በእንተ ርእስየ

Wednesday, October 25, 2017

ሕይወተ ወራዙት ክፍል 5/17-በአማርኛ



ክፍል አምስት
ግብረ አውናን የሚያስከትለው ጉዳት
ግብረ አውናን ውጥረትን ለፈጠረ አንድ ችግር የተሳሳተ አማራጭን መጠቀም እንደመሆኑ መጠን በሕይወት ዘመናችን ሁሉ ብርታትና ጥንካሬን የሚጠይቁ መንገዶችን እንድንሸሽ ያለማምዳሉ፡፡ ሰነፍ እንድንሆን ያደርጋሉ፡፡ ግብረ አውናን ኃጢአት እንደመሆኑ መጠን በዚህ ዓለምና በወዲያኛው ዓለም ቅጣትን ያስከትላል፡፡ በዚህ ዓለም እንደ አውናን መቀሠፍ (ዘፍ. 38፡9)፣ ሰላም ማጣት፣ ቁጭት፣ ጸጸት፣ ጭንቀት፣ መረበሽ፣ ንጽሕ ያለመሆን ስሜት ወዘተ ያስከትላል፡፡ ካደገ ደግሞ ወደ ዝሙትና ግብረ ሰዶም መምራት፣ ተስፋ መቁረጥ፣ አጉል ጸጸት (ኀፍረተ አካልን ተናዶ እስከ መቁረጥ ሊያደርስ ይችላል)፣ አጉል ትሕትና (መንፈሳዊ አገልጋዮች ከሆኑ አገልግሎቱ ንጽሕናን የሚፈልግ በመሆኑ ኑሮአቸውና መንፈሳዊ አገልግሎታቸው ሳይጣጣም ሲቀር ማገልገል አይገባኝም በማለት ከትሩፋትና ከበጎ ሥራ ራሳቸውን የሚያሸሹ አሉ)፡፡ ነገር ግን ክፉ ሥራን እንጂ የትሩፋት ሥራን መሸሽ በምንም መልኩ አይበጅም፡፡ በጋብቻ ውስጥ አንዱ ለሌላው ወገን ደስታና እርካታ ማሰቡ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ሴጋ ደግሞ የራስን ደስታና እርካታ ብቻ የማሰብ ልምድን ያሳድጋል፡፡

ከግብረ አውናን እንዴት መላቀቅ ይቻላል
1.       የማር ጠብታ ልብስ ላይ የወደቀ እንደሆነ በፍጹም የሚለቅ አይመስልም ነገር ግን ትንሽ ለቅለቅ ያደርጉት እንደሆነ ወዲያውኑ ይለቃል፡፡ ይህ ክፉ ልማድም እንደማር በቀላሉ ባይሆንም ከልብ በመጸጸት በጠንካራ መንፈስ ከተነሡ ሊያስወግዱት ይቻላል፡፡ ተስፈ አለመቁረጥ፡፡
2.       መሰንጋት ልማድ ነው፡፡ ልማድ ደግሞ በልማድ ይሸነፋል፡፡ ከዚህ ልማድ ጋር ለመዋጋት ከመነሣትህ በፊት ‹‹ይህን ልማድ ምን ያህል ከልቤ ጠልቼዋለሁ›› በማለት ራስን መጠየቅ ያፈልጋል፡፡ መላልሰህ የምትሰናከለው ሳትጸጸት ቀርተህ ሳይሆን ጣዕሙ ከልቡናህ ስላለና ጎጂነቱ ዘልቆ ወደ ልብህ ስላልገባ ነው፡፡ እሱን ለማውጣት መታገል ያስፈልጋል- በጾም፣ ጸሎት፣ ስግዳት፣ መጻሕፍትን ማንበብ፣ መዝሙራትን መዘመር... ግድ ይላል፡፡
3.       ‹‹ተዐቅቦ›› መከልከል- መቆጠብ ያስፈልጋል፡፡ ወደዚህ መጥፎ ሀሳብ ልቡናህን የሚስቡትን ነገሮች ከማየት፣ ከመስማት፣ ከመንካትና ከመሳሰሉት ነው፡፡ የሴቶችን ገላ በፊልም በአካልም ከማየት መቆጠብ፣ በመዋኛና በመጠመቂያ ቦታዎች ራስህን ጠብቅ የሴት ልጅን መልክና ቅርጽ መርዘህና አትኩረህ አትመልከት፣ ስለ ዝሙት የሚያሳስቡ ስዕሎችን፣ ጽሑፎችንና ወሬዎችን መሸሽ ቦታ አለመስጠት ንቆ ማለፍ ያስፈልጋል፡፡
4.        ዘወትር ልቡናህ የሚጠመድበትን ነገር ፈልገህ አድርግ፡፡ ቦዘኔ አትሁን፣ ትጉህ ሠራተኛ ሁን፣ ሥራህም በእንቅስቃሴ የተሞላ ወይም አእምሮን ያለ ዕረፍት የሚያሠራ ይሁን፡፡ በትርፍ ሰዓትህ የሚነበብ ወይም ሌላ የሚሠራ ሥራ ፈጥረህ ሥራ፡፡
5.       ‹‹ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው›› የሚለውን ቃል አስብ፡፡ በዚህ ክፉ ልማድ ተጠምደህ ሳለ ለብቻህ መሆንን አትውደድ፡፡ ቢቻልህ አኗኗርህና መኝታህ ከምታፍረውና ከምታከብረው ሰው ጋር ይሁን፡፡ ከብቸኝነት ይልቅ መወያየትን ይልቁንም መንፈሳዊ ውይይትን ዘወትር አድርግ፡፡ በጸሎት ከሚረዳህ መንፈሳዊያን መምህራንና አባቶች ጋር ጊዜ ማሳለፍን ውደድ፡፡
6.       እንቅልፍ የያዘህ ስለ መሰለ ብቻ ወደ መኝታ አትሂድ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ስትተኛ ውለህ እንቅልፍ ያምርሃልና፡፡ ነገር ግን ሰይጣን ሊፈትንህ ከሆነ በምትተኛበት ጊዜ እንቅልፍ ከአይንህ ይርቃል፡፡ ተከትሎም ፈተናው ይመጣና ወደ ዝሙት ሕሊናህ ይሳባል፡፡ ሰውነትህን በመዳበስ ፍትወትህን ለማርካት ትጥራለህ፡፡ ስለዚህ ከመተኛትህ በፊት በደንብ መድከምህንና ቶሎ ማሸለብ መቻልህን መርምረህ ተኛ፡፡ አንተን/ አንቺን አጋጥሞህ/ሽ አያውቅም?
7.       ጸሎት ማድረግንም አትርሳ የሚረሳ ነገር አይደለም፡፡ ስትተኛ በጀርባህ ወይም በሆድህ አትተኛ፡፡ ከዚህ ይልቅ በጎንህ ለመተኛት ሞክር፡፡ አመጋገብህ በልክ ይሁን፣ ጾምን በተገቢው መንገድ ጹም፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትን አንብብ፡፡ የመንፈሳዊ ሙያ ባለቤት ከሆንክ የምታውቀውን የዜማ ድምፅ አውጥተህ አንጎራጉር:: ያም ባይሆን የምትችለውን መዝሙር ዘምር፡፡
8.      እንዲህ ያለ ፈተና ሲነሣብህ አንድ ዓይት የዐካል እንቅስቃሴ (ሰፖርት) ሥራ፡፡ ወይም ወዲህና ወዲያ ተንቀሳቀስ፡፡ ከዚህም ሁሉ ይልቅ ደግሞ ከሆነልህ መስገድ ይመረጣል፡፡ ሽንት መሽናትም ጥሩ መድኃኒት ሊሆንህ ይችላል፡፡ በጊዜው ጠበል መጠመቀንንም ቸል አትበል፡፡ ደግሞ ጥንቃቄ የተሞላበት ይሁን፤ ዓይኖችህን ከሴቶች አካል ንቀል፡፡
9.       ሰውነትህ ሲበላህ ይልቁንም ወደ አባለ ዘርዕ አከባቢ ከሆነ ትኩረት ሰጥተህ አታስበው፡፡ ምክንያት እንዳይሆንብህ ተጣጥበህ ንጹሕ ለመሆን ሞክር፡፡ የበላህ ቦታ ግን በምንም መልኩ አትከከው፡፡ ከዚያ ይልቅ መጽሐፈ መነኮሳት ‹‹ሕመም ወይም ማሳከክ በተሰማህ ቦታ ላይ በሕሊናህ አማትብበት፡፡ በሕሊናም ማለቱ የሚያይህ ሰው ነገር እንዳይመራመርህ ለማድረግ ነው፡፡ በተረፈ ግን አጥብቀህ ጸልይ፡፡››
ትኩረት የሚሹ
ከግብረ አውናን ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው በጋብቻ ውስጥ ያሉ በማንኛውም መልኩ ሩካቤ ሲፈጽሙ ኮንደም መጠቀም አይፈቀድም፡፡ ምክንያቱም እንደ አውናን ዘርን ከማኅፀን ውጭ ማፍሰስ ነውና፡፡ በትዳር ያሉ ባልና ሚስት ኮንደምን የሚጠቀሙት ወሊድ ለመቆጣጠር ነው፡፡ ነገር ግን በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት ማንኛውንም ወሊድ መቆጣጠሪያ መንገድ መጠቀም አይቻልም፡፡ ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታዎች እንጂ በእኛ ፎርሙላ የሚገኙ አይደሉም፡፡ ነገር ግን በባልና ሚስት መካከል የሚደረገው ወሲብ ሥርዓት ያለው መሆን አለበት፡፡

ይቀጥላል

2 comments:

  1. መንፈሳዊ አገልጋዮች sibal, diakonatin yatekalilal?

    ReplyDelete
  2. yhen yarege hitsan dikuna mekebel ychilal?

    ReplyDelete