እስኪ
ከሁሉ አስቀድመን በዮሐንስ ራዕይ ላያ የሰፈረውን ምእራፍ 13 ከቁጥር አንድ እስከ ዘጠኝ ያለውን እናንብብ እርሶ ሙሉውን
ምዕራፉን ያንብቡ፣ ዘመኑ ክፉ ነውና አውሬው በረቀቀ መልኩ ስልቱን ቀይሮ ትውልዱን ከክርስቶስ ለይቶ ለራሱ ለማድረግ እየሰራ
ስለሆነ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ የተከተልነውን፣ የወደድነውን፣ ልዩ ቦታ የሰጠናቸውን ሰዎችም ይሁኑ ድርጅቶች ወይም አካላት በምን
መንፈስ እንደተከተልናቸው፣ እንደወደድናቸው መመርመር ያስፈልጋል፡፡ መንፈሱ በሁሉም ቦታ ይሰራል፣ የሃይማኖት ቦታዎችም ይሁኑ
በፖለቲካ ስፍራዎች ወይም በሌሎች ቦታዎች ይሰራል፣ የሱ ዓላማ ቦታ መምረጥ ሳይሆን ሰውን ጠምዶ የራሱ ማድረግ ስለሆነ
በማስተዋል እንጓዝ እላለሁ፡፡ መከተል የሚመጣው ከአባልነት ሲያልፍ ነው፡፡ ሕዝቡ ያ የሚከተሉት ሰው (አካል) ጓደኛ/አባል
ለመሆን ከሚፈለገው ቁጥር በላይ ሲሆን ስርዓቱ መከተልን ብቻ ይፈቅድላቸዋል፡፡ ይህን በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ እንደመለከታለን፡፡
መከተል መነሻው አንድ ሰው ወይም ድርጅት (በአንድ ሰው እንደሚቆጣጠር እንዳንረሳ) ላለው ጥሩ ነገር ለማግኘት ሲባል
የምናደርገው ነው፡፡ መጨረሻው ግን መጪውን አውሬ ለመከተል እያደረግን ያለነው ልምምድ ነው፡፡
ዛሬም ሰዎች የዲያብሎስን ሀሳብ ስለሚፈጽሙለት አንዳንዶች በቀጥታ ሌሎች ደግሞ በተዘዋዋሪ አባሉ ወይም ጓደኛው ሆነውታል
የአባልነት ወይም የጓደኝነት ቁጥርም ከመጠን በላይ ስለሆነ ካሁን በኋላ ያለው አማራጭ መከተል ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰይጣን ከጥንተ
ጀምሮ ሕዝቡን በብዙ የሠይጣን መንግሥት አሰራር (መዋቅር) ውስጥ ገብተው ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን ‹‹ከኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁንልህ››
ይላል የእግዚአብሐር ሕግ፡፡
ከጊዜያዊ ሰውን መከተል ጋር ተያይዞ፤ በፖለቲካ፣ በሃይማኖት፣ በሙዚቃ፣በሌላም…
የአውሬውን ምስል እንደሚጠቀሙ ባሁኑ ጊዜም የፖለቲከኛውን፣ የዘፋኙንም፣ የስፖርተኛውን…. ፎቶ መጠቀም ከአውሬው ዘመን
ጋር ያመሳስላል፤ የሚገርመው ደግሞ ፎቶዎቻው የምንጠቀማቸው ሰዎች ከእግዚአብሔር ይልቅ ወደ ሰይጣን/ወደ ዓለም የቀረቡ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡
ታዋቂ ብለን የቆጠርናቸውስ በማን ዘንድ ነው? በዓለም ዘንድ ወይስ በቤተክርስቲያን ዘንድ? በሠይጣን ዘንድ ወይስ በእግዚአብሔር
ዘንድ? መጪው አውሬውም ሕዝቡ እግዚአብሔርን ትቶ እሱን እንዲከተል ያደርጋል፡፡ ዛሬ የያዝነው ፎቶ ምንም እንኳን አፍ አውጥቶ ባይናገርም
ከአእምሮ አልፎ ስሜታችንን ገስቶ መንፈሳችንን እንደተቆጣጠረ መዘንጋት የለብንም፡፡ በአውሬው ዘመንም ልክ እንደዛሬው ሰዎች የአውሬውን
ፎቶ ይዘው በኪሳቸው፣ በቲሸርታቸው፣ በጃኬታቸው፣ በቤታቸው፣ በመኪናቸው እየለጠፉ ደጋፊ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ በቤታችን ካስቀመጥነው
የቅዱሳን ስዕል እኩል ከተቀመጠ፣ የፌዝ ቡክ መለያ ስዕል የነበረውን የቅዱሳን ሥዕል ወይም የረሳችን ፎቶ ቀይረን በተከተልነው ሰው
ወይም በአውሬው መተካት ስንጀምር አውሬውን መቀበላችን፣ በአእምሮአችን መሳላችንን ያሳያል፡፡ እያደረግን ያለነው ግን መጀመሪያውም
ሠይጣን የነበረውን፣ ዛሬ ደግሞ መልኩን ቀይሮ ሌላ መስሎ የመጣ መሆኑን እንኳን እንዳንመረምር ጊዜ ሳይሰጠን በአጭር ጊዜ ውስጥ
በሚያደርጋቸው ተአምራት እንድንከተለው እና እንድንደግፈው በማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃም ተከታዮቹን በመጠቀም የደጋፊነት ፍርማ
የማሰባሰብ ስራ በማሰራት ለራሱ ያስገዛል ማለት ነው፡፡ ይህንን ማወቅ የሚቻለው በእውቀት ብቻ አይደለም፣ ፖለቲካ መተንተን ስለቻሉበት
አይደለም መለየት የሚቻለው፣ የሃይማኖት እውቀት ስላለን አይደለም ይልቁን የእግዚአብሔር ፈቃድ ከጠየቅን ብቻ ነው፡፡ ይህ ማለት
እየሆነ ያለው በአእምሮአችን ልክ ስንመዝነው ትክክል መስሎ የታየን፣ አስደሳች ነው ብለን የተቀበልነው ነገር እግዚአብሔርን አስደስቶታል
ወይ? የሚለውን ማረጋገጥ ከቻልን ትክክል ነው፡፡ ሠይጣን ደግሞ ከመጀመሪያው እና ከሁለተኛው የማወቂያ መንገድ እንዳናልፍ ነገሮች
በፍጥነት በቀናት እና በሳምንታት ቢበዛ በወራት በመስራት ከእግዚአብሔር የሆነ አስመስሎ ያቀርባል፡፡ በዚህ መሀል አድስ ነገር ሳይኖር
የነበረውን በመተግበር አንድ ሰው ሳይቀር የተለየ ነገር የተሰራ በማስመሰል ሕዝቡ የአግዚአብሔርን ፈቃድ ሳይለይ እንዲከተለው ያደርጋል፡፡
የሚገርመው ግን ሕዝብ ሁሉ ለአውሬው ከሰገደ በኋላ ትክክለኛ እግዚአብሔር ሲገለጥ ሕዝቡ ሁሉ ለአውሬው ቃል ገብቶለት ወይም ፈርሞለት
ስለ ነበር ወይም ከሱ ጋር ለመሆን ወስኖ ስለ ነበር ለእግዚአብሔር መሆን አይችልም፤ የእግዚአብሔር የሆኑ ነገሮችን በሙሉ መጠቀም
አይችልም፡፡
ሰውን መከተል ምን አይነት ተጽዕኖ አለው? - ባርነት፣ መገዛት፣ በሰው ሀሳብ መመራት፣ የራስን አእምሮ እና ልብ አለመጠቀም፣
የተከተሉት የሆነውን ሁሉ መሆን፤ ከወደቀ መውደቅ፣ ከተሳሳተ መሳሳት፣ ካመነ ማመን፣ ከተቀበለ መቀበል፣ ከተቃወመ መቃወም፣ ከግል
እምነት ወደ ቡድን እምነት ማድላት፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ብቻ እግዚአብሔር የሰጠውን አእምሮ፣ ስሜት እና ልብ አለመጠቀምን ያመጣና ከእግዚአብሔር
ዘንድ የሚለይ ይሆናል፣ ሐዋርያት ህዝቡ ክርስቶስን እንዲከተሉ አደረጉ እንጂ እነሱን እንዲከተሉ አላደረጉም፣ (መጥምቀ መለኮት ቅዱስ
ዮሐንስ ራሱ ‹‹የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የአግዚአብሔር በግ እነሆ ነበር ያለው››)፣ ፍቅር ልብ ላይ ነው ማረፍያው፤ ልብ
ላይ የሚያድረው ደግሞ እግዚአብሔር ነው- ታዲያ እኛ ልባችንን ለምድራዊያን ፖለቲከኞች እና ዘፋኞች ካሳደርን እግዚአብሔር አልተካደም
ወይ?፣ ቅዱሳን አልተካዱም ወይ? ለመሆኑ እያደረግን ያለነው ነገር ትክክል ነው (አእምሮአችንን)፣ ያስደስታል (ስሜታችንን)፣ የእግዚአብሔር
ፈቃድ ነው፤ እግዚአብሔር ወዶታል (ልባችንን) በዚህ ሁሉ አረጋግጠን ነው ወይ እንዲሁ ሆ ብለን የተነሳነው? ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ
የሆነ ሁሉ እድሜው አጭር ነው ለሕዝብ ግን ታላቅ ሐዘን እና የልብ ስብራት ነው፡፡ ክርስቲያኖች አውሬው በምድር ላይ ተገልጦ ሕዝብ
ሁሉ ቢከተለው እንደማይከተል ሁሉ አሁን ባለው ሁኔታ ግን አንድም ሰው የሚቀር አይመስልም፡፡
አውሬው
የስምንት ሺህ ዓመት ልምድ ያለው በመሆኑ የተመረጡትን እንኳን እስከ ማሳት ይደርሳል፤ በምትሐቱ፣ በጥበቡ፣ በእውቀቱ እና በድርጊቱ፡፡የአግዚአብሔር
እያስመሰለ፣ ከእግዚአብሔር የተቀባ በማስመሰል፣ ከእግዚአብሔር የሆነ በማስመሰል ሕዝብ እንዲከተለው በማድረግ ባልተከተለው ላይ ሕዝብ
እንዲነሳበት ያደርጋል፡፡ ሠይጣን እና ተከታዮቹ በጭካኔ መንፈሱ ካልተሳካለት ትሕትና ወደሚመስል የተመረጡት የተበሉት
ጳጳሳት፣ ካህናት፣ መነኮሳትን፣ ዲያቆናትን፣ መምህራነ ወንጌልን፣ ማኅበራትን፣ ድርጅቶችን፣ በተለያየ መድረክ ተጽዕኖ ፈጣሪ ተብለው
የታወቁትን ሲያስት ተከታዮቹ በሙሉ ይወድቃሉ፡፡ ይህ ሰይጣን ከምን ጊዜም በላይ ሕዝብን ለመጣል የሚጠቀምበት ሴራ ነው፡፡ ምንም
እንኳን ጊዜው ቢደርስም፣ የአግዚአብሔር ፈቃድ ቢሆንም ጌታችንን አይሁድ እንዲይዙት ያደረገው በሱ ሞት መንጋው እንዲበተን ነበር፤
እውነትም በክርስቶስ መያዝ ከአንዱ በቀር ሌሎች ፍርሐት እና ድንጋጤ ይዟቸው ነበር፡፡ ሌሎችማ እነ ሉቃስ እና ቀለዮጳ ተስፋ ቆርጠው
አምነው የነበሩትን ትተው ብርቱ ነብይ እንደ ነበረ አድርገው እያወሩ ወደ ኤማውስ መንደር ይሄዱ ነበር፡፡ አሁንም እየሆነ ያለው
ከመንፈሳዊ ሊቃውንት እስከ ምእመን ድረስ ከእግዚአብሔር ይልቅ ሰውን የሚከተል፣ ሰውን የሚደግፍ፣ የዚህች ሀገር መፍትሔዋ ከቤተክህነት
መሆኑ ቀርቶ ከፖለቲካ ዓለም ብቻ እንደሆነ በማሰብ ቤተክህነት ራሷ ፖለቲካን ወይም ምድራዊውን መንግሥት ብቸኛ መፍትሔ አድርጋ እንድትወስድ
ማድረግ ቤተክርስቲያን ከጥንት ጀምሮ ይሰራ እንደነበር አሁንም ለአውሬው ለማስረከብ እየተሰራ ያለ ሴራ ነው፡፡ ምንም እንኳን እግዚአብሔር
ስለተመረጡት አባቶች ባያሳካውም ቤተክርስቲያን እውቅና ሰጪ ሳትሆን እውቅና ጠያቂ ለመሆን እንድትሄድ የሚያደርግ አካሄድ እየተስተዋለ
ነው፤ ይህ ደግሞ ለመጪው አውሬ ምቹ ይሆንለታል፡፡
ሰኔ 16/2010
No comments:
Post a Comment