በእንተ ርእስየ

Friday, October 27, 2017

ሕይወተ ወራዙት ክፍል 17/17- በአማርኛ



ክፍል አስራ ሰባት
ምዕራፍ አስር
ወጣት እና አደንዛዥ ዕፀዋት
በዘማናችን የሰው ልጆች አደንዛዥና አፍዛዥ ወይም ከመጠን በላይ አነቃቂ የሆኑ መርዛማ ዕፀዋትን ባሉበት ሁኔታ ከመጠቀም ማለትም አኝኮ ከመዋጥና ጨምቆ ከመጠጣት አልፈው ሄደዋል፡፡ ዕፀዋቱን ንጥረ ነገር ለይተው በማውጣት በመርፌ ለመጠቀም በሚመች መንገድና በሚዋጡ እንክብሎች መልክ አዘጋጅተው ይጠቀሟቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ ከአንድ ወር በላይ ሊያነቁ ወይም አንድን ሰው ችግሩንና ጉዳቱን እንዲረሳ ሊያፈዙት የሚችሉ ናቸው፡፡
ዛሬ ዛሬማ አደንዛዥ፣ መርዛማና አደገኛ ዕፀዋት ከተጠቃሚዎቻቸው አኀዝ መበርከት ባሻገር በግለሰብእና በአገር ደረጃ ዋነኛ የሀብት ማግኛ መንገድ ሆነው እየተቆጠረ ነው፡፡ በፊት በድብቅ ወደ ከተሞች ይገባ የነበሩ ዕፀዋት ዛሬ ግን በይፋ ይጫናሉ፣ በአደባባይ ይቃማሉ...፡፡ ቤተ ክርስቲያን ግን ለዘመናት ስታወግዝ ኖራለች፡፡ ወደፊትም ትኖራለች፡፡
ትንባሆ ማጨስ፣ ጫት መቃም፣ ሺሻ መማግ በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ተገቢ አይደሉም፡፡ ምክንያቱም እኛ የአግዚአብሔር ቤተመቅደስ ነን፡፡ በቤተ ክርስቲያን ደግሞ የሚታጠነው ዕጣን እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ እንዲሁም በስጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ የሚለውን የእግዚአብሔር ሕግ መጣስ ይሆንብናል፡፡ 1ቆሮ. 6፡20፣ 1ቆሮ. 3፡17፡፡
ሲጋራ፣ ጫት እና የመሳሰሉት ሁሉ ሱስ በመሆን የሰው ልጆች በተፈጥሮ ያገኙትን ነጻ ፈቃድ ስለሚጻረሩ ሰው ሊጠቀምባቸው አይገባም፡፡ባሪያ ያደረገን ነገር ደግሞ ከእግዚአብሔር ይለየናል፡፡ 1ቆሮ. 6፡12 ‹‹ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ ሁሉ ግን አይጠቅምም። ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ በእኔ ላይ ግን አንድ ነገር እንኳ አይሠለጥንብኝም፡፡›› ይህን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ በፍትሕ መንፈሳዊ ደግሞ ‹‹አእምሮንና አካልን ሁሉ የሚጎዳና የሚገድሉ ተክሎች የተከለከሉ ናቸው፡፡›› (ፍ.ነ.አን.23፡804-807)

ሕይወተ ወራዙት ክፍል 16/17- በአማርኛ



ክፍል አስራ ስድስት
ምዕራፍ ዘጠኝ
ዘፈንና ወጣቶች
ዘፈን በቅኔና በግጥም ከልዩ ልዩ የድምጽ መሣሪያ ጋር እየተቀነባበረ የሚቀርብ ስልት ያለው ጩኸት ወይም ድምጽ እና   የተውኔት ዲቃላ ሲሆን ዓለማውያን ሰዎች ደስታቸውን የሚገልጡበት ነው፡፡ ዘወትር ለሥጋ ፍላጎት የተሟላ ኃላፊ ፍቅርን ያወሳል፡፡ስለዚህም ፈጣሪ ሳይሆን ሰው እንዲመለክ በማድረግ የሰይጣን ተገዥ መሆን ማረጋገጫ ነው፡፡ አሁን አሁንማ በግልጽ ሰይጣንን የሚያወድሱ ሰዎች ተነስተዋል፡፡
ዘፈን ከአካል እንቅስቃሴ ጋር ያለውን ትስስር ከመረመርክ ይጮኻሉ፣ ተንቀሳቃሽ ፊልሞችም እንዲሁ በድምጽ የታጀቡ ናቸው ለመቀስቀስ እና ተጽእኖ ለመፍጠር ነው፡፡ ዘፈንም እንዲሁ ሰውን የመግዛት ኃይል አለው፡፡
(ሀ) ዘፈን የአጋንንት ስራ ነው፡፡ አጋንንት ይዘፍናሉና (ኢሳ. 13፡21) እንዲሁም በ1መቃ. 36፡27-28 ‹‹... እየዘፈኑም ከአጋንንት ጋር ይጫወቱ ነበር፡፡ አጋንንትም ጫወታቸውንና ዘፈናቸውንም ሁሉ ያደንቁላቸው ነበር፡፡›› እስኪ በሀገራችንም ሆነ ሌሎች ሀገሮች ዘፋኞች ፀጉራቸውን አንጨብረውና በመጠጥ እና በአሺሽ ጦዘው አንገታቸውን በማወናጨፍ የሚዘፍኑት ዘፈን መገኛው የባለዛሮች ነው፡፡  እንደ ቅዱስ ሐዊ ትምህርት ዘፈንና ዳንስ ከሰይጣን የተገኘ ነው፡፡ እንዲሁም የጭፈራ ዓይነት ሁሉ ምንጮች አጋንንት ናቸው፡፡
ዘፋኝነት የሰጋ ስራ ነው፡፡ (ገላ. 5፡21) ሮሜ. 13፡13፣ 2ጴጥ. 2፡13-15፡፡ ዘፈን በዜማው፣ በግጥሙና ከእርሱ ጋር በተጎዳኘ ባሉ ነገሮች ማለትም በስካር፣ በዳንስ፣በጭፈራ፣ በእስክስታና በአጠቃላይ ውዝዋዜን በመሳሰሉ አጋሮቹ በመታገዝ ወደ ዝሙትና ወደ ከፋ ኃጢአት የሚያመራ ነው፡፡ ዛሬም የምናየው ይህንን ነው፡፡ ስለዚህ ወጣቱ ከዚህ መራቅ አለበት፡፡ ዘፈን የሰይጣን ነው፡፡ ሱስ ወደመሆን ያድጋል ያን ጊዜ መላቀቅ ይከብዳል መንፈሳዊነትን ይጋፋል፤ ለጸሎት ለመዝሙርና ለምስጋና፣ ለመንፈሳዊ ነገር ያለን ፍቅርና ትጋት እንድበርድ ያደርጋል፡፡ ከዚያም የረከሱ የአጋንንት ማደርያ ያደርጋል፡፡ (1ሳሙ. 16፡23) ንጉሡ ሳዖል ላይ ያደረው አጋንንት በደዊት በገና ይርቅ ነበር፡፡
የዘፈን አድማጭ የዘፈን ተባባሪ ነው፡፡ዘፋኙ ዘፈንን ከውስጡ በአንደበቱ አማካኝነት አውጥቶ ለሌሎች ያጋራል፡፡ አድማጩ ደግሞ በጆሮው ይጋራል፡፡ እንደውም የአድማጩ ይብሳል፡፡ ስለዚህ ዘፈን ባለመስማት ከፈለግን ልባችንን ለዘፈን መስጠት አያስፈለግም፡፡ መስማት እና ማዳመጥ ይለያያልና፡፡ በዘመናት ዘፈን ጎጂ እንጂ ጥቅሙ ታይቶ አያውቅም ስለዚህ እንዝፈን አንስማ፡፡ (ዘፍ. 4፡21፣ መሳ. 16፡23-31፣ ዘጸ. 17፡31)
የመናፍቃን መዝሙር
ዘፋኝነት እና ዘፈን መስማት ለመንፍቃን መዝሙር ሊያጋልጥ ይችላል፡፡ ምክንያቱም የመናፍቃን መዝሙር ከሚያስጨፍር ዘፈን አይለይምና፡፡ዘፈን መስማት ኃጢአት ነው የመናፍቃንን መዝሙር መስማት ግን ዓመፅና ክህደት ነው፡፡ ለዚህ እኮ ነው ብዙ ዘፋኞች ወደ መናፍቃን የሚሄዱት ዋና ስራቸው ግጥም መቀየር ብቻ ስለሆነ ነው፡፡ሁለቱም የአጋንንት ስለሆኑ ማለት ነው፡፡ የክርስቶስ ስም ስለተጠራበት አትመን ክርስቶስ አይደለም፡፡ በክርስቶስ ስም የመጣ የሠይጣን ትምህርት እና ተቋም ማኅበር ነው፡፡ ብዙ ዕውቀት ለማግኘት እነዚህን አንብባቸው (1ቆሮ. 10፡18፣ ኤፌ. 4፡5፣ 2ቆሮ. 11፡13፣ ዘጸ. 23፡13፣ 2ቆሮ. 11፡14-15)፡፡
ዘፋኝነት የአደባባይ ኃጢአት ነው ቤተ ክርስቲያንም ታወግዛለች፡፡ የተጠመቀ ሁሉ ከዘፈን የተለየ መሆን አለበት ክርስቲያን ሆኖ ዘፋኝ የለምና፡፡ ዛሬም ብዙዎች በዚህ ሕይወት ሲኖሩ እንመለከታለን ትክክል ግን አይደለም፡፡ ዘፋኝ እና ዘማሪ መሆን አይቻልም፣ ዘፋኝ እና ክርስቲያን መሆን አይቻልም፡፡ በሕዝብ ፊት ዘፋኝነትን ትተናል ብለው ከተመለሱ ብቻ ቤተ ክርስቲያን ትቀበላቸዋለች፤ ማስተማሯን ግን አታቋርጥም፡፡ ካልሰመዋት ግን እግዚአብሔርን ትተው የዘፈን አባት የሆነውን ሰይጣንን ሰምተዋልና ፍርድ ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቀበላሉ፡፡ ገላ. 6፡7፣ 1ሳሙ. 15፡22፣ ሮሜ. 2፡3

ሕይወተ ወራዙት ክፍል 15/17- በአማርኛ



ክፍል አስራ አምስት
ምዕራፍ ስምንት
ወጣት እና የሚያሠክር መጠጥ መጠጣት
... መጽሐፍ ቅዱስ መስከርን እና ለብዙ የወይን ጠጅ መጎምጀትን እንጂ በልክ መጠጣትን አይቃወምም፡፡ ይህም ይታወቅ ዘንድ ጌታችን በቃና ገሊላ በእናቱ አማላጅነት ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ የለወጠው፡፡ክርስቶስ ለውጦ የሰጣቸው የወይን ጠጅ አልኮልነት የሌለውና የማያሳክር  ሆኖ አይደለም ነገር ግን ልካቸውን አውቀው መጠጣት የሰዎቹ ድርሻ ነው፡፡ ዛሬም ቢሆን ወጣቶች መጠጥ ሲጠጡ አእምሮኣቸው እስኪስት ድረስ መጠጣት ኃጢአት ነው፡፡ ምክንያቱም መስከር ያስቀጣልና፡፡በአግባብ ከተጠጣ መልካም መሆኑን ሲገልጽ ቅዱስ ጳውሎስም የመንፈስ ልጁ ጢሞቴዎስ ሲጽፍ ‹‹ስለ ሆዲህ ስለ ብሽታህ ብዛት ጥቂት የወይን ጠጅ ጠጣ፡፡›› (1ጢሞ. 5፡23) በሌላ መልኩም ወይን በብሉይ ኪዳንም በሐዲስ ኪዳንም ይቀርብ ነበር፡፡ ማቴ. 26፡17-29፣ ሉቃ. 10፡34፣ ጦቢ. 4፡15፣ ሲራክ. 34፡24-26፣ ቲቶ. 2፡3፣ 1ጢሞ. 3፡8፡፡ እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ካነበቡ ስለ መጠጥ ብዙ ግንዛቤ ያገኛሉ፡፡ ለማንኛውም ግን ሁሉም ነገር በግባብ ካልሆነ ጉዳቱ የከፋ ነው፤ መጠጥም እንዲሁ፡፡
የአልኮል መጠጥ የሚያስከትለው ጉዳት
መጠጥ ከመጠን በላይ ከሆነ ያሰክራል፡፡ የሚገርመው ደግሞ ሰው ከመጠን በላይ መጠጣቱን ና መስከሩን እንኳን ላይገነዘበው ይችላል፡፡ የስካርን ጉዳት ሲገልጽ ‹‹ዋይታ ለማን ነው? ኀዘን ለማን ነው? ጠብ ለማን ነው? ጩኸት ለማን ነው? ያለ ምክንያት መቍሰል ለማን ነው? የዓይን ቅላት ለማን ነው? የወይን ጠጅ በመጠጣት ለሚዘገዩ አይደለምን? የተደባለቀ የወይንን ጠጅ ይፈትኑ ዘንድ ለሚከተሉ አይደለምን? ወደ ወይን ጠጅ አትመልከት በቀላ ጊዜ፥ መልኩም በብርሌ ባንጸባረቀ ጊዜ፥ እየጣፈጠም በገባ ጊዜ። በኋላ እንደ እባብ ይነድፋል፥ እንደ እፉኝትም መርዙን ያፈስሳል።ዓይኖችህ ጋለሞታዎችን ያያሉ፥ ልብህም ጠማማ ነገርን ይናገራል።›› (ምሳ. 23፡29-33)
ስካር ማስተዋልን ያሳጣል፤ የራስን ተድላ እንጂ የሌላን አያሳስብም፡፡ ሰካራም ስለማያስተውል የተመከረውን በሙሉ አይሰማም ይረሳል፡፡ ሰው ከሰከረ ሕዋሳቱ እንደማይቀናጁለት ሁሉ አእምሮውም በትክክል አያስብም፡፡ አዝወትሮ የሚሰክር ከሆነ ደግሞ የአእምሮ ስራ ይዛባል፡፡ ለዚህ ነው ነብዩ ሆሴዕ ‹‹ግልሙትናና የወይን ጠጅ ስካርም አእምሮን ያጠፋል›› (4፡11) ያለው፡፡ እንዲሁም ጠቢቡ ሶሎሞን በምሳሌው ‹‹የወይን ጠጅ ፌዘኛ ያደርጋል፥ ብርቱ መጠጥም ጠበኛ ያደርጋል፤ በዚህም የሳተ ሁሉ ጠቢብ አይደለም›› (ምሳ. 20፡1) ሉቃ. 21፡34፡፡
ስካር ወደ ዝሙትና ወደ ጉልምትና ነው የሚያመራው፡፡ ይህም ጠቢቡ ሶሎሞን እንዲህ ይላል ‹‹ወደ ወይን ጠጅ አትመልከት በቀላ ጊዜ፥ መልኩም በብርሌ ባንጸባረቀ ጊዜ፥ እየጣፈጠም በገባ ጊዜ። በኋላ እንደ እባብ ይነድፋል፥ እንደ እፉኝትም መርዙን ያፈስሳል። ዓይኖችህ ጋለሞታዎችን ያያሉ፥ ልብህም ጠማማ ነገርን ይናገራል›› (ምሳ. 23፡31-33)፡፡ አንድ ነገር ልንገራችሁ በየመጠጥ ቤቱ የሚያስተንግዱ እህቶች መስፈርታቸው ወንዶችን በዝሙት መሳብ የምትችል መሆን አለባት፡፡ ሎጥ ላይ የደረሰውን ማስታወስ ግድ ይላል፡፡ በኃጢአት ምክንያት ሰዶም እና ጋሞራ ሲጠፉ ሚስቱም፣ ልጆቹን ሊያገቡ የሚችሉ ወንዶችም ጠፉ፡፡ ነገር ግን ልጆቹ በወይን ጠጅ አስክረውት ከእርሱ ጋር ተኝተዋል፡፡
ስካር የስጋ ስራ እንጂ የመንፈስ አይደለም፡፡ (ገላ. 5፡19፣ ሮሜ. 13፡13) ንስሐ ካልገቡ የስካር መዘዙ በምድር ብቻ የሚቀር አይደለም ‹‹ሰካራሞች የእግዚአብሔርን መንግስት አይወርሱም›› (1ቆሮ. 6፡10)፡፡ እንዲሁም ኢሳ. 28፡1-8፣ ምሳ. 23፡29፣ ኢዮ. 1፡5፡፡ሌሎችንም በዚህ መልኩ እናስብ የጤና፣ ሱስ፣የሰላም፣ የወጭ...፡፡ሌላውን ከሕይወተ ወራዙተ ክፍል 2 ያንብቡ፡፡

ሕይወተ ወራዙት ክፍል 14/17- በአማርኛ



ክፍል አስራ አራት
.... የቀጠለ....ስለ መዝናናት እና መደሰት
ሲኒማና ቴሌቪዥን
ተንቀሳቃሽ ስዕል ፊልም ይባላል፡፡ በሲኒማ የምናያቸው ነገሮች ተዋሕደውን የኛ አንድ አካል ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ፊልም ላይ ያየኸውን ለጊዜው ልትጠላው ትችላለህ፡፡ ነገር ግን አንድ ቀን በቅጽበት ማሰብ ትጀምራለህ፡፡ ሰይጣን ደግሞ ልዩ ልዩ የኃጢአት ሥራዎችን እንድትመለከት በር ይከፍታል፡፡
ወደፊት በምዕራባውያን የሚሠሩ ፊልሞች የሀገራችንን የማይውጥበት ምክንያት የለም፤ አሁንም እያየን ስለሆነ፡፡ ብዙ ፊልሞች ትዕቢትን፣ የዘር ልዩነትን፣ አድልዎን፣ ጭካኔንና ግፍን፣ ቅንጦትን፣ ግለኝነትን፣ የራስ ጥቅምን ማስቀደምን፣ የሥልጣን ሽሚያንና ስግብግብነትን፣ ምንዝርን፣ ዝሙትን፣ ግብረ ሰዶምን፣ ዓመፅን፣ ስርቆትን፣ ቂምንና የሕዝብ መጨፍጨፍን አጉልተው የሚያሳዩ ናቸው፡፡
ፊልም የሰው ልጆችን ሊጎዳ የሚችለው በብዙ አቅጣጫ ነው
(ሀ) መጥፎ ድርጊቶችን የሚያንጸባርቁ ፊልሞችን ደጋግሞ ማየት ውጤቱ ያው ነው፡፡ መተሻሸት፣መተቃቀፍ፣ ብዙ ተራክቦን የሚያሳይ ካየህ ለፍትወት መነሳሳትህ አይቀሬ ነው፡፡ እግዚአብሔርን በደልክ ማለት ነው፡፡
(ለ) በፊልሙ ላይ ከሚታዩት ዓይነት ሰዎች ጋር እንደዋለ ያህል ሊቆጠር ይችላል፡፡ መዝ. 17፡26 ‹‹ከንጹሕ ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ ከጠማማ ጋር ጠማማ ሆነህ ትገኛለህ፡፡››
(ሐ) ምንም እንኳን በተግባር ባትፈጽመውም ክፉ ነገርን በደስተኛ ልብ መቀበል በራሱ መርከስ ነው፡፡ በሥጋ የሚፈጸመው በልቡና ወጥቶ ወርዶ የተወሰነ ሐሳብ ነው፡፡
(መ) ዝሙት የሞላባቸውን ፊልሞች መመልከትህ ወደ ክፉ ኃጢአት ይወስድሃል፡፡ አጠገብህ ሰው ስለሌለ የዝሙት ፊልሞችን ታይህ ይሆናል፡፡ ነገር ግን የማታየው እግዚአብሔር ካንተ ጋር መሆኑን አትርሳ፤ ቅዱሳንም በዙሪያህ ናቸውና ተው ይቅርብህ፡፡
(ሠ) ፊልምን አዘወትሮ መመልከት ሱስ የመሆን ባሕርይ አለው፡፡ 1ቆሮ. 6፡12 ‹‹ሁሉ ተፈቅዶልኛል አንድስ እንኳን በእኔ ላይ አይሰለጥንብኝም›› ጊዜን ማጥፋት፣ ነገሮችን ችላ ማለት ይከተላሉ፡፡
(ረ) በፊልም ያዩትን በትዳራቸው በመተግበር ትዳራቸውን አደጋ ላይ የሚጥሉ ሰዎች አሉ፡፡
(ሰ) ፊልም አዘወትሮ መመልከት እንደ ፊልሙ ተዋናይ የመኖር ምኞትን በማሳደር ተግቶ በመሥራት የማግኘት ወኔን ይሰልባል፡፡ ወጣቶች በሕልም ዓለም እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል፡፡
(ሸ) ፊልም ወጣቱ ሁሉን ነገር ያለ ረድኤተ እግዚአብሔር ለማግኘት የሚያስቡ ትዕቢተኞች ያደርጋቸዋል፡፡
(ቀ) ፊልም ዘወትር የሚመለከት ወጣት ነጻ ተመልካች መሆን አይችልም፡፡ እርሱ ራሱ በአንድ አቅጣጫ በፊልሙ ውስጥ ይተውናል፡፡
(በ) መልካም ነው ከተባለው ፊልም እንኳን ባላሰብከው መንገድ አንድ መልካም ባሕርይህን ታጣለህ፡፡ ሌብነትን፣ ዝሙትን፣ ጉልበተኛነትን፣ ውሸትንና የመሳሰሉትን ሳታወድስ አትቀርም፡፡መዝ. 9፡23
ምክር፡- እኛ ክርስቲያኖች ዓለማውያን ፊልም የሚሠሩት ገንዘብ ለማግኘት እና የሠይጣንን አሰራር ማሰረጨት ስለሆነ ልንርቀው ያስፈልጋል፡፡ ከዘፈን ይበልጥ የሰውን ሕይወት ወደ ክፉ ጎዳና ሊወስድ የሚችል እንደሆነ የሚካድ አይደለም፡፡ ብዙ ለማግኘት ብለው ፊልም የሚያከራዩ ክርስቲያኖችም አሉ ግን ይህ ስራቸው ከመንፈሳዊ ሕይወታቸው ጋር አይሄድም፡፡ ስለዚህ ከወዲሁ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ከፊልም ሱስ ነጻ ለመሆን መጀመሪያ ከፊልም ጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያዘነብል ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ የቀረውን ደግሞ ከ‹‹ሕይወተ ወራዙት ክፍል 2 አንብብ፣ ንስሐ አባትህን አማክራቸው››