበት፤ ራሳችንን መግዛት ያስፈልጋል፡፡ አብዝቶ መመገብ ነፍስን ለሥጋ ማስገዛት ነው፤ሰውነትንም እንደ ማምለክ ይቆጠራል፡፡ ሲወጣ ሲገባ ስለ ምግብ ብቻ የሚያስብ፣ ስለ ምግብ ዓይነት የሚያወራ አይታችሁ አታውቁም፤ ለሆድ መገዛት ስንጀምር ነፍስን ማስራብ ይመጣል ያን ጊዜ ደግሞ የኃጢአት ባሪያ እንሆናለን፤ የወጣትነት ጾሮች በተለይ ዝሙት በኛ ላይ ይሰለጥናል፡፡
ወጣቶች ይልቁኑም በዝሙት ሥራና ሀሳብ የሚፈተኑ ሰዎች በሚገባ መጾም አለባቸው፡፡ ካልሆነ ክር ላይ ሰም እንደመጨመር ነው፡፡ አብዝቶ መመገብ ከወጣትነት ጋር የኃጢአት ሐሳቡን በግድ እንዲመጣ ያደርጋሉ›› (ማር.ይስ.አን.20 ምዕ. 1)፡፡ አብዝቶ መመገብ እና ለመብል መሳሳት የኃጢአት ምንጭ ከመሆናቸው ባሻገር በራሳቸው ኃጢአት ሆነው ይቆጠራሉ፡፡ ሕዝ. 16፡49 ‹‹አነሆ የእህትሽ የሰዶም ኃጢአት ይህ ነበረ ትዕቢት፣ እንጀራ መጥገብ፣ መዝለልና ሥራ መፍታት በእርስዋና በሴቶች ልጆቿ ነበረ፡፡›› ሰይጠነቀቅ ቀርቶ አብዝቶ ከመመገቡ የተነሳ ሕልመ ሌሊት ያገኘው ሰው እንደ ኃጢአት ይታሰብበታል፡፡ ምክንያቱም አብዝቶ መመገብ ኃጢአትን እንደሚወልድ እያወቀ ችላ ብሎ በመመገቡ ነው፡፡
‹‹ከሰውነት እንደ ምንጭ የሚነቃ ርኩስ ዘር በዝቶ ስለ ፈሰሰ ጎስቋላ ምንጣፍ፣ ልብሱ፣ በዝሙት ደስ የተሰኘ እና ሥጋው ሁለንተናው የረከሰ ነው ሥጋ ሁል ጊዜ ያነቃዋልና ዘሩ በሚፈሰው በሌሊት ብቻ አይደለም፡፡ ሕሊናውንም ያረክሰዋል›› ማለት ነው፡፡ (ማር.ይስ. አን. 20)
አንድ ሰው በንቁ ልቡና ሳለ ወደ ኃጢአት የሚያመሩትን ነገሮች ተግቶ እየተቃወመ ነገር ግን በተኛ እና ባንቀላፋ ጊዜ ዝንየት ቢያገኘው በተራክቦ ዘር በማፍሰስ ያያት ሕልሙ ዕዳ ሆና አትቆጠርበትም፡፡ ኃጢአት ከልቡ በሚቃወምና ሰው ላይ ሕልመ ሌሊት እንደ ኃጢአት አትቆጠርበትም፡፡ ይህን ለማስረዳት አረጋዊ በፊልክሲዩስ መጽሐፍ እንዲህ የሚል ሐተታ አስፍሯል፡፡‹‹ሰይጣን ጌታችንን የኔን ወገኖች አጋንንት ባንተ ወገኖች ላይ አሰለጥናቸዋለው፣ ነገር ግን ወገኖቼ የአንተን አይችሏቸውምና ድል ይሆናሉ፡፡ እነርሱ ምንም ባይችሏቸው እኔ ግን በሕልመ ሌሊት አስታቸዋለሁ፡፡›› አለው ጌታችንም ‹‹ጭንጋፍ አባቱን ለመውረስ ከቻለ ሕልመ ሌሊት ወገኖቼ ላይ ዕዳ ሆና ትቆጠርባቸዋለች፡፡›› ጭንጋፍ አባቱን መስሎና አህሎ ባለመገኘቱ የአባቱ የሆነውን ነገር መውረስ እንደማይቻለው እንደዚሁም በተግባር ያልተፈጸመች ሕልመ ሌሊት እንደ ተግባር ኃጢአት ተቆጥራ አታስኮንንም ማለት ነው፡፡ እስከ አሁን በተነሳው መሠረት አንድ ሰው ያየው ሕልመ ሌሊት ኃጢአት መሆኑን እና አለመሆኑን ማወቅ ይችላል፡፡ በርሱ ላይ የሚፈርድ ግን ኃጢአት ይሰራሉ፡፡
ሕልመ ሌሊት (ዝንየት) እና መንፈሳዊ ሥርዓቱ
በሕልመ ሌሊት የተመታ ሰው በዝያው ዕለት ሥጋወደሙ መቀበል አይችልም፡፡ ወደ ቤተ መቅደስም መግባት አይችልም፡፡ ልብሱን ካጠበ ወይም ከቀየረና ገላውን ከታጠበ በኋላ በማግስቱ መግባት ይችላል፡፡ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ግን ጸሎት፣ ትምህርትና የመሳሰሉት መንፈሳዊ ተግባራት በዕለቱም ቢሆን ሊያከናውን ይችላል፡፡ (ተአምረ ማርያም መጽሐፍ ላይ ያለውን ታሪክ ያስታውሱ)፡፡ ቤተ መቅደስ ውስጥ መተኛት ፈጽሞ የተከለከለ ነው፡፡ ነገር ግን እኛ የሌሊት መርሐግብር ሲኖር ከአዋቂዎች ጀምሮ እስከ ተራ ምእመን ድረስ በቤተ መቅደስ ውስጥ ስንተኛ እናያለን፤ መተኛት ከሆነ ቤታችን መተኛቱ ይሻላል፡፡ በዚህ ጊዜ አጋንንት በሕልመ ሌሊት እንዲመቱ ሊያደርግ ይችላል፡፡ በዚህ ሁኔታ ወደ ቤተ መቅደስ ገብተህ የምታገኘውን ፀጋ ሥርዓቷን ለማክበር ብለህ ቤተ መቅደስ አፍአ (በውጭ) ብትቆምም አታጣውምና፡፡ ስለዚህ ከልማድ እንራቅ አብረን ዋዜማ፣ ወይም ቅዳሴ የሄነው ጓደኛችን ከሕልመ ሌሊት ነጻ ሆኖ እኛ ግን ነጻ ካልሆን ምንም እንኳን የቤተ ክርስቲናችን ሥርዓቷ ማርኮህ ውስጥ ለመግባት ብትከጅል፤ ከጓደኛህም በመቅረትህ ቢሰማህም ተው ይቅርብህ የመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት አይደለም ሥረዓቷን አክብር፣ ዛሬ ሥርዓቷን ካላከበርክ ነጌ ደግሞ ዶግማዋን በቀላሉ ትጥሳለህ፣ ወይም የልማድ ክርስቲያን ሆነህ ትቀራለህ፡፡ ዛሬ መናፍቃን እና ተሀድሶ መናፍቃን መነሻቸው ይህ እኮ ነው፡፡ ሰይጣን ሰዎች ቤተ ክርስቲያን እንዳይመጡ ማድረግ ስራው ነው፣ ከሄዱ በኋላ ግን እንዳይጠቀሙ ለማድረግ ሥርዓቷን እንዲጥሱ አምላካቸው እንዲያዝንባቸው፣ በመላእክት እንዲቀሰፉ እና በመጨረሻም ዶግማዋን ችላ እንዲሉ ያደርጋል፡፡ ሃይማኖት አለኝ የሚለውን ባለቤቱ ሳያውቅ ሃይማኖት አልባ ማድረግ ነው፡፡ ዛሬ ተሀድሶዎች ያደረጉት ይህንን ነው፡፡ ስለ ስርዓት ስያስተምሩ ችግር የለውም እያሉ ሕዝቡን አደንዝዘውታል፡፡ ብናስተውል ዛሬ እኮ ሃይማኖት ያለው ሰው አታገኙም ደንዝዘናል፡፡
ሌላው ደግሞ በቤትህ እንኳን ተኝተህ ብታድር ተኝተህ ባደርክበት ልብስ ወደ ቤተ ክርስቲያን አትሂድ፡፡ ምክንያቱም አንተ ሳታውቅ ፈሳሽ ከሰውነትህ ወጥቶ ይሆናል፤ እንዲህም ለሕልመ ሌሊትም ተጋልጠህ ይሆናልና፡፡ ***ሩካቤ ያደረጉ ባልና ሚስት መተጣጠብን ምክንያት በማድረግ ከመጸለይ ወደ ኋላ ማለት የለባቸውም፡፡ ሩካቤያቸው ንጹሕ ስለሆነ መላ አካላችንን ካልታጠብን አንጸልይም አይበሉ፡፡ ለባልና ሚስት ዘር የወጣበትና የነጠበበትን አካል ማለት ኃፍረተ ሥጋቸውን ብቻ መታጠብ ይበቃቸዋል፡፡
የሕልመ ሌሊት መፍትሔ
ብዙ ሰዎች ተግቶ ለመጸለይ፣ ለማስቀደስ፣ሱባኤ ላይ እያሉ፣ለመቁረብ በወሰኑ ጊዜ ሕልመ ሌሊት እንቅፋት እየሆነ ይፈተኑበታል፡፡ በእርግጥ መብላት መጠጣት ሳያቆሙ ሙሉ ለሙሉ ከሕልመ ሌሊት መለየት አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ የሚቻል ነገር አይደለም፡፡ በተአምራት ግን በተአምረ ማርያም ላይ ተጽፎ እናገኛለን፡፡ ያንን አናንብብ/እንስማ፡፡ እንግዲህ መፍትሔዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡
1.       ባ ኢሳይያስ እንዲህ ይላሉ‹‹ሌሊት በሕልም ከሴት ጋር የተገኛህ መስሎህ ዘር ቢወርዲህ በመዓልት አታስባት-በደስታ መላልሳ አታስባት፡፡
2.       ሕልመ ሌሊት በምታይበት ጊዜ ከነቃህ ቸል ብለህ ተመልሰህ አትተኛ ፈጥነህ ተነሥ ታጥበህ ጸሎት አድርስ፡፡ ከተቻለ ስገድ ባይቻልህ ግን የባሕርይህን ድካም ፈጣሪህ ያውቀዋልና ይቅር በለኝ፣ እርዳኝ፣ አድነኝ፣ እያልክ ወደ እግዚአብሔር ለምን፡፡ እንዲህ በማድረግህ የሰይጣንን መንገድ ትዘጋበታለህ፡፤
3.       ውኃ በብዛት አለመጠጣት
ፍልክ. ክፍል 3 ‹‹እንደ ውኃ ጥም አካልን የሚደርቅ ከሕልመ ሌሊትና ከዘር መፍሰስ የሚከላከል፣ በመዓልት ሐልዮ፣ ኃጢአትን የሚያጠፋ የለም፡፡›› ውኃ ሰውነትን ያለሰልሳል፣ በውስጣችን ያለው እሳት ደግሞ ያፈለዋል ያን ጊዜ ዘርን ያነቃቃል ስሜታችንም ያይላል፡፡
ማቴ. 12፡43-45 ‹‹ርኩስ መንፈስ ግን ከሰው በወጣ ጊዜ ዕረፍት እየፈለገ ውኃ በሌለበት ቦታ ያልፋል፤ አያገኝም፡፡ በዚያን ጊዜ ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ ይላል-ሲመጣም ባዶ ሆኖ ተጠርጎና አጊጦ ያገኘዋል፡፡›› ሰይጣን ከሚጾም ሰው ርቆ ይሄዳል፡፡
4.        በሕልመ ሌሊት በተደጋጋሚ እንዳትጠቃ ወደ ዝሙት ከሚያመራ ማናቸውም ነገር ሽሽ፡፡ በመሸ ጊዜ የምታያቸውን ፊልሞች፣ ንባቦች፣ ሌሎችንም ነገሮች በጥንቃቄ መርምረህ ለፍትወት የሚያጋልጡትን ሽሻቸው፡፡ ከዚያ ይልቅ ደጋግ መንፈሳዊ መጻሕፍትን ለማንበብ መትጋት ያስፈልጋል፡፡
5.       ከመኝታ በፊት ጠግቦ ላለመብላት ሞክር፡፡ ትኩስና የሞቁ ነገሮችን ላለመውሰድ መጣር፡፡ እንዲህ ከሆነ ‹‹በሰላም እተኛለሁ አንቀላፋለሁም››
6.       ከመንፈሳዊ መምህራንና ከአበው ካህናት ጋር እየተማከሩ በሚያቀርቡት የመፍትሔ ሀሳብ መጓዝ ነው፡፡ ነገር ግን ከበሳል ሰው ጋር መሆን አለበት፡፡ (ፍልክ. ክፍ. 7)
7.       በቀንና ሌሊት ብርቱ ተጋድሎ ማድረግ፡፡ ‹‹አጋንንት በሚዋጉበት ጊዜ ልቡናውን ያነፃ ያን ጊዜ በቀን ንጽሕና የረጋ ሀሳብን በሌሊት ደግሞ ንጽሕና ጥርት ያለ ሕልምን ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቀበላል›› (መጽሐፈ መነኮሳት)
8.      ከመኝታህ በፊት መጸለይ ያው የተለመደ ነው በሚል ማብራሪያ አያስፈልግም፡፡ ምክንያቱም ከሰባቱ የጸሎት ጊዜያት ውስጥ አንዱ የመኝታ ጊዜ ጸሎት ነውና፡፡ ስለዚህ ዝም ብለህ አትተኛ፡፡ ‹‹በሰላም አሳድረኝ›› ማለት ከሕልመ ሌሊትም ለመትረፍ የሚረዳ ጸሎት ነውና፡፡
***ከዚህ ውጭ አንዳንድ ባህታውያንና መሪጌታ ተብዮዎች በተለያዩ መንገዶች መፍትሔ እያሉ ወጣቱን በሰይጣን ሲያቆራኙ ይታያሉና ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡  

 ‹‹ይቀጥላል››

No comments:

Post a Comment