በእንተ ርእስየ

Friday, October 27, 2017

ሕይወተ ወራዙት ክፍል 12/17- በአማርኛ



ክፍል አስራ ሁለት
.... የቀጠለ....ስለ ትውዝፍት
አፍአዊ ጌጥ መውደድ ‹‹አምልኮ ጣዖት ነው››
መታበይ፣ መኩራራት፣ ማማረጥ፣ተስፋ መቁረጥን የመሳሰሉ ኃጢአቶች በሙሉ በአብዛኛው አፍአዊ ጌጥን ከመውደድ ይወለዳሉ፡፡ ሰዎች ይህን ሲያገኙ እንደሚኮሩና ደስ እንደሚላቸው ሁሉ ያጡትም እንደሆነ በሕይወታቸው አንድ ታላቅ ነገርን እንዳጡ በመቁጠር ያለ መጠን ሲማረሩና ሲያዝኑ ይገኛሉ፡፡ አልፎ ተርፎም በተገቢው መንገድ የሚሹትን አፍአዊ ጌጥ ካለገኙ በመስረቅ፣ በመዋሸትና ፍላጎታቸውን ሊያሟሉ ለሚችሉ ሀብታም ሰዎች በመገዛት ያሟሉታል፡፡ ይህ መገዛታቸው ልክ በማጣቱ ሐሳባቸው ይሟላላቸው ዘንድ ለዝሙት ከመንበርከክና ከመግደል አንሥቶ ለማንኛውም የኃጢአት ተግባር ወደ ኋላ አይመለሱም፡፡ አፍአዊ ጌጥ ያጡበትንም ሰው እስከ መካድ ይደርሳሉ፡፡
ጌጥን መውደድ ባርነት ብቻ ሳይሆን ‹‹ጣዖት ማምለክ›› ነው፡፡ በተለይ ያለጌጥ ምንም ነገር የማይሆንልሽ፣ ጌጣ ጌጦችሽን ዐሥር ጊዜ ሣጥን ከፍተሸ የምትመለከቺ፣ ዕጣን የምታጭሽ፣ ሽቶ የምትቀቢ፣ የምታናፍሽ ከሆነ ይህ ጣዖት ሆኖብሻል፡፡ ጣዖት የሚያመልኩ ሰዎች ከዚህ የተለየ ምን ያደርጋሉና፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ የሚያሰጠው የዋሕ እና ዝግተኛ መንፈስ እንጂ በሽቶ፣ በቅባትና ማኳኳያ ነገሮች አይደለም፡፡2ጢሞ.4፡5፡፡ ዛሬ በዓለም ላይ ያለው ጌጣ ጌጥና ኮስሞቲክስን ተመለከትሽ ለጊዜው ያሳመሩ ይመስሉና ከጊዜ በኋላ ግን በተፈጥሮ ያለንን ነገር ላይመለስ አበላሽቶ ይሄዳል፡፡ ከዚህ ከተረፈ ደግሞ ይህም እንደ ልብስ ዘማ ያስብልሽ ይሆናል እንጂ ሌላ ትርፍ የለውም፡፡ ዘማዊያንስ የሚያደርጉት ይህን አይደለም እንዴ? የሽቶ ገበያ ለምን እንደተወደደ ታውቂያለሽ? ለዝሙት ዓለም ስለሚውል እኮ ነው፡፡
አፍአ ጌጥን አለመጠቀም ያስመሰግናል፡፡ ለዚህም በመልክዐ ማርያም ‹‹እንሶስላ መጠቀምና ሌላ ምድራዊ ጌጥን ላልፈቀዱ የእግር ጥፍሮችሽ ሰላምታ ይገባል›› ይላል፡፡ ስለዚህ እኛ ክርስቲያኖች የመጋጌጫ ነገሮች ከክርስትናዬ ጋር ይሄዳል ወይ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡
ስለ ፀጉር አያያዝ
የፀጉር አያያዝ ሕገወጥ እንዳይሆን ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ለእናንተ ጠጉርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጎናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ፡፡›› 1ጴጥ. 3፡3  1ጢሞ. 2፡10፡፡ በ1ቆሮ. 11፡15 ‹‹ፀጉርዋ መጎናጸፊያ ሊሆን ተስጥቶአታል›› ስለዚህ ፀጉርዋን ማስረዘም ተገቢ ነው፡፡ ፀጉርዋን መቁረጥ ወይም መላጨት የሚያሳፍራት መስሎ ካልተሰማት መቁረጥ ወይም መላጨት መብቷ ነው፡፡ ፀጉርዋን ካስረዘመች ግን በጸሎት ጊዜ ራሷን መሸፈን/ መከናነብ አለባት፡፡ 1ቆሮ. 11፡6
ወንድ ግን ፀጉሩን ቢያስረዝም ነውር ይሆንበታል፡፡ ሠለስቱ ምዕት ስለ ፀጉር በተናገሩበት በፍትሐ ነገሥት ‹‹ፀጉርህን ስበህ እስክታየው ድረስ አታሳድገው›› ብለዋል፡፡ ሐዋ. 18፡18 ያንብቡ፡፡ ካህናት ፀጉራቸውን አያሳድጉ የሚለው ናዝራውያንን አይመለከትም፡፡ እነ መልከጼዴቅ፣ ሶምሶን፣ ነብዩ ኤልያስ፣ መጥምቁ ዮሐንስ ፀጉራቸውን አይላጩም፡፡ ዘኁ. 6፡5 መሳ. 13፡5፡፡ ወንዶች ፀጉራቸውን ስያሳጥሩ ጋሜ፣ ቁንጮን፣ ጌጥን ልዩ ልዩ ቅርጽ ማውጣት የለባቸውም፡፡ ዛሬ በየፀጉር ቤቱ የምናየው የፀጉር ስታይል፣ ወንዶች እየተቆረጡ ያለው ፀጉር ስታይልስ ሕገወጥ መሆኑን እናስተውል አባቶች ግን ‹‹በፀጉርህ ላይ ጌጥ አትተው›› ይላሉ፡፡
ስለ መልክ ካነሳን ደግሞ መጨነቅ አያስፈልግም፡፡ እግዚአብሔር የሰጠንን በአግባቡ ከመያዝ ውጭ ልንጨነቅ አያስፈልግም፡፡ ምሳ. 11፡22 ውበት ሐሰት ነው ደም ግባትም ከንቱ ነው፤እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን እርሷ ትመሰገናለች፡፡

No comments:

Post a Comment