ክፍል ስምንት
ምዕራፍ አምስት
ድንግልና
ድንግል የሚለው ቃል ‹‹ተደነገለ፣ ተጠበቀ›› መጠበቅ ማለት እንደ አገባቡም ፍቺው ሊለያይ ይችላል፡፡ ለዕቃ እንደሆነ
ገና ከማምረቻ የወጣ፣ ምንም ያልተሠራበት፣ ያላደፈ፣ ያላረጀ፣ ያልተቀላቀለ ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት እስኪ ለሰው ደግሞ ተጠቀሙ፡፡
ድንግል መሬት ሲባል ደግሞ ለምነቱ እንደተጠበቀ ያለ፣ ለእርሻ ያልዋለ ወይም ያልታረሰ፣ ያልተቆፈረ፣ ዘር ያላረፈበት፣ እንደተፈጠረ
ያለ፡፡ ለሰው ስነገር ደግሞ ወንድ የማታውቅ፣ በጥብቅ፣ ልጃገረድ ወይም ሴትን የማያውቅ ወንድ ማለት ይሆናል፡፡ ዘፍ. 24፡16
ራዕ. 14፡4፡፡ ነገር ግን አንዲትን ሴት ምኅተመ ድንግልና ስላላት ብቻ ሩካቤ አድርጋ አታውቅም ወይም ሩካቤ ስላደረገች ማኅተመ
ድንግልና የላትም ማለት አይቻልም፡፡ የወንዶች ድንግልና እንደ ሴቶች ተጨባጭ ጉልህ የድንግልና ምልክት ስለሌላቸው ከሴት ጋር ሩካቤ
ፈጽመው የማያውቁ ሆነው ሳለ ደናግል አይደሉም ለማለት አይቻልም፡፡ ሩካቤን ፈጽመው የማያውቁ ሴቶች ስወለዱ ጀምሮ ማኅተመ ድንግልና
የሌላቸው ሊሆኑ ይችላሉ ወይም ከጊዜ በኋላ በከባድ የአካል እንቅስቃሴ፣ በአደጋ፣ በሕክምና ወይም በዕድሜ ብዛት ምክንያት ማኅተመ
ድንግልና ሊፈርስባቸው ይችላል፡፡ እንዲህ ያሉ ሴቶች ማኅተመ ድንግልናቸውን ቢያጡ ሩካቤ ፈጽመው እስካላወቁ ድረስ ደናግል መባላቸው
የተጠበቀ ነው፡፡
ወንዶቸች ሩካቤ ፈጽመው ሳለ እንደ ሴቶች የሚገሠሥ ማኅተመ ድንግልና ስለ ሌላቸው ድንግልናቸው አልፈረሰም እንደማይባል
ሁሉ ሴቶች ሩካቤ ሥጋ እየፈጸሙ በልዩ ልዩ ምክንያት ማኅተመ ድንግልናቸው ባይገሠሥ መደበኛ ሩካቤ እስከ ፈጸሙ ድረስ ደናግል ሊባሉ
አይችሉም፡፡ አንዲትን ሴት ድንግል የሚያሰኛት ሥራዋና ዝንባሌዋ ብቻ ነው፡፡
ማኅተመ ድንግልና ሕግ ይባላል፡፡ ምክንያቱም ‹‹አታመንዝር›› የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ መፈጸምና አለመፈጸምን የሚያስታውቅ
የሕግ ምልክት በመሆኑ ነው፡፡ እስከ ጋብቻ በንጽሕና ተጠብቆ ከሚኖርበት የድንግልና ሕግ ወደ ጥንድነት የሚተላለፉበት ጋብቻም
‹‹ሕግ›› ይባላል፡፡ ያገባ ለማለት ‹‹ሕጋዊ›› ይባላል፡፡ ለዚህ ነው አንድ ወንድ የአንድን ሴት ድንግልና ሲገሥ ሕጓን ወሰዳባት
ማለት ትዳር እንዳትይዝ፣ ሕጋዊ ባል እንዳይኖራት አደረጋት ማለት ነው፡፡
በሌላ መልኩ ማኅተመ ድንግልና ዓይን ይባላል ወይም በዓይን ይመሰላል፡፡ ይህም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የተናገረውን
‹‹ድንግላናቸውን እንደ ዓይን ብሌን ይጠብቁ ዘንድ ላላገቡ
ደናግል ምከራቸው አስተምራቸው›› መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ሴት በድንግልናዋ (በዓይን) ባሏን ታያለች እሱም እንዲሁ፡፡ ድንግልና
ባልና ሚስት በተለየ መልኩ የሚተያዩበት የማይመረመር ‹‹ዓይን›› ነው፡፡ የኑሮ ደረጃቸውን በድንግልና ሆነው መርምረውና ተመልክተው
ያገቡ ሰዎች አይጸጸቱም፡፡ ምክንያቱም አንድ ሰው ደረጃው ማግባት ይሁን መመንኮስ በሚገባ ለይቶ ማወቅ የሚችለው ንጽሕናውን ጠብቆ
ለመኖር ከቻለ ብቻ ነው፡፡ ዓይን ታማሚ ብትሆን ሰውነት ሁሉ ጨለማ እንደሚሆን ሁሉ (ማቴ. 6፡22) ድንግልናም በሕገ ወጥነት በዝሙት
ሥራ ካጠፉት አንድ ሰው ሰውነቱ ሁሉ እንደጨለመበት ሊያምን ይገባል፡፡ምክንያቱም ድንግልና ሃይማኖትና ምግባር መሠረታቸውን ለቀው
እንዳይኖር የሚያደርግ ጽኑ መሠረት ነውና፡፡
የድንግልና ዓይነቶች
በሁለት ወገን ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው የድንግልና ዓይነት ድንጋሌ ሥጋ ነው፡፡ ሁለተኛውም ድንጋለ ነፍስ
ይባላል፡፡ ድንጋሌ ሥጋ ለድንጋለ ነፍስ መገለጫ ፣ ጥላ ወይም አምሳል ነው፡፡ አማናዊ ድንግልና የምትባለው ድንግልና ግን የነፍስ
ድንግልና ናት፡፡ (ዮሐ.ተግ. 28)፡፡ ድንጋሌ ሥጋ በግዘፍ የሚታይ በገሢሥ (የሴቶች) የሚታወቅ ሲሆን ድንጋሌ ነፍስ ግን ረቂቅ
ነው፡፡ ነፍስ ግን ድንግልናዋ በብዙ ጎዳና ነው፡፡ አንድ ጊዜ በኃጢአት ተግባርና ሐሳብ የተወሰደበት ድንግልና በንስሐ ይመለስላታል፡፡
የነፍስን ድንግልና የሚያጠፋው የኃጢአት ሥራና ሐሳብ ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ በቅዱስ ጋብቻ የተወሰኑ ባልና ሚስት በሚፈጽሙት ሩካቤ
ድንጋሌ ሥጋቸው ሲጠፋ የነፍስ ድንግልናቸው ግን አይወገድም፡፡ ምክንያቱም በሕጋዊ ባለትዳሮች ሩካቤያቸው ኃጢአት ባለመሆኑ ነው፡፡
እስኪ ይህን አስቡ ወደ ትዳር ዓለም ሳትገቡ ድንግልናችሁን ያጣችሁ አልጸጸታችሁም? በድንግልና ሆናችሁ
በጋብቻችሁ የስጋ ድንግልናችሁን ስታጡስ ተጸጸታችሁ? በፍጹም አይጸጽትም ምክንያቱም የነፍስ ድንግልና ስላላጣችሁ ነው፡፡ ከጋብቻ
በፊት ግን የስጋም የነፍስም ድንግልና ስላጣችሁ ጸጸት ይሰማችኋል ወይም ደግሞ በትዳር መገኘት የነበረበት ደስታ የማይገኘው ለዚህ
ነው፤ አንዳንዴ ጊዜ እንደውም በማግባታችሁ የምታዝኑበት ጊዜ የለም? ምክንያቱ እሱ ነው ድንግልና! ከጋብቻ በፊት፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ
አፈወርቅም በድንግልና ያገባች ሴት ‹‹ባልም ብታገባ ድንቅ በሚሆን ድንጋሌ ነፍስ ድንግል ናት›› ይላል፡፡ (ዮሐ.ተግ. 28)
ድንጋሌ ነፍስ የሌለው
ሰው የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርስም፡፡ ይህም ማለት የነፍስን ድንግልና የሚያጠፋው ኃጢአት ብቻ በመሆኑ ኃጢአቱን በንስሐ ያላራቀ
ወይም ንስሐ ያልገባ ሰው ወደ መንግሥተ ሰማያት አይገባል ማለት ነው፡፡ ራዕ. 14፡4 ‹‹ከሴቶች ጋር ያልረከሱ እነዚህ ናቸው ድንግሎች
ናቸውና በጉ ወደሚሄድበት የሚከተሉ እነዚህ ናቸው፡፡ ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኩራት እንዲሆኑ ከሰዎች የተዋጁ እነዚህ ናቸው፡፡››
ዮሐ.ተግ. 28 ‹‹ድንጋሌ ነፍስ ከመርዓዊው ክርስቶስ ጋር አንድ ያደርጋል፡፡ ወደ መንግሥተ ሰማያት ያስገባልና፡፡››
ደናግላንና አለባበሳቸው
ለዐቅመ ሔዋን የደረሱና
ያልደረሱ ደናግላን የሆኑና ያልሆኑ ሴቶች ተለይተው የሚታወቁበት የፀጉር አሠራር፣ አለጫጨትና የአለባበስ ሁኔታ በየሀገሩ ይገኛል፡፡
ጥንቱን የሀጋራችንንም ብሔር ብሔረሰቦች ባህል ወደ ኋላ መለስ በሉና አስቡ፤ የዛሬው ግን....፡፡ ድሮ እስራኤላውያን ደናግል ለፍሬ
አልደረስንም ሲሉ ወርቅ እንደ አበባ የፈነዳበት ነጭ ሐር ለብሰው ይታዩ ነበር፡፡ ደናግላን የተለየ አለባበስ አንደ ነበራቸው መጽሐፍ
ቅዱስ ይመሰክራል፡፡ትዕማር ድንግል በነበረች ጊዜ ብዙ ኅብር ያለውን ልብስ ለብሳ ነበር እንዲህ ያለውን ልብስ የንጉሡ ልጆች ደናግሉ
ይለብሱት ነበርና፡፡ ነገር ግን በተደፈረችና ክብሯን ባጣች ጊዜ ‹‹ብዙ ኅብር ያለውን ልብስዋን ተርትራ እየጮኸች ሄደች›› 2ሳሙ.
13፡18-19፡፡ ዛሬስ ሴቶች እህቶች ቀሚሳቸውን ቀድደው፣ አጭር ጣል የተደረገች ቀሚስ መሳይ ልብስ፣ የተወጣጠረች ቲሸርት፣ ዳሌ
የምታሳይ አጭር ነጠላ፣ የውስጥ ሰውነት የሚያሳይ ስስ ቀሚስ፣ ሰይጣን አምላኪዎች የሚያደርጉት የፀጉር አሠራር ምንን ያሳያል? አንዲት
ሴት ድንግል ሆና እያለች የተቀደደ ቀሚስ፣ አጭር ቀሚስ... ለብሳ ብትሄድ ሌላ መልእክት የለውም ‹‹እኔ ድንግል አይደለሁም፣ እኔ
ዘማ ነኝ፣ ተዋርጃለሁ፣ ሕጋዊ ትዳር መያዝ አልፈልግም...›› ማለት ነውና ራሳችንን እንጠብቅ፤ እኛ ክርስቲያኖች አለባበሳችን አስተማሪ
መሆን አለበት፣ ምሳሌ እንኳን ባይሆን ለሌሎች መሰናክል መሆን የለብንም፡፡
መደንገል እስከ መቼ?
ይህ እንደ ሰው የአኗኗር
ዘይቤ ይለያያል፡፡ ለአንዱ ጋብቻውን እስኪፈጽም ድረስ ሲሆን ለሌላው ደግሞ እስከ ዕድሜ ልክ ይሆናል፡፡
1. እስከ እድሜ ልክ መደንገል፡- እስከ ሞት ድረስ ድንግልናቸውን
መጠበቅ የሚኖራቸው በድንግልና ለመነኮሱት ነቸው፡፡ በርግጥ ምንኩስና ድንጋሌ ሥጋ ያላቸው ሰዎች ብቻ የሚጓዙበት ጎዳና አይደለም::
ባለ ትዳር የነበሩ ወይም ሳያገቡ ለዝሙት ተጋልጠው ድንጋሌ ሥጋቸውን
ያጡ ሰዎችም በንስሐ ተመልሰውም ይኖሩበታል፡፡ እንደ ቀላል የሚታይ ግን አይደለም፡፡የዓለምን ኑሮ እንደ ልብ ኖረው ሲሰለች ብቻ
የሚገባበት አድርጎ ማሰብ ስሕተት ነው፡፡ ምንኩስና በድንግልና ሲሆን ብዙ ጸጋና ክብር ያመጣል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ከመመንኮስ በተጨማሪ
የግድ ድንግል ሆኖ መገኘትን የሚጠይቁ ብዙ ታላላቅ መንፈሳዊ የሹመት ደረጃዎች እና የአኗኗር ዘይቤዎች ይገኛሉ፡፡ በድንግልና መመንኮስ
ጣዕመ ዓለምን ሳይቀምሱ በመሆኑ ከምንኩስናም በኋላ ለሚኖሩት የንጽሕና ኑሮ አጋዥነት ይኖረዋል፡፡ ምክንያቱም ከመነኮሱበት ዓላማ
ጋር የማይስማማ በልቡናቸው የሚቀር የዓለማዊ ኑሮ አሻራ ባለመኖሩ ነው፡፡ ‹‹ያላዩት ሀገር አይናፍቅም›› ይባል የለ፡፡ በርግጥ
ይህን የመሰለ የምናኔ ኑሮ ለመኖር ስጦታ ያፈልጋል (1ቆሮ. 7፡7)፡፡ ምንም እንኳን በጋብቻም ሆነ በምንኩስና መኖር ሁለቱም የእግዚአብሔር
ስጦታዎች ቢሆኑም በጋብቻ መኖር ለሁሉ የተሰጠ ሲሆን ምንኩስና ግን መመረጥና መታደል የሚጠይቅ ነው (ማቴ. 19፡11)፡፡
ድንግልናን በሕይወት ዘመን በሙሉ ጠብቆ በምንኩስና መኖር ከስጦታነት
በተጨማሪ በፈቃደኝነት ሊደረግ የሚገባው ነገር ነው እንጂ የሚገደድበት ተግባር አይደለም፡፡ ወጣቶችም በኛ ውሳኔ እና በእግዚአብሔር
ፈቃድ ወደዚህ ሕይወት መግባት ይቻላል፡፡ የሚበልጥ ሕይወት ነውና፡፡(1ቆሮ. 7፡38፣ ማቴ. 19፡21፣ ኤር. 1፡5፣ 1ቆሮ.
7፡25-26)፡፡
2. እስከ ጋብቻ ጊዜ ድረስ መደንገል
በሀገራችን የድንግልና ሕይወት ከጥንት አባቶቻችን ጀምሮ የተከበረና
በማንኛውም ሰው ዘንድ ዋጋ ያለው ነገር ነበር፡፡ እስከሚያገባ
(ታገባ) ድረስ በድንግልና መቆየት ግዴታው (ዋ) ነበር ነውም፡፡ ይህንንም ለማድረግ ሴቷና ወንዱ እንዳይተያዩ፣ እንዳይገናኙ እርስ
በርሳቸው ስሕተት እንዳይሰሩ በማለት በልዩ ልዩ ዘዴ ይጠብቁ ነበር፡፡ ቶሎ እንዲያገቡም ይደረግ ነበር፡፡
ባሁኑ ጊዜ ደግሞ እጅግ በዛ እንጂ በሁሉም ረገድ እስኪደራጁ ድረስ
ሳያገቡ መዘግየት መልካም ሆኖ ሳለ ስለ ንጽሕናቸው አጠባበቅ ደግሞ ምንም የተወሰደ እርምጃ ስለሌለ የድንግልና ሕይወት እየቀለለና
ዋጋ እያጣ መጥቷል፡፡በጨቅላ እድሜያቸው ያገቡ ልጆች ጋብቻቸውን እንዳይጸናና ችግር እያጋጠማቸው እንደሆነ ሁሉ ሳያገቡ ድንግልናቸውን
የሚያጡ ስድ የለመዱ የዛሬ ተጋቢዎችም ራሳቸውን ገትቶ መያዝ ስለማይሆንላቸው ከትዳር በኋላ ስያዝኑና ሲያለቅሱ ማየት የዘወትር ክስተት
ሆኗል፡፡
ለእስራኤላውያን ድንግልናቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው በሕግ ተስጥቷቸዋል፡፡
ይህም ድንግልናውን የሚያጠፋ ሁሉ በድንጋይ ተወግሮ፣ በእሳት ተቃጥሎ ይገደል ነበር፡፡ ዛሬ በገጠራችን አከባቢዎች አንድ ሰው የትዳር
አግኝቶ እስከሚያገባ ድረስ ድንግልናውን ጠብቆ ይኖር ነበር፡፡ ከትዳር በኋላ ወንድ ድንግልናውን በከበረ ስጦታነት በረቂቅ መንገድ
ለሚስቱ ሲያስረክብ ሴቲቱ ደግሞ ሕጓን ሊታወቅ በሚችል መልኩ (በግዘፍ) ለባሏ ትሰጣለች፡፡ ይህ ሲሆን በባልና በሚስት መካከል ጥልቅ
የሆነ መከባበር፣ መተሳሰብ፣ መተማመንና መፋቀር ይጎልብታል፡፡ ከዚህ ውጭ የሆነ ጋብቻ ግን እንደው መቻቻል እንጂ መፋቀር የጎደለው
ይሆናል፡፡ በእናንተ አከባቢ ያለ ድንግልና ከተጋቡ ሰዎች ምን አነበባችሁ? እናንተስ?
ጋብቻ በደናግላን ያምራል፡፡ የብዙ ቅዱሳን ወላጆችም በድንግልና ኖረው
በቅዱስ ጋብቻ የተወሰኑ ናቸው፡፡ድንግልናን እስከ ጋብቻ ድረስ ጠብቆ ማቆየት ለሰው ልጅ በሙሉ የተሰጠ ችሎታ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ
በውዴታ መደረግ ያለበት ነገር ብቻ አይደለም፡፡
በሀገራችን እንኳን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ድንግልናዋ የጠፋ ሴትን
ማንም አያገባትም ይልቁንም ድንግልናዋን የወሰደ ሰው በግድ እንዲያገባት ይደረግ ነበር፡፡ እሷም ባያገባት እንኳን ተመልሳ ትዳርን
አታስብ፤ ያለ ድንግልና የሆነ ጋብቻ ጣዕም የለውምና፡፡
ስለዚህ ወጣቶች ራሳችንን ጠብቀን ከኛ በታች ያሉ ታዳጊዎችንም አስተምረን
የቀደመው ባህላችንን እንመልስ እላለሁ፡፡
No comments:
Post a Comment