ከሁሉ አስቀድመን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አንድነት የሚለውን እስኪ እንስማ ይህም ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በርሱ ያመኑ በሙሉ አንድ እንዲሆኑ ጸለየ ‹‹ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ፥ ከቃላቸው የተነሣ በእኔ ስለሚያምኑ ደግሞ እንጂ ስለ እነዚህ ብቻ አልለምንም፤ አንተ እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ፥ አንተ፥ አባት ሆይ፥ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ፥ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ።››(ዮሐ. 17፡20) አንዲሁም በመስቀሉም በአይሁድ እና በአህዛብ መካከል የነበረውን ጥል በማስወገድ አንድ አደረጋቸው፡፡ ይህ እንዲህ ተብሎ ነው የተጻፈው ‹‹እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ›› (ኤፌ. 2፡14-16) በሌላ መልኩም የምዕመናን ተስፋ፣ አካል፣ መንፈስ፣ ሃይማኖት፣ ጥምቀት፣ ጌታ እና አምላክ አንድ ናቸው እንዲህ በማለት ‹‹በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤አንድጌታአንድሃይማኖትአንዲትጥምቀት፤ከሁሉበላይየሚሆንበሁሉምየሚሠራበሁሉምየሚኖርአንድአምላክየሁሉምአባትአለ›› (ኤፌ. 4፡4-6) ፡፡ በኑሮኣቸው ውስጥም ምእመናን በፍቅር እንጂ በመለያየት መኖር አይገባቸውም፡፡ ‹‹እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፥ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ›› (ዮሐ 13፡34) ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱም ‹‹ትእዛዚቱም ይህች ናት፥ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናምን ዘንድ፥ ትእዛዝንም እንደ ሰጠን እርስ በርሳችን እንዋደድ ዘንድ›› (1ዮሐ. 3፡23) ቅዱስ ያዕቆብ በክርስቶስ ላመን እና አንድ መሆን ላቃተን ለኛ እንዲህ ይለናል ‹‹በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን? ትመኛላችሁ ለእናንተም አይሆንም፤ ትገድላላችሁ በብርቱም ትፈልጋላችሁ፥ ልታገኙም አትችሉም፤ ትጣላላችሁ ትዋጉማላችሁ ነገር ግን አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም፤ትለምናላችሁ፥ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም›› (ያዕ. 4፡1-3) ፡፡ በተጨማሪም ቅዱስ ጳውሎስ አንድነት የሚገኘው በተለይ በድርጅት ወይም አንድ ላይ በሆነ ነገር ስለ ተሰባሰቡ ሳይሆን በእውነት እና በፍቅር በአገልግሎት ነው፤ ይህም በመንፈሳዊ አገልግሎት እንጂ በምድራዊ ነገር አንድ መሆን እንደማይቻል ነው (ኤፌ. 4፡11-16)
ውድ አንባቢያን አንድነት ሲነሳ
በውስጣችሁ የሚፈጠር አንድ ነገር እንዳለ አምናለሁ፡፡ ምንም እንኳን ያሰብንበት መንገድ ብለያይም ማለቴ አንድነት ለአንዳንዱ በአንድ
ነገር፣ ለሌላው ደግሞ በሌላ ነገር እንደሚሆን አምናለሁ፡፡የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ግን ብዙ ጊዜ በመንፈሳዊ አገልግሎት ዙሪያ እንቅፋት
መስሎን የሚታይ ነገር ግን በፍጹም ሊሆኑ የማይችሉ/የማይገቡ ነገሮች ዙሪያ ህዝብን አንድ የማድረግ ላይ ባለን ግንዛቤ የራሴን እይታ
ለማቅረብ ነው፡፡ እንድጽፍ ያነሳሳኝም በአሁኑ ጊዜ ይህች ዓለም ሰይጣን ከሰማይ ከወደቀ ጊዜ ጀምሮ ዘሬም በግልጽ በምናየው መርዙ
ህዝብን እየመረዘ፣ በጅራቱ እያፈዘዘ፣ በምትሐቱ እያደነዘዘ፣ በተለያዩ ነገሮች እንዲለያዩ አድረጎ፤ ለእግዚአብር እንዳይሆን፣ ከክርስቶስ
አንድነት ለይቶ፣ አንድ ያደረገንን ክርስቶስን እየታቀወመ፣ ለሐሳዊ መሲህ መንገድ እየጠረገ ያለውን የሳይጣንን አሰራር ስመለከት
እኛ እግዚአብሔርን ለማገልገል የተሰበሰብን ሰዎች በአገልግሎት ላይ እያለን ነገር ግን ዓላማችን ከግብ ሳናደርስ በተለያዩ ነገሮች
ጊዜያችንን እንድናጠፋ፤ ዛሬ ሊሰራ የሚችለውን በስብሰባ እና በሂደት ብዛት ነፍሳት ላይ ተጫወትን፣ የኔ ብቻ ይሆን በሚል መንፈስ
የብዙዎች ሕይወት አለፈ ከቤተ ክርስቲያን ኮበለሉ፣ ሳናስተምራቸው ሄዱ ለመሆኑ ተጠያቂው ማን ይሆን? እኛው ወይስ ራሳቸው? መጽሐፍ ቅዱስስ ምን ይላል? አንድ መሆን
ካቃተን ለምን ወደ ኋላ ተመልሰን ሐዋርያት የኖሩበትን ሕይወት አንመለከትም? አንድነታቸው በምን ነበር? ልዩነታቸውስ በምን ይሆን?
ከሐዋርያት በኋላ የተነሱ ሐዋርያውያነ አበውስ እንዴት ነበር ኑሮአቸው? የሊቃውንቱ ዘመንስ እንዴተ ነበር ያለፈው? ብለን ለምን
አንጠይቅም? የኛ ችግር የዓለምን ነገር እንዳለ ይዘን ወደ ቤተ ክርስቲያን የገባን ይመስለኛል ለዚህ ነው የማይሰምርልን፡፡ አንድ
ቲያትር ስራ ላይ የሚሳተፍ ተዋናይ ከዚያ በኋላ ያለው ሕይወቱ በዚያ እንደማይቀጥል የኛ ግን የቀጠለ ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን ቅዱስ
ጳውሎስ ‹‹በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ›› (ሮሜ. 12፡2) እያለን እኛ ግን መንፈሳዊ እና ዓለማዊ
‹‹ስራዎች›› (አገልግሎቶች) ተቀላቅሎብን የዓለምን አሰራር እና ተግባር ወደ ቤቱ አመጣነው (ዮሐ. 2)፡፡
ዓላም በሰይጣን ቁጥጥር ስር ስለ ሆነች ዘወትር የሰይጣንን ስራ ትሰራለች፤
ዘረኝነቱ፣ ጎጠኝነቱ፣ ብሔርተኝነቱ፣ ራስ ወዳድነት፣ አልጠግብ ባይነቱ እና ወዘተ የእለት ተግባሯ ነው፡፡ ዛሬ ሳስበው የኛም አንደዝያ
የሆነ ይመስለኛል ለምድር አሰራር የተዘረጋው ለሰማያዊ መንገድም የተሰራ ይመስል በምድር ልክ ሰፍተነዋል በዚህ መሀል ብዙዎቹ ለሰይጣን
ተላልፈው ተሰጥተዋል፡፡ እኛ በሚጠፉ እና አንድ በማያደርጉን ነገሮች ስንጨቃጨቅ፣ ስንናታረክ፣ ስንነዛነዝ ሰይጣን ግን አንድ ከሚያደርገን
ከእግዚአብሐየር እና ከመንግስቱ በጥበቡ እየለየን፣ እኛ የሱን ስራ እየሰራንለት አሳረፍነው፡፡ ይህን እና የመሳሰሉትን በማሰብ የሚቀጥለውን
በአንድነት ዙሪያ ያለኝን የራሴን እይታ ለመጻፍ ተገደድኩ፡፡
በትርጉም ደረጃ ስንመለከት አንድነት
ማለት የተለያዩ ነገር ግን በአንድ ነገር የሚስማሙበት፣ የሚመሳሰሉበት፣የሚተባበሩበት፣አንድ የሚሆኑበት ማለት ነው፡፡ የሚለያያቸው
ብዙ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ ለምሳሌ ሰው በባሕርይ እንድ ቢሆንም በጠባይ፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በአመለካከት፣በሀሳብ፣ ወዘተ ሊለያይ
ይችላል፡፡ በባሕርይ አንድ ነው ያልኩት፣ ሰው በበሕርይው ሰው ነው፣ እንሰሳም እንሰሳ ነው በራሱ ፈቃድ ሊለውጠው አይችልም ሲፈጠር
እግዚአብሔር የሰጠው እና የሚሰጠው ነው፡፡ ስለ ሆነም ሰው በመሆኑ
ብቻ ሁሉም ሰው እንድ ነው፣ ከሁሉም የሚቀድመውም ሰውነት ነው፡፡ ማንም ሰው ማስብ ያለበትም መጀመርያ ሰው መሆኑን ነው ሌሎች ነገሮች
ከዚያ በኋላ የሚመጡ ናቸው፡፡
ዛሬም በዓለማችን ላይ ሰዎች አንድ
ለመሆን በድርጅት (ዓለም አቀፍ፣አህጉር አቀፍ፣ሀገር አቀፍ)፣ በማኅበር (ሃይማኖታዊ እና ኢ-ሃይማኖታዊ) እና ወዘተ ተደራጅተው
የጋራ የሆነ ነገር እንዲኖራቸው ይደራጃሉ፡፡ ይሁን እንጂ አንድ የሚያደረጋቸው ዓላማቸው እና ግባቸው ነው እንጂ በውስጡ የሚለያዩት
ነገሮች የሉም ማለት አይቻልም፡፡ በተጠቀሱት አካላት የታቀፉ ሰዎች አንድ ያደረጋቸው ሰው መሆናቸው እና የተሰባሰቡበት ዓላማ ነው፡፡
ይህን አንድነታቸውን ለማጽናት ለተሰባሰቡበት ወይም ለተደራጁበት ነገር መተዳደሪያ ደንብ ያዘጋጃሉ፤ሁሉ ነገራቸውም በዚያ መመሪያ
የተወሰነ ይሆናል፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ በዚያ ውስጥ ያሉ ሰዎች በምንም መልኩ አንድ ሊሆኑባቸው የማይችሉባቸው ነገሮች አሏቸው፡፡አንዚህ
ማኅበራትም ሆኑ ድርጅቶች እነዚህን ልዩነት ለማጥፋት አይታገሉም ይልቁን አንድ ያደረጋቸውን ነገር ብቻ ይመለከታሉ በልዩነታቸው ይደሰታሉ
ልዩነታቸው ውበታቸው ሆኖ ይኖራል፡፡
የሀገራችን የኢትዮጵያ ገጽታ ስንመለከት
ደግሞ ከሌሎች የዓለም ሀገራት ልዩ ያደርጋታል በዚህ ደግሞ ደስ ይለናል፡፡ በእውነት ኢትዮጵያን ለተረዳት፣ ላስተዋላት ብዙ ነገሮችዋ
ልዩ ናቸው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ሁሉንም መዘርዘር ዓለማዬ ባይሆንም ለመግለጽ ያህል የኢትዮጵያ ህዝብ በሰውነት እና በኢትዮጵያዊነቱ አንድ
ነው በሌሎች ግን አንድ ሊሆን አይችልም ከዚህ ውጪ ባሉ ነገሮች አንድ ማድረግ አይቻልም፤ በቋንቋው፣ በባህሉ፣በብሔሩ፣ ወዘተ አንድ ለማድረግ መጣር ከህዝቡ መካከል
መለያየትን፣ ጦርነትን፣ ጠላትነትን፣ የበላይነትን፣ የበታችነትን እና ወዘተ አመለካከቶችን መፍጠር ነው፡፡ ለዚህ አይደል እንዴ ነብየ
እግዚአብሔር ኤርምያስ ‹‹ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዥንጉርጉርነቱን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን?›› ያለው፡፡ የቀደሙ አባቶቻችን ቢሆኑ
ከጠላት ጋር በኢትዮጵያዊነታቸው ሲዋጉ፣ በልዩነታቸው ደግሞ ተከባብረው ኖረዋል እስከ ዛሬም አብሮ አሉ፡፡ በመሀል ግን ይህን ልዩነት
ለመጨፍለቅ የሞከሩ ነገስታትም ሆኑ ገዢዎች ሳይሰምራላቸው አልፈዋል፡፡ እስከ አሁን ያወራሁት ስለዚህ ዓለም ማለት ዓለማዊ ወይም
ስጋዊ ኑሮን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ግን ስለ መንፈሳዊ አንድነት ከልዩነቶቻችን ጋር ያለውን ኅብረት እንመለከታለን፡፡
ሰው የተፈጠረው በስድስተኛው ቀን ከሰባት በሕርያት ማለትም ከአራቱ
ባሕርያተ ስጋ እና ከሶስቱ ባሕርያተ ነፍስ ነው፡፡ ከሌሎች ፍጥረታት ደግሞ እጅጉን ልዩ ነው፤ በመልክ እና በምሳሌ ብንል እግዚአብሔርን
መስሎ፣ በአፈጣጠር ደረጃ ስንመለከት ደግሞ እግዚአብሔር ሌሎች ፍጥረታትን ጨለማን ከፊታቸው አስከትሎ ቢፈጥር አዳምን- ሰውን ግን
ብርሃንን ከፊት አኑሮ በጊዜ ነግህ ፈጠረው፡፡ ምን ይህ ብቻ ሌሎች ፍጥረታት አግዚአብሔር ሲፈጥራቸው በመናገር ወይም በማሰብ ሲሆን
አዳምን ግን በማሰብ ያሰበውን ተናግሮ የተናገረውን በተግባር (በገቢር) ፈጠረው፡፡ ሌላውና የሚገርመው ደግሞ ከመላእክት ውጪ ያሉ
ሕይወት ያላቸው ፍጥራታት ለዘለዓለም የመኖር ፀጋ የላቸውም ሰውን ግን እግዚብሔር በአፍንጫው እፍ ባለበት የሕይወት እስትነፋስ ለዘለዓለም
የመኖር ለጊዜው ነፍሱ ከስጋው ብትለይም ጌታችን ዳግም ሲመጣ ፍጹም ዘለዓለማዊ ሆኖ መነሳቱ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሚያሳየው የሰውን
ክብር ነው፡፡ ሆኖም ግን ከሌሎች ፍጥረታት ከሳጥናኤል ቀጥሎ እግዚአብሔር ላይ ያመጸ የሰው ልጅ ነው፡፡ በአመጹም ወደቀ መለያየት
እና ሌሎች ምድራዊ ጠባይኣት ወረሱት፡፡እግዚብሔርም አመጹን ሳይቆጥርበት ከሕግ በታች ሰው ሆኖ ወደ ቀደመ ክብሩ መልሶታል፡፡ በዚህ
ጊዜ ነበር የተለያየው እና ክብሩን አጥቶ የነበረው የሰው ልጅ አንድ የመሆን እድል ያገኘው፡፡ በዚህ ምድር ያለው በሙሉ ደግሞ የአዳም
ልጅ ነው ከአዳም ያልተገኘ ሰው የለምና፡፡ ጌታችንም በአንድ ሰው
፤በአዳም ምክንያት ወደ ዓለም የመጣውን ሞትን በሞቱ ሞትን ገድሎ ሕይወትን ሰጠን፡፡ በክርስቶስ ያመኑም በክርስቶስ አንድ ናቸው፡፡
ጌታችን እንደ ተናገረ ‹‹›አባት ሆይ እኛ አንድ እንደሆን አነዚህ አንድ ይሁኑ›› ብሎ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም በአባቱ ግርካዊ በእናቱ
እብራዊ ቢሆንም ‹‹ከአሁን በኋላ ግርካዊ፣ አይሁዳዊ፣ ሮማዊ፣ ወንድ ወይም ሴት የለም ሁሉም በክርስቶስ አንድ ናቸው›› ያለው በክርስቶስ
ያመነ ሁሉ አንድ አባት፣ አንድ ዓላማ (መንግሥተ ሰማያት)፣ አንድ ልብ አለው ማለት ነው፡፡ ለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ሐዋርያት በዘመናቸው
‹‹አንድ ሀሳብ እና አንድ ልብ ነበራቸው›› የሚለን፡፡ እንዲህ ስባል ግን ሐዋርያትን የሚለያያቸው ነገር የለም ማለት አይደለም
ከቅዱስ ጳውሎስ ንግግር መረዳት እንችላለንና፡፡
ሐዋርያት በክርስቶስ መሰረትነት ቤተ ክርስቲያንን ሠሩ፡፡ ስለዚህ ክርስቲያኖች
በምድራዊ ነገር ቢለያዩም በመንፈስ አንድ ናቸው፡፡ በምድራዊ ነገር ሊባል በባህል፣ በቋንቋ፣ በሌላም አንድ ላይሆኑ፡፡ ስለዚህ በክርስቶስ
ያመኑ ሰዎች በሙሉ በከርስቶስ ማለትም በመንፈስ አንድ ናቸው የሚወርሱት አንድ መንግስት ነውና ይህን የሚያገኙት ደግሞ በመንፈስ
አንድ መሆናቸውን ሲያከብሩ እና ሲጠብቁ ብቻ ነው፡፡ አሁንም ቅዱስ ጳውሎስ የስጋ ፍሬዎች ብሎ ከዘረዘራቸው መካከል አንዱ መለያየት
ነው ይህን የሚያደርግ የእግዚአብሔርን መንግስት አይወርስም ይላል፡፡ (ገላ. 5)
የህዝቡን ልዩነት ከቋንቋ አንጻር
ስንመለከት እውነት ነው ምድር በአንድ ቋንቋ ነበረች ዛሬ ግን የቋንቋውን መብዛት መራገም አንችልም ምክንያቱም በሐዲስ ኪዳን እግዚአብሔር
መንፈስ ቅዱስ ባርኮ አክብሮ ለሐዋርያት ገልጧልና፡፡ ሐዋርያትም ምንም ዓይነት የቋንቋ ችግር ሳያጋጥማቸው ወንጌልን ለዓለም አዳረሱ፤
ህዝቡንም እኛ በምንችለው ቋንቋ ይማር አላሉም በህዝቡ ቋንቋ አስተማሩ እንጂ፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትም ቢሆኑ በተለያዩ ቋንቋ እንደተጻፉ
እንረዳለን ዛሬም ያንን መሠረት በማድረግ አንዱ መጽሐፍ ቅዱስ ከ1500 በላይ በሚሆኑ ቋንቋ ታትሟል፡፡ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ
ደግሞ ተመልከቱ እውነት የሐዋርያት አካሄድ የተከተለ ነው ብዬ አላምንም ምክንያቱም አስተማሪውም ቢሆን የህዝቡን ቋንቋ ካለመልመድ
ግድ በራሱ ቋንቋ ካልሰሙ ያለ ይመስላል፤ ይህ ደግሞ ሐዋርያዊነት አይደለም፡፡ ይህን ለማወቅ ጥናትም አያስፈልግም ምክንያቱም በግልጽ
የሚታወቅ ነውና፡፡ ህዝብ አንድ ሆነ ማለት በአንድ ቋንቋ ስለ ተናገረ ወይም ስለ ተማረ እይደለም ይህን መቼም ቢሆን ማድረግ አይቻልም፤ ‹‹እንደ የሰይጣን ማኅበርተኞቹ ካልሆን
ወይም ካላሰብን በቀር››፤ አግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለማድረግ ያልወደደውን እኛ ማድረግ አንችልም፡፡ ህዝብ አንድ የሚሆነው በዓላማ
እና በሃይማኖቱ (በመንፈስ) ካልሆነ በቀር በሌላው አንድ ማድረግ አይቻልም፡፡ ስለዚህ መንፈሳዊ ስራ የሚሰራው የህዝቡን ማንነት
ከተረዱ በኋላ ነው፤ ሙሉውን የሐዋርያዊ አገልግሎት መዘርዘር ባይቻልም ህዝቡን ማወቅ (ባህሉን፣ ቋንቋውን፣ መልክአ ምድሩን፣....)
መሆን እንዳለበት ግልጽ ነው፡፡ የጌታችንን እና የሐዋርያትን ትተን የሀገራችንን ብንመለከት እንኳን አባ ፍሬምናጦስ፣ ዘጠኙ ቅዱሳን፣
አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እና ሌሎችም ቢሆኑ መጀመሪያ ያደረጉት የህዝቡን ቋንቋ መልመድ አልነበረም ወይ? መች በራሳችን ቋንቋ
እናስተምር አሉ?፣ መች የኛን ባህል ተቀበሉ አሉ? ሐዋርያዊነት ይህ ነው፡፡ የሀገራችንን ሁኔታ ስንመለከት ግን በተቃራኒው ነው፡፡
ሰማንያ ብሔር ብሔረሰብ ያላት ሀገር እስከ ዛሬ ግን መጽሐፍ ቅዱስ እንኳን ከግእዝ እና ከአማርኛ ውጪ ታትሞላት አላየንም፣ ስብከተ
ወንጌልም እንኳን ቢሆን ከአማርኛ ውጪ አታስተምሩ የተባልን ይመስላል፣ ቅደሳሴውን ብንወስድ ከግእዝ እና ከአማርኛ ውጪ አትጠቀሙ
የተባለ ይመስል ህዝቡም ባያዳምጥም ሰምቶ ወደ ቤቱ ይሄዳል፡፡ ይህ ግን እስከ መጨረሻ ልያቆየው አልቻለም ህዝቡ ለቤተ ክርስቲያን
ያለው ፍቅር እየቀነሰ ሌላው ደግሞ እውነትም ይሁን ሐሰት ህዝቡ በሚሰማው ቋንቋ የሚያሰተምረውን ሲያገኝ መከተል እንደጀመረ አሁንም
ቢሆን በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳለ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስም ትልቁ እና ብቸኛው
ዓላማ የሆነውን ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት፣ ያላመኑትን ማሳመን፣ ያመኑትን ማጽናት እና መጠበቅ ሆኖ ሳለ በሌላ በምድራዊ ነገር
የተጠመደ ይመስለኛል ይህ ደግሞ ጌታችን ‹‹በመቅደስም በሬዎችንና በጎችን
ርግቦችንም የሚሸጡትን
ገንዘብ ለዋጮችንም
ተቀምጠው አገኘ፤
የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፥ የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፥ ርግብ ሻጪዎችንም። ይህን ከዚህ ውሰዱ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው›› የሚለው የተፈጸመ ይመስለኛል፡፡ ከስብከተ ወንጌል ይልቅ ለምድራዊ ነገር ስደከም ገንዘብ ላይ ማነጣጠር... ህንጻ
ስላሴ የሆነውን ሰውን ከማነጽ ይልቅ ምድራዊ ሕንጻ ሲታነጽ ማየት ከጀመርን ቆየን፡፡ከቅዱስ ሲኖዶስ ይልቅ ብዙ ማኅበራት በተቻላቸው
መጠን እየሰሩ ይገኛሉ፤ ነገር ግን አንድነት ምን እንደ ሆነ፣ እንዴት አንድ አንደ እንደሚኮን፣ ያልተገነዘቡ ይመስለኛል፡፡ በአሁኑ
ጊዜ ከሀገር፣ ከክፍለ ሀገራት፣ ከደብራት፣ከሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ ከግቢ ጉባኤያት ባለው ነባራዊ ሁኔታ መረዳት ይቻላል፡፡ይህም
ሰው አንድ የሚሆነው በምድራዊ ነገር ማለትም በቋንቋ፣ በባህል፣ በብሔር፣በሰፈር፣ በክልል እና ወዘተ የሚመስላቸው የተባራከቱ ይመስለኛል፡፡
‹‹ይመስለኛል›› ብዬ የምናገረው ሳላምንበት ቀርቼ ሳይሆን ሁሉም በመንፈሳዊ ዓይን ብመለከተው ለመጋበዝ እና የራሴ እይታም ስለሆነ
ነው፡፡ ማንበብ ለምትፈልጉ ደግሞ ወንድማችን ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ያደረገውን ጥናት የማኅበረ ቅዱሳን ሐመር መጽሔት የ2009
እትም ከመስከረም እስከ ህዳር ላይ ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሐዋርያዊ ስራ›› የሚለውን በማንበብ የራሳችንን
አገልግሎት መገምገም እንችላለን፡፡ እንዲሁም በመምህር ደረጀ ወይንዬ ‹‹ዜና ገዳማት ወአድባራት›› ብሎ በ2006 ዓ.ም ባዘጋጀው
ዘጋቢ ፊልም ላይ በመካከለኛው ኢትዮጵያ እና ጠረፋማው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያስተምራቸውን እንደሚፈልጉ ጩኸታቸውን ሰምተናል፡፡ እንደ
ማንነታቸው እንድረስላቸው ወደ ውጭ ከመውጣታችን በፊት እስኪ ቆም ብለን ሀገር ውስጥ እንመልከት መስራት እየቻልን ያልሰራናቸው ነገሮች
አሉ፡፡ ‹‹ሕዝቤ እውቀት ለማጣቱ የተነሳ ጠፍቷል›› ተብሎ የለ ‹‹በመጨረሻው ዘመን ርሀብ ይሆናል ይህም የእግዚአብሔር ቃል ካለመስማት
የተነሳ ነው›› ይላል ነብዩ አሞጽ፡፡ በሌሎች ቦታዎች ህዝቡ ቃለ እግዚአብሔር ዘወትር እየሰማ ክርስቲያናዊ ሳይሆን የልማድ ኑሮ
ይኖራል አብዛኛው የሀገሬው ሰው ግን እግዚአብሔር እንዳለ በማመን ብቻ ለዘመናት ቃሉን ሳያደምጥ ሲሰማ፣ (ለማዳመጥ ስለማይገባው)
ሌላው ደግሞ ጭራሹኑ ሁለቱንም እድሎች ሳያገኝ ቆይቷል፡፡ የኛ ጥቅም ይቅርብንና እንድረስላቸው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ
ቤተ ክርስቲያን የሐዋርያት ትምህርት በቀጥታ የምታሰተምር ስትሆን ነገር ግን ለሁሉም እንደ ማንነቱ ስብከተ ወንጌል ብታስፋፋ ኖሮ
አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ምን እንደሚሆን መገመት አያዳግትም፡፡ የሚገርመኝ ደግሞ ምድራዊ መንግስት እንኳን ህዝቡ በሚሰማው ቋንቋ፣ በሚረዳው የሕግ ትርጉም
እያገለገለ ባለበት ዘመን ለሰማይ መንግስት የምትሰራ ቤተ ክርስቲያን
ይህን አለማድረጓ፣ የሐዋርያትን ትውፊት ወደ ጎን የተወች ይመስለኛል፡፡ አንደሚመስለኝ የአቅም ማነስ ጉዳይ ነው ለማለት
ብዙ ሺህ ዘመናትን አሳልፋለች አገልጋዮችን ከሰፈር ከህዝቡ ውስጥ ከማፍራት ይልቅ ከሌላ ቦታ ብቻ የማምጣት ስራ ስትሰራ መቆየቷ አሁን ላለው የሐዋርያዊነት ችግር ምክንያት ሆኗል፡፡ከሌላ ቦታ በማምጣታችን
ተቃውሞ ኖሮኝ ሳይሆን ያመጣናቸው አገልጋዮች የሐዋርያዊነት የግንዛቤ ጉድለት በሚመሰል መልኩ እንደ ቅዱስ ፍሬምናጦስ፣ ዘጠኙ ቅዱሳን
እና ሌሎችም መሆን አልተጋደሉም ይልቁን ህዝቡ በሌለው እነሱ ባላቸው ማገልገል ጀመሩ፤ትርፉ ድካም ሆኖ ቆየ በዚህም ህዝቡ ይህችን
ቤተ ክርስቲያን ሳያውቃት፣ ሳይረዳት፣ እየወደዳትም፣እያወቃትም የኮበለለ እግዚአብሔር ይቁጠረው፡፡ ምን ሃይማኖት መካድ ብቻ የቤተ
ክርስቲያንን ትምህርት ከልጅነቱ ሳያገኝ ቀርቶ ጥሩ ምግባር ሳይይዝ ያደገ ስንት ነው? ይህ የሆነው እንግዲህ በኢትዮጵያ ነው በሌላ
ምድር አይደለም፡፡ስለዚህ ህዝብ አንድ የሚሆነው በቋንቋ ሳይሆን በክርስቶስ ነውና አመለካከታችንን ለውጠን ህዝቡ ባለው አገልግለን
የሌለንን እንዲያድለን ደግሞ መጀመሪያ ውስጣችንን ዝግጁ አድርገን እግዚአብሔርን እየለመን ልንታጠቅ እንችላለን፡፡ ምክንያቱም የህዝብ
ቋንቋ ማወቅ ብንፈልግ ዛሬ እንደ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ ወርዶ ላይገልጥልን ይችል ይሆናል ጥሩ አመለካከት ካለን፣ ሐዋርያዊነት
ከገባን፣ ስጋዊ እና ራስ ወዳድነት ሳይሆን መንፈሳዊነት ከገባን ታግለን
መታጠቅ ይቻላል፤ካልቻልን ደግሞ እግዚአብሔር አልፈቀደምና በታደሉት እና በሚችሉት እንጠቀም፡፡
ከግብጽ ኦርቶዶክስ፣ ከአርመን
እና ከሌሎች ጋር አንድ ያደረገን ባህል እና ቋንቋ እኮ አይደለም እንድ ያደረገን ክርስቶስ ነው፤ አንድ ባደረገን በከርስቶስ እስከመጨረሻ
እንኖራለን ለምን በባህል፣ በቋንቋ እና በሌላ አንድ አልሆንም ብለን አናውቅም ስለዚህ እኛ ኢትዮጵያውያንም የ80 ብሔር ብሔር ሰብ
ሀገር ሰዎችም ይህን እናስብ አንጂ አንድ በሚያደርጉን አንድ አንሆናለን አንድ በማያደርገን ደግሞ በምድር እንከባበራለን፣ እንኮራበታል፣
እናምርበታለን፡፡ ይህን የሚለው በሐዋርያዊ አገልግሎት ለተሰማራችሁ እና ለሚመለካታችሁ አካላት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የማየው ሰው ከቃለ
እግዚአብሔር ይልቅ የሚሰማበትን ቋንቋ የሚያዳምጥበት ዘመን ላይ ነን ከቋንቋው ውጪ ያለውን መስማት አይፈልግም፡፡ይህ ደግሞ በሐዋርያት
ዘመንም የነበረ ነው ለምሳሌ ‹‹በገዛ ቋንቋቸው ሲናገር በሰሙ ጊዜ
ይበልጥ ዝም አሉ›› የሐዋ.22፣2፤ ከሚነገረው ምንነት ይልቅ በቋንቋው
ስለተነገረው ብቻ በብዛት ያደምጡት እና ይቀበሉት ነበር፡፡ ከዚህ አንጻር ህዝቡን እነሱ በሚሰሙት ቋንቋ እናስተምር ይህን ካደረግን ሃያ ዓመት ሳይሆን በአምስት ዓመት ውስጥ
ለውጥ እናመጣለን፡፡ የአገልጋይ እጥረት አለ ብዬ አላምንም ካለም በጊቢያት፣ በሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ በማሰልጠኛዎች ግንዛቤ ማስጨበጥ
በሚቻለው ሁሉ ማሰማራት ይቻላል፡፡ በነዚህ የአገልግሎት ቦታዎች ያሉ ሰዎች ሰፊ ቦተ የመድረስ አቅም አላቸው፤ የግቢ ጉባኤ ተማሪ
ከቆየበት ግቢ ወደሚሄድበት ሁሉ ሕዝቡ ባለው ነገር ሁሉ ማስተማር ይችላል ሌሎችም አንዲሁ፡፡ የኛ ችግር ግን ህዝቡን አንድ ሁኑ
የምንላቸው በምን እንደሆነ አልገባኝም ለእስከአሁኑ ክፍተቱ ይህ ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡ስለዚህ አባቶችም ቢሆኑ አንድ ሁኑ አንድ
ሁኑ እያሉ ዘወትር ከሚመክሩን አንድ የምንሆንበትን በትክክል ይንገሩን አልነገሩንም ሳስበው ግን አንድ ሁኑ የምሉን በክርስቶስ ሳይሆን
በምድራዊ ነገሮች መስሎ ታየኝ ምክንያቱም በኛ በልጆቻቸው መካከል ብቻ ሳይሆን በራሳቸውም መካከል መለያየት ሰፍኖ ማግኘቴ አሳዝኖኛል፡፡
ውድ አንባብያን ከመፍረዳችሁ
በፊት ራሳችሁን ተው እና ሌላውን አስቡ፡፡ ይህን ስል ምሳሌ ልስጣችሁ እናንተ እግር አላችሁ እንበል የሌለውን አስቡ፣ አይን አላችሁ
ማየት ትችላላችሁ ማየት የተሳናቸውን ደግሞ አስቡ፣ እናንተ በምትሰሙት ቋንቋ በምታውቁት ባህል ምድራዊውም ሆነ መንፈሳዊ አገልግሎት
(ትምህርት ወንጌል፣ ቅዳሴ፣ ንስሀ...) ታገኛላችሁ እንበል ሌላው ደግሞ እያገኘ እንዳልሆነ አስቡ፣ በእናንተ ሰፈር ቤተ ክርስቲያን፣
መብራት፣ ውኃ እና ወዘተ አላ እነበል የሌለውን ደግሞ አስቡ፤ ሕመሙ የሚሰማችሁ እናንተ ራሳችሁን በሌላቸው ሰዎች ስትተኩ ወይም
አጥታችሁ ስታዩ ብቻ ነው የሚገባችሁ ይህን ደግሞ የራሴ ጥናት አለኝ፡፡ ለምሳሌ እናነት ኦሮምኛ ወይም ወላይትኛ አትሰሙም በነዚህ
ስፍራዎች ሄዳችሁ ቀኑ ሰንበት እሁድ ሆኖ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄዳችሁ ቅዳሴው ከዜማው ውጪ ሁሉ ነገር በነዚህ ቋንቋዎች ቢሆን ምን
ይሰማችኋል? ምን አይነት እርምጃስ ትወስዳላችሁ? እስከ ዛሬ ካላሰባችሁ እውነትም ራ ወዳዶች ናችሁ ምክንያቱም ልክ እንደ እናንተው
እስከ ዛሬ አማርኛ እና ግእዙን ሳይሰማ አሜን ሲባል እየዘገየ አሜን እያለ፣ምን ስባል እንደሚነሳ ባያውቅም ሰው ሲሰግድ እየሰገደ
በቃ ምን ልበላችሁ ይህን ያደረጉ ክርስቶስ በዚህች ቤት መሆኑን በጭላንጭል የተረዱ ናቸው ሌሎችማ የሉም በተኩላ አፍ ውስጥ ግብተዋል፤
እናንተስ ምን ነበር ልትሆኑ የምትችሉ? በሰው ሳይሆን በራሳችሁ ፍረዱ ከዚያ በኋላ ክርስትና እንደገባችሁ ትረዳላችሁ፣ እውነት ክርስቶስን
መውደዳችን በዚያ ይታወቃል ሌላውንም በዚህ መልክ አስቡ ክርስትና ደግሞ ይህ ነው እውነት በልጀራህን እንደራስህ አድርገህ ውደድ
የሚለው ቃልና ቅዱስ ጳውሎስ የመጨረሻ ዘመን ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉ (2ጢሞ. 3፡1-5) ያለው ለዚህ የማይውል ይመስላችኋል?
የቤተ ክርስቲያን ባህርያትም ይህንኑ ያስተምሩናል ይህም ቅድስት፣ አንዲት፣
ሐዋርያዊት እና ኩላዊት ናቸው፡፡ በውስጧ ያሉ ምእመናንም ይህንኑ ይከተሉ ይገባል፡፡ ስለዚህ አንባብያን እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለካታችሁ
አካላት ህዝቡን አንድ ለማድረግ ብላችሁ አንድ ማድረግ የማንችልባቸውን ከያዝን ትርፉ ድካም ስለ ሆነ አንድ መሆን በሚችሉባቸው ነገሮች
ብቻ አንድ እናድርግ ካልሆነ ግን አንድ የምንሆንበትንም የሚጎዳ ስለሆነ ለምድርም ለሳማይም ሳይሆን የሰይጣን ሆነን እንቀራለን፡፡
እኛ ከቅዱሳን ህብረት የሚኖረን ምድራዊውን በምድር ትተን ሰማያዊውን ለሰማይ ካደረግን ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም
ምድራዊውን የሰዎችን ልዩነት በምድር አክብሮ ለማያልፈው በሰማያዊ ክብር አበቃቸው፡፡ ሐዋርያትም ከመንፈስ ቅዱስ የተቀበሉትን ፀጋ
በታማኝነት በምንፈስ ቅዱስ እየተመሩ ህዝቡን መስለው አስተምረው ለአባቶቻችን፣ ለሊቃውንት ከዚያም ዘሬ ለኛ ደረሰ፡፡ እስኪ እውነት
እንነጋገር በኛ ጊዜ ያለው ጭቅጭቅ በሐዋርያት ዘመን ነበረ እንዴ? አልነበረም በዚህ ቋንቋ ካልሆነ አናስተምርም ብለው ያውቁ ይሆን?
በፍጹም የመንፈስ ቅዱስን ፀጋ ወዴት አድርገው? አንድ ሆነው የነበረስ በቋንቋ ነበር እንዴ? አይደለም አንድ ቋንቋ ተናጋሪ ሆነው
ቢሆን ኖሮ ያ ሁሉ ቋንቋ ባልተገለጠላቸው ነበር፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለ ‹‹...ወደ እናንተ
ልንመጣ ወደን ነበርና፥
እኔ ጳውሎስም
አንድና ሁለት ጊዜ፥
ሰይጣን ግን
አዘገየን...››
(1ተሰ. 2፡18) እኛንም የክርስቶስን ወንገጌል ለዓለም ሳንሰብክ በማይረቡ ነገሮች እያዘገየን ነውና ብንነቃ ይሻላል፡፡
በመጨረሻም ህዝብ አንድ የሚሆንበትን እየለየን፣ የሚለያይበትንም እየተረዳን
ሐዋርያት ባስተማሩን እና ባወረሱን መልኩ አገልግሎታችን እንቀጥል እንጂ በራስ ወዳድነት እና በሰይጣነዊ አሰራር ህዝብን አንበትን
የምል ሀሳብ አለኝ፡፡ ሀሳብ ሲጡበት የቱ ጋር እንደ ሆን አገልግሎታችንን እንገምግም፡፡ ይቀጥላል!
ረጋሳ ዓለሙ
መጋቢት 2009 ዓ.ም ፣ጅማ
No comments:
Post a Comment