በእንተ ርእስየ

Thursday, October 11, 2018

ሆድ አደሮች በቤተክርስቲያን


እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር ሁለት ጠባይ እንዲኖረው አድርጎ ነው ይህም እንሰሳዊ እና መልአካዊ፡፡ እንደ እንሰሳ ይበላል፣ ይጠጣል፣ ይተኛል፣ ይሞታል ወዘተ፡፡ እንደ መልአክ ደግሞ ሕያው ነው፣ ያመሰግናል፣ ይነቃል፣ ባአጠቃላይ የነፍስን ፈቃድ እየተከተለ እግዚአብሔርን እንዴት እንደሚያስደስት ያስባል ያደርጋልም፡፡ ነገር ግን የሰው ልጅ አብዛኛውን ጊዜ ስለ ስጋው ሲያስብ ይኖራል፣ ማለትም ስለ ሆዱ ማለት ነው፡፡ በዓለም ላይ ብዙዎቻችን የምንዳክረው ስለ ሆዳችን ነው፡፡ ነገር ግን ከክርስቶስ ልበልጥብን አይገባም ምክንያቱም የዕለት ምግብ የሚሰጥ ራሱ አምላካችን ነውና፡፡
ባሁኑ ጊዜ ግን በስመ ክርስቶስ ወይም በስመ ማኅበር ለገዛ ሆዳቸው የሚሮጡ፣ የሚኖሩ፣የሚማሩ፣ የሚያገለግሉ፣ አንድ ክርስቲያን ያደርጋል ተብሎ የሚታሰበውን በሙሉ የሚያደርጉ እየመሰሉ ለገዛ ሆዳቸው የሚመላለሱ እየጨመሩ መጥተዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለጊዜው የተናገረው ስለ ሐሰተኞች ነቢያት ማለት ስለ መናፍቃን ነበር ምክንያቱም ጌታችን በስሜ ይመጣሉ እንዳለው ሁሉ ዓላማቸው ስለ ክርስቶስ ሳይሆን ለገዛ ሆዳቸው ነው እንጂ መስቀል ላይ የተከፈለውን የክርስቶስን ዋጋ የሚሰብኩ አይደለም፤ ዓላማቸው ሆዳቸውን መሙላት ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ራሳቸውን ለለዩ ለመናፍቃን ነው፡፡ እኔ መጻፍ የፈለኩት ግን ከውስጥ ሆነው ለክርስቶስ ወንጌል ጠላት የሆነውን፣ የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት እየጣሰ ያለውን የውስጥ ሆድ አደርን ነው፡፡ ሆድ አደር! ስለ ክርስቶስ የሚሰብክ ይመስላል ነገር ግን ዓላማቸው ገንዘብ ማግኘት ነው፡፡ ገና ስጀመር የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት የተማሩትም ለገንዘብ፣ ወይም በልማድ ይሆናል፡፡ በእንዲህ ዓይነት የተማረ ሰው ነው የክርስቶስን ወንጌል ለዓለም የሚያዳርሰው! በፍጹም አይታሰብም እንዲህ ዓይነት ሰው ወንጌሉ ወይም የሐዋርያዊ ስራ በሚፈልገው ልክ ሳይሆን በራሱ ልክ ነው የሚያስበው፣ የሚያደርገው፣ የሚናገረውም፡፡ ሕዝቡ ባለው ሳይሆን እሱ ባለው ይራመዳል፣ በሕዝቡ ማንነት ሳይሆን በራሱ ማንነት ይለካል፡፡ አውደ ምህረት ላይ ለመውጣት ሕዝቡን ማወቅ ጉዳዩ አይደለም ሰሙ አልሰሙ፣ ተረዱ አልተረዱ ጉዳዩ አይደለም፡፡ የሕዝቡን ባህል፣ ቋንቋ፣ መልክእምድር፣ ዳራ ማወቅ አይፈልግም ግን የቤተክርስቲያናችን ሐዋርያዊ ስራ እንዲህ አይልም፤ ሕዝቡን ሳያውቁ ማስተማር የለማ፡፡
የክርስቶስ ወንጌል ሕዝቡ በሚሰማ ቋንቋ፣ በሚረዳው ባህል፣ ሕዝቡ ባለው የሃይማኖት ዳራ፣ የእውቀት ደረጃ፣ ሥነ ልቡና እና ወዘተ መሰረት ያደረገው መሆን ነበረበት፡፡ ጌታችን ባረገ በአስረኛው ቀን መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት በሰደደ ጊዜ የክርስቶስን ወንጌል ለዓለም ለማዳረስ መንፈሳዊ መሳሪያ ይሆናቸው ዘንድ 72 ቋንቋ ገለጠላቸው፡፡ በሐዋርያት ስራ ታሪክ የሕዝብን ቋንቋ ባለማወቅ ያጋጠማቸው ችግር ሰምተን አናውቅም ምክንያቱም ሆድ አዳሮች አልነበሩም፣ የክርስቶስን ወንጌል ለፍጥረት ሁሉ ለማዳረስ ነበር ዓላማቸው፡፡ ይህንን በታላቅ ትጋት ፈጸሙ ግን ሆድ አደሮች የሕዝብን ነገር ማወቅ ዓላማቸውም አይደለም፡፡ ሕዝቡን ሳያውቁ ለወንጌል ይሰማራሉ፤ ቋንቋውን ሳያውቁ እናስተምርህ ይሉታል የሕዝቡን ትቶ በራሱ ቋንቋ ያስተምራል ግን ሕዝቡ አይሰማም፡፡ ምን ያድርግ ሆዱ አልጎደለ፣ ደሞዙ አልተቋረጠ፤ ሊቋረጥ እንደሚችል እንኳን አለማሰቡ ገርሞኛል፡፡ ግን ሕዝቡ ከሃይማኖቱ እየኮበለለ ነው በሆድ አደሮች፡፡በተለይ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በጠረፋማው የሀገሪቱ ክፍል፡፡ ሆድ አደሮች ቤተክርስቲያን ውስጥ ለተስፋፋው ኃይለኛ ሙስና፣ዘረኝነት፣ተሀድሶ ና ሌሎች ግግሮች ምክንያቶች ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ልማት እየተባለ የሚወራውም ለሙስና መደበቅያ እንጂ መንፈሳዊ ሊማት አይደለም፤ ምክንያቱም በቤተክርስቲያን ሊማት ማለት ሕዝብን በወንጌል ማለምለም ነው፡፡
የሆድ አደራች ሌላው መገለጫው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለ ሀሳባቸው ምድራዊ ነው፡፡ የተሰጣቸው ፀጋ፣ ኃላፊነት፣ ክብር ሰማያዊ ቢሆንም የነሱ የዘወትር ጭንቀት ምድራዊ ነው፡፡ በስመ ወንጌል ወደማያውቁት ሕዝብ ከሄዱ በኋላ ያንን ሕዝብ የሚያደክሙበትን፣ የሚበትኑበትን፣ ከሞላላቸውም ማጥፋት የዘወትር ተግባራቸው ነው፡፡ ተተኪ ማፍራት ካለው ህብረተሰብ መሆኑ ቀርቶ በምድራዊ አጠራር ከዘራቸው ብቻ ያፈራሉ ሌላው በመካከላቸው እንዲገባ አይፈልጉም አይ መሸወድ ዋስትና የሌለው ሕይወት፣ ቤተክርስቲያንን የሚሰረስር የውስጥ ወንበዴ፣ ያልተነቃበት የውስጥ መናፍቅ፣ የመስቀል እና የወንጌል ጠላት፡፡ የአከባቢው ሕዝብ አገልግሎት ሲጠይቃቸው ዘረኞች ሆነው ዘረኞች እያሉ የሚደስኩሩ፡፡ ይህ እቅዳቸው በአካባቢው ያለው ሕዝብ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ባዳ እንዲሆን እና ሙሉ በሙሉ ትቶላቸው ሃይማኖቱን እንዲክድ ማድረግ ነው፤ እያደረጉም ነው በተለይ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ክልሎች በመረጃ የተደገፈ ነው፡፡ የሆድ አደሮች ዓላማ ወንጌልን ማስፋፋት ሳይሆን ሆዳቸውን መሙላት፣ ባህላቸውን ማንጸባረቅ፣ ቋንቋቸውን ማሳደግ፡፡ ሃያ ዓመት ከሕዝቡ ጋር ኑረው የሕዝቡን ቋንቋ በመጥላት መልመድ እየቻሉ ወንጌልን ሳያስተምረው በአውደ ምህረት እየለፈለፉ ማንም ሳይሰማቸው ስንቱ ትቶላቸው ሄደ? ሆዳቸውን እየሞሉ ለክርስቶስ ወንጌል ጠላት የሆኑ ቤት ይቁጠራቸው፡፡ ነገር ግን ብያውቁ ኖሮ እና ትክክለኛ ሐዋርያ ቢሆኑ ኖሮ የሕዝቡን ቋንቋ ባወቁ ወይም ለማወቅ ጥረት ባደረጉ ነበር፡፡እዚህ አንድ አርቀው አሳቢ አባት የተናገሩትን ልንገራችሁ ‹‹ከምያሳዝነኝ ውስጥ ይህን ያህል በዚህ ክልል ኖሬ የክልሉን ቋንቋ አለመቻሌ ነው፤ መማር ያለብኝን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ተምሬያለው ግን ማስተማር አልቻልኩም ምክንያቱም ሕዝቡ እንደማይሰማ እየተነገረኝ ነው፤ ደግሞ ምድራዊ መንግሥት እንኳን ከእኛ ተሽሎ የሚያስፈልጋቸውን ስጋዊ አገልግሎት እነሱ በሚሰሙት ቋንቋ እየሰጣቸው ይገኛል፡፡›› አሉኝ ግን እሷቸው ቁጭታቸውን እና እውነታውን ነው የሚናገሩት፡፡ እውነትም  ቀዳሚዋን ቤተክርሰቲያን ከምድራዊ አሰራር ወደ ኋላ ያስቀሩ ሆድ አደሮች አይመስላችሁም?
የሆድ አደሮች መጨረሻ ምንፍቅና፣ ጥንቆላ፣ ተሀድሶ መናፍቅነት በመጨረሻም ሰይጣን አምላኪዎች መሆን ነው፡፡ ስጀመር ዘረኝነት የሰይጣን መንፈስ ነው፡፡ የእውቀታቸው መለኪያ በሸመደዱዱት ልክ እንጂ ባመኑት ልክ አይደለም፤ ያውቃሉ ግን አይምኑም፡፡ ከዚህ የተነሳ የቤተክርስቲናችን የክህነት መስፈርት በሸመደደው ልክ እንጂ ባመነ፣ በተመሰከረለት መሆኑ ቀርቷል፡፡ ዛሬ ለተበላሸው የቤተክርስቲያናችን ሥርዓት ምንጩ ማን መሰላችሁ? ሆድ አደሮች አይደሉምን? የተማሩት ትምህርት የክርስቶስን ወንጌል ለማስፋፋት ሳይሆን ለሆዳቸው ስለሆነ በጎደለባቸው ጊዜ ከውጭ መናፍቅ ጋር እየታጃለሱ ሥርዓቷን ማበላሸት፣ ዶግማዋን መለወጥ ወዘተ፣ ስለ ገንዘብ ደግሞ የቤተክርስቲያንን ቅርስ መሸጥ፣ አብዛኛው በውጭ ሀገር ያለው በሺዎች የሚቆጠር የብራና መጻሕፍት መቼም በሆድ አደሮች ካልሆነ በስተቀር በሀገሬው ሕዝብ ነው የተሸጠው እንዳትሉ፡፡
የቤተክርስቲያን ሀብት ምእመናን ናቸው፣ የገቢ ምንጯም ከእነሱ ውጭ ማንም የላትም እንደ መናፍቃን ከውጭ የሚገባላት የላትም ነገር ግን ለዘመናት ገንዘብ በማጣት ወንጌል ከማስተማር ቦዝና አታውቅም ነበር፡፡ ሐዋርያቶቿ ይህ አይበግራቸውም ነበር ነገር ግን ዛሬ በሆድ አደሮች ሐዋርያዊ ስራዋ የታገተ ይመስለኛል ይህም የሆነበት ምክንያት ሕዝብን ያማከለ ሐዋርያዊ ስራ አልተካሄደም፡፡ ሰባኪ ከአድስ አበባ ማምጣት እንጂ ሕዝብ ማነው ይምለው ጥያቄ አይጠየቅም፤ ሰባኪውም ጠሪዎቹ በነገሩት ልክ ጮኾ ይሄዳል ለውጥ ግን የለም፡፡ በተለይ ኦሮሚያ ክልል ብዙ የሕዝብ ጉባኤ ይካሄድባታል ነገር ግን ለውጥ የለም ሕዝቡ አሁንም እየጠፋ ነው፡፡ በሕዝቡ ቋንቋ ይሰጥ ሲባል ዘረኞች፣ ተሀድሶ፣ፖለቲከኝ... ወዘተ ይባላል፡፡ ለመሆኑ ዘረኛው የትኛው ነው? በሕዝቡ ቋንቋ የማታስተምር ከሆነ ዝም ብለህ እንደምትጮኽ እንዴት አይገባህም? ሆድህ ካልጎደለ አይታወቅህም አንድ ቀን እንደምጎድልህ ማወቅ ግን ነበረብህ፡፡ ይህን የሚያደርገው እኔ አይደለሁም የሐዋርያት ጌታ በሃምሰኛው ቀን የወረደ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ብልጥ እና ሐዋርያ ብትሆን ግን በሕዝቡ ቋንቋ፣ ባህል መሠረት ባስተማርክ ነበር፡፡ ዘረኛ ሆነህ ነው እንጂ ይህን ዓመት ሁሉ በሕዝብ መሀል ኖረህ ቋንቋቻውን በለምድክ ነበር፣ ባህሉን በተረዳህ ነበር አንተ ግን የመጣህበትን ቋንቋ እና ባህል ስታራግብ ኖርክ ቤተክርስቲያንን ስለማትወክል አይደንቀኝም፡፡ ግን ቅድስት ቤተክተርስቲያንን ከመናፍቃን ይበልጥ በአንተ ስለተጎዳች ዝም አልልም፡፡ ምክንያቱም የቤተክርስቲያን ጠላት አምራች አንተ ራስህ ስለሆንክ ማለት ነው፡፡
የሆድ አደሮች መገለጫው ሌላው ወንጌል ባለማስተማራቸው የሕዝብ ቁጥር እየቀነሰ ሲሄድ የሚገባው ገንዘብ እንዳይጎድልባቸው በስመ ገቢ ማመንጫ እና በስመ ልማት ሕንጻ መገንባት፣ ማስገንባት ነው፡፡ ታቦተ ሕጉ ቆሞ ወንጌል ከማስተማር የገንዘብ ልመና መርሐግብር መብዛቱ፣ ገንዘብ ለማግኘት ተብሎ ጽላቱ የሚከብርበትን ቀን እስከመቀየር መድረስ፤ ለምሳሌ መስከረም 17 የመስቀል በዓል ስለሚከበር በዕለቱ ደግሞ ጉራጌዎች ወደ ተወለዱበት ስለሚንቀሳቀሱ ከእነሱ የሚገኘው ገንዘብ እንዳይቀር ተብሎ በዚህን ቀን የሚታሰበው የቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ በዓል ወደ ጥር 17 መሸጋገሩ ከውስጤ አልወጣ ያለ ክስተት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ በአንድ አስተዳደር ስር ያሉ ተመሳሳይ መታሰቢያ ያላቸው አብያተ ክርስቲያናት ሁለቱም አንድ ጊዜ የሚነግሱ ከሆነ የሚገኘው ገንዘብ ስለሚጎድል የአንዱ ቤተክርስቲያን ጽላት እንዳይወጣ ተደርጎ የአንዱ ብቻ ሲወጣ ማየቴም አሳዝኖኛል፤ ለዚህ ነው ይህንን ጽሑፍ ለማውጣት የተገደድኩት፡፡ ባሁኑ ጊዜማ ሰለቸኝ ለስብከተ ወንጌል ማለትም የሥላሴ ሕንጻን ከማነጽ ይልቅ ድንጋይ ለመከመር የሚለመነው ገንዘብ፣ የሚሠራው ስራ ልዩ ነው፡፡ ይህ ጥቅሙ በምድራዊ መንግሥት ዘንድ ለመወደድ እንጂ በሰማያዊው ንጉስ ዘንድ እንደማያስከብር ይታወቃል፡፡ ሕዝቡ ኮብልሎ ስለሄደ፣ ወይም ስላልተማረ ምን አገባኝ በማለት ዝም ስላለ የሚጠይቃቸው የለም በራሱ አከባቢ በስመ ቤተክርስቲያንን የፈለጉትን ይሆናሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ቤተክርስቲያንን ከዓላማዋ እና ከባሕርይዋ ውጭ ስለሚያደርጋት ብያስቡበት መልካም ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ለሕዝብ ናት እንጂ ለተወሰኑ ሰዎች የስጋዊ የገቢ ምንጭ እንድትሆን አይደለም፡፡
ሆድ አደሮች የሚኖሩት ሆዳቸው ይሙላላቸው እንጂ ስለ ቤተክርስቲያን ሥርዓት አይጨንቃቸውም፡፡ በቅዳሴ ሰዓት የሙዳይ ምጽዋት ፍተሻ እንጂ በሕዝብ መሀል እየሄዱ የምእመናን ሕሊና መስረቃቸው ምናቸውም አይደለም፡፡ ይህ ዕለት ዕለት የማየውን ነው የምነግራችሁ፡፡ ይህንን የሚያደርገው ደግሞ የቤተክርስቲያኒቱ ዘበኛ ነው፤ ዘበኛው ለወንጌል እና ለጸሎት የተሰቀሉ መብራቶች ለማጥፋት፣ የቤተክርስቲያን በር ለመዝገት የሚቸኩል እንጂ የቤተክርስቲያኒቱ ዓላማ የገባው አይደለም፡፡ ከኋላው ደግሞ ሰበካ ጉባኤ አለ ዘበኛው በቅዳሴ ሰዓት እየዞረ እንዲፈትሽ የታዘዘው፡፡ ሰባካውም ቢሆን የሙዳይ ገንዘብ የሚቆጥረው በሰንበተ ክርስቲያን እሑድ አይደለም እንዴ? ኧረ እንዲህ አይደለም! ሕዝቡ የመረጣችሁ ሰንበት እንድትሽሩ ነው እንዴ? ሥርዓተ ቤተክርስቲያን እንድታፈርሱ ነው እንዴ? ወይስ ሙስናን ለመዋጋት ለግልጽነቱ ብላችሁ ይሆን በሕዝብ ፊት የሙዳይ ገንዘብ የምትዘረግፉት?... ለመሆኑ ከቅዳሴ የሚበልጥ አለ እንዴ? ቅዳሴውስ የሰበካውን አባላት አይመለከትም? የእነሱ ይቅር በዕለቱ ቅዳሴ ለማስቀደስ የቆመውን ወጣት ገንዘብ ቁጠር እያሉ ጸሎት ያሚያቋርጡ በብዙ አብያተ ክርስቲያን ማየቴ ነው፡፡ ብነገራቸው አይሰሙም ሊማት ነዋ፣ ገንዘብ ብቻ! እስኪ መጀመሪያ ሕዝብ አስተምሩ አያንገብግባችሁ፡፡ ሕዝብ ካለ የምትንገበገቡለት ገንዘብ ከእነሱ ይገኛልና፡፡ አሁን አሁንማ መርሐግብራቱ የሚዘረጉት ገንዘብ ለመሰብሰብ ብቻ የሆነ ይመስላል፡፡ በቤተክርስቲያን አውደ ምህረት የሰዎች ሙገሳ፣ የገንዘብ ልመና፣ የሳይንስ እና የፖለቲካ መልእክት ማስተላለፍ የተለመደ ሆኗል፤ ነገር ግን መሆን የነበረበት በፖለቲካ መድረክ ቤተክርስቲያን  መልእክት ማስተላለፍ ነበረባት፡፡ ምን ይደረግ በዘረኞች እና በሆድ አደሮች ነገሩ ተቀያየረ እና ቤተክርስቲያን የበታች ኃላፊው ፖለቲካ ከበላይ ሆኖ መራት፡፡
ሌላው የሆድ አደሮች ስራ የሰንበት ትምህርት ቤት አወቃቀርን በእነሱ ልክ ማድረግ ነው፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤቱ ከሕዝቡ የተውጣጣ ሲሆን ቤተክርስቲያን ሲሄድ ግን ሰንበት ትምህርት ቤቱን እንዲያስተምር በተመደበው መምህር ልክ ይወሰናል፡፡ እሱን የማይመስሉ ቦታ የላቸውም ብሰበሰቡ እንኳን ይበተናሉ በመምህሩ፡፡ ተቀባይነት ለማግኘት ግድ መምህሩ የምናገረውን ቋንቋ መናገር፣ እሱ ከሚያውቀው ባህል የወጣ መሆን አለበት፡፡ እንዲህ አይነቱ ዬት ዬት እንደሆነ መገመት አያዳግታችሁም፡፡ በዚህ አይነት አመለካከት ያላችሁ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች አንድ ቀን በእናንተ ላይ መድረሱ ስለማይቀር እስኪ ሁላችሁም ራሳችሁን ተመልከቱ፡፡ ዛሬ ዛሬማ የሰንበት ትምህርት ቤቱ አባላት ከሰበካ የተማሩትን ሥርዓተ ብልሹነት ይፋ እያወጡ ነው፡፡ በቅዳሴ ሰዓት ገንዘብ ማስገኛ ዕጣዎችን ማዞር፣ ባጠቃላይ ከዘረኝነት አንስቶ ሥርዓት አልበኝነት እየገነነ መምጣት አሳሳቢ የሆነ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ነው፡፡የቤተክርስቲያን አገልግሎት በአማርኛ ልክ የተሰራ ነው ሌላው ባእድ ነው፡፡ ግን መብቃት አለበት፡፡ ሌሎች ይቅሩ ከሀገሪቱ ክፍል የተወጣጡ ተማሪዎች የምስተናገዱባቸው በሀገራችን የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት እንኳን እንዴት ማሰብ አቃታቸው? ምክንያቱም ዘረኞች እና ሆድ አደሮች ስለሆኑ ነው፡፡ ለማስመሰል ግን በሕዝብ ቋንቋ አያስተማርን ነው የሚሉ በስተዋል፣ ላሁኑ ይለፈኝና እውነታውን ግን አላስቀርም በተለይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለውን አገልግሎት ማስመሰሉ ቀርቶ በእውነት እስከሚሰራ፤ እንዳይማይፈለግ በማስረጃ የተደገፈ ስለሆነ ራሳችንን ብንመለከት፡፡ ሃይማኖታዊ መሆኑ ቀርቶ ፖለቲካዊ እንደሆነ ከተግባሩ ተረድተናል፣ የአገልግሎት ጥያቄ ሲጠየቅ ከፖለቲካ ጋር ማላከክ፤ማያያዝ፣ዘረኛ ማለት፣ ሊሰሟመቸው ለሚችሉ ሰዎች እና አካላት ጥያቄ አቅራቢዎቹን ማቅረብ (መረጃው በእጄ ስላለ) ሌለውም ብለዋል ግን ለዚህ ለባለቤቱ ለቤተክርስቲያን አምላክ እንስጥ፡፡ ብዙ ጊዜ ደግሞ ትምህርታቸው ስለ ተሀድሶ ነው ደግሞ ለራሳቸው ሳይጣን አምላኪዎች ሆነው፡፡ ዘረኝነት ሰይጣን ማምለክ ነውና፡፡ እስኪ መጀመሪያ ቤተክርስቲያኗ ዬት እንዳለች እንወቅ፣ ልታደም የሚችለውንም ሕዝብ እንለይ (እንወቅ) ከዚያ ሁሉም ነገር ቀላል ይሆናል፡፡ የሐዋርያት አምላክ ሁሉን ነገር ማስተካከሉ አይቀርም ነገር ግን በፍቅር እና በስምምነት ይሁን፤ የተስተካከለ ለት ግን የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፡፡ በመሠረቱ ክርስቲያን ተዋደው የሚኖሩባት እንጂ ተቻችለው አይደለም፣ እንድንዋደድ እንድንደማመጥ ራሳችንን እናስተካክል፣ አመለካከታችንን እናስተካክል፡፡

ምድር ሁሉ አውሬውን ይከተላል- አሁን ካለው ጋር ሲታይ


እስኪ ከሁሉ አስቀድመን በዮሐንስ ራዕይ ላያ የሰፈረውን ምእራፍ 13 ከቁጥር አንድ እስከ ዘጠኝ ያለውን እናንብብ እርሶ ሙሉውን ምዕራፉን ያንብቡ፣ ዘመኑ ክፉ ነውና አውሬው በረቀቀ መልኩ ስልቱን ቀይሮ ትውልዱን ከክርስቶስ ለይቶ ለራሱ ለማድረግ እየሰራ ስለሆነ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ የተከተልነውን፣ የወደድነውን፣ ልዩ ቦታ የሰጠናቸውን ሰዎችም ይሁኑ ድርጅቶች ወይም አካላት በምን መንፈስ እንደተከተልናቸው፣ እንደወደድናቸው መመርመር ያስፈልጋል፡፡ መንፈሱ በሁሉም ቦታ ይሰራል፣ የሃይማኖት ቦታዎችም ይሁኑ በፖለቲካ ስፍራዎች ወይም በሌሎች ቦታዎች ይሰራል፣ የሱ ዓላማ ቦታ መምረጥ ሳይሆን ሰውን ጠምዶ የራሱ ማድረግ ስለሆነ በማስተዋል እንጓዝ እላለሁ፡፡ መከተል የሚመጣው ከአባልነት ሲያልፍ ነው፡፡ ሕዝቡ ያ የሚከተሉት ሰው (አካል) ጓደኛ/አባል ለመሆን ከሚፈለገው ቁጥር በላይ ሲሆን ስርዓቱ መከተልን ብቻ ይፈቅድላቸዋል፡፡ ይህን በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ እንደመለከታለን፡፡ መከተል መነሻው አንድ ሰው ወይም ድርጅት (በአንድ ሰው እንደሚቆጣጠር እንዳንረሳ) ላለው ጥሩ ነገር ለማግኘት ሲባል የምናደርገው ነው፡፡ መጨረሻው ግን መጪውን አውሬ ለመከተል እያደረግን ያለነው ልምምድ ነው፡፡
ዛሬም ሰዎች የዲያብሎስን ሀሳብ ስለሚፈጽሙለት አንዳንዶች በቀጥታ ሌሎች ደግሞ በተዘዋዋሪ አባሉ ወይም ጓደኛው ሆነውታል የአባልነት ወይም የጓደኝነት ቁጥርም ከመጠን በላይ ስለሆነ ካሁን በኋላ ያለው አማራጭ መከተል ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰይጣን ከጥንተ ጀምሮ ሕዝቡን በብዙ የሠይጣን መንግሥት አሰራር (መዋቅር) ውስጥ ገብተው ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን ‹‹ከኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁንልህ›› ይላል የእግዚአብሐር ሕግ፡፡
ከጊዜያዊ ሰውን መከተል ጋር ተያይዞ፤ በፖለቲካ፣ በሃይማኖት፣ በሙዚቃ፣በሌላም…
የአውሬውን ምስል እንደሚጠቀሙ ባሁኑ ጊዜም የፖለቲከኛውን፣ የዘፋኙንም፣ የስፖርተኛውን…. ፎቶ መጠቀም ከአውሬው ዘመን ጋር ያመሳስላል፤ የሚገርመው ደግሞ ፎቶዎቻው የምንጠቀማቸው ሰዎች ከእግዚአብሔር ይልቅ ወደ ሰይጣን/ወደ ዓለም የቀረቡ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ታዋቂ ብለን የቆጠርናቸውስ በማን ዘንድ ነው? በዓለም ዘንድ ወይስ በቤተክርስቲያን ዘንድ? በሠይጣን ዘንድ ወይስ በእግዚአብሔር ዘንድ? መጪው አውሬውም ሕዝቡ እግዚአብሔርን ትቶ እሱን እንዲከተል ያደርጋል፡፡ ዛሬ የያዝነው ፎቶ ምንም እንኳን አፍ አውጥቶ ባይናገርም ከአእምሮ አልፎ ስሜታችንን ገስቶ መንፈሳችንን እንደተቆጣጠረ መዘንጋት የለብንም፡፡ በአውሬው ዘመንም ልክ እንደዛሬው ሰዎች የአውሬውን ፎቶ ይዘው በኪሳቸው፣ በቲሸርታቸው፣ በጃኬታቸው፣ በቤታቸው፣ በመኪናቸው እየለጠፉ ደጋፊ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ በቤታችን ካስቀመጥነው የቅዱሳን ስዕል እኩል ከተቀመጠ፣ የፌዝ ቡክ መለያ ስዕል የነበረውን የቅዱሳን ሥዕል ወይም የረሳችን ፎቶ ቀይረን በተከተልነው ሰው ወይም በአውሬው መተካት ስንጀምር አውሬውን መቀበላችን፣ በአእምሮአችን መሳላችንን ያሳያል፡፡ እያደረግን ያለነው ግን መጀመሪያውም ሠይጣን የነበረውን፣ ዛሬ ደግሞ መልኩን ቀይሮ ሌላ መስሎ የመጣ መሆኑን እንኳን እንዳንመረምር ጊዜ ሳይሰጠን በአጭር ጊዜ ውስጥ በሚያደርጋቸው ተአምራት እንድንከተለው እና እንድንደግፈው በማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃም ተከታዮቹን በመጠቀም የደጋፊነት ፍርማ የማሰባሰብ ስራ በማሰራት ለራሱ ያስገዛል ማለት ነው፡፡ ይህንን ማወቅ የሚቻለው በእውቀት ብቻ አይደለም፣ ፖለቲካ መተንተን ስለቻሉበት አይደለም መለየት የሚቻለው፣ የሃይማኖት እውቀት ስላለን አይደለም ይልቁን የእግዚአብሔር ፈቃድ ከጠየቅን ብቻ ነው፡፡ ይህ ማለት እየሆነ ያለው በአእምሮአችን ልክ ስንመዝነው ትክክል መስሎ የታየን፣ አስደሳች ነው ብለን የተቀበልነው ነገር እግዚአብሔርን አስደስቶታል ወይ? የሚለውን ማረጋገጥ ከቻልን ትክክል ነው፡፡ ሠይጣን ደግሞ ከመጀመሪያው እና ከሁለተኛው የማወቂያ መንገድ እንዳናልፍ ነገሮች በፍጥነት በቀናት እና በሳምንታት ቢበዛ በወራት በመስራት ከእግዚአብሔር የሆነ አስመስሎ ያቀርባል፡፡ በዚህ መሀል አድስ ነገር ሳይኖር የነበረውን በመተግበር አንድ ሰው ሳይቀር የተለየ ነገር የተሰራ በማስመሰል ሕዝቡ የአግዚአብሔርን ፈቃድ ሳይለይ እንዲከተለው ያደርጋል፡፡ የሚገርመው ግን ሕዝብ ሁሉ ለአውሬው ከሰገደ በኋላ ትክክለኛ እግዚአብሔር ሲገለጥ ሕዝቡ ሁሉ ለአውሬው ቃል ገብቶለት ወይም ፈርሞለት ስለ ነበር ወይም ከሱ ጋር ለመሆን ወስኖ ስለ ነበር ለእግዚአብሔር መሆን አይችልም፤ የእግዚአብሔር የሆኑ ነገሮችን በሙሉ መጠቀም አይችልም፡፡
ሰውን መከተል ምን አይነት ተጽዕኖ አለው? - ባርነት፣ መገዛት፣ በሰው ሀሳብ መመራት፣ የራስን አእምሮ እና ልብ አለመጠቀም፣ የተከተሉት የሆነውን ሁሉ መሆን፤ ከወደቀ መውደቅ፣ ከተሳሳተ መሳሳት፣ ካመነ ማመን፣ ከተቀበለ መቀበል፣ ከተቃወመ መቃወም፣ ከግል እምነት ወደ ቡድን እምነት ማድላት፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ብቻ እግዚአብሔር የሰጠውን አእምሮ፣ ስሜት እና ልብ አለመጠቀምን ያመጣና ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚለይ ይሆናል፣ ሐዋርያት ህዝቡ ክርስቶስን እንዲከተሉ አደረጉ እንጂ እነሱን እንዲከተሉ አላደረጉም፣ (መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ራሱ ‹‹የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የአግዚአብሔር በግ እነሆ ነበር ያለው››)፣ ፍቅር ልብ ላይ ነው ማረፍያው፤ ልብ ላይ የሚያድረው ደግሞ እግዚአብሔር ነው- ታዲያ እኛ ልባችንን ለምድራዊያን ፖለቲከኞች እና ዘፋኞች ካሳደርን እግዚአብሔር አልተካደም ወይ?፣ ቅዱሳን አልተካዱም ወይ? ለመሆኑ እያደረግን ያለነው ነገር ትክክል ነው (አእምሮአችንን)፣ ያስደስታል (ስሜታችንን)፣ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፤ እግዚአብሔር ወዶታል (ልባችንን) በዚህ ሁሉ አረጋግጠን ነው ወይ እንዲሁ ሆ ብለን የተነሳነው? ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ሁሉ እድሜው አጭር ነው ለሕዝብ ግን ታላቅ ሐዘን እና የልብ ስብራት ነው፡፡ ክርስቲያኖች አውሬው በምድር ላይ ተገልጦ ሕዝብ ሁሉ ቢከተለው እንደማይከተል ሁሉ አሁን ባለው ሁኔታ ግን አንድም ሰው የሚቀር አይመስልም፡፡
አውሬው የስምንት ሺህ ዓመት ልምድ ያለው በመሆኑ የተመረጡትን እንኳን እስከ ማሳት ይደርሳል፤ በምትሐቱ፣ በጥበቡ፣ በእውቀቱ እና በድርጊቱ፡፡የአግዚአብሔር እያስመሰለ፣ ከእግዚአብሔር የተቀባ በማስመሰል፣ ከእግዚአብሔር የሆነ በማስመሰል ሕዝብ እንዲከተለው በማድረግ ባልተከተለው ላይ ሕዝብ እንዲነሳበት ያደርጋል፡፡ ሠይጣን እና ተከታዮቹ በጭካኔ መንፈሱ ካልተሳካለት ትሕትና ወደሚመስል   የተመረጡት የተበሉት ጳጳሳት፣ ካህናት፣ መነኮሳትን፣ ዲያቆናትን፣ መምህራነ ወንጌልን፣ ማኅበራትን፣ ድርጅቶችን፣ በተለያየ መድረክ ተጽዕኖ ፈጣሪ ተብለው የታወቁትን ሲያስት ተከታዮቹ በሙሉ ይወድቃሉ፡፡ ይህ ሰይጣን ከምን ጊዜም በላይ ሕዝብን ለመጣል የሚጠቀምበት ሴራ ነው፡፡ ምንም እንኳን ጊዜው ቢደርስም፣ የአግዚአብሔር ፈቃድ ቢሆንም ጌታችንን አይሁድ እንዲይዙት ያደረገው በሱ ሞት መንጋው እንዲበተን ነበር፤ እውነትም በክርስቶስ መያዝ ከአንዱ በቀር ሌሎች ፍርሐት እና ድንጋጤ ይዟቸው ነበር፡፡ ሌሎችማ እነ ሉቃስ እና ቀለዮጳ ተስፋ ቆርጠው አምነው የነበሩትን ትተው ብርቱ ነብይ እንደ ነበረ አድርገው እያወሩ ወደ ኤማውስ መንደር ይሄዱ ነበር፡፡ አሁንም እየሆነ ያለው ከመንፈሳዊ ሊቃውንት እስከ ምእመን ድረስ ከእግዚአብሔር ይልቅ ሰውን የሚከተል፣ ሰውን የሚደግፍ፣ የዚህች ሀገር መፍትሔዋ ከቤተክህነት መሆኑ ቀርቶ ከፖለቲካ ዓለም ብቻ እንደሆነ በማሰብ ቤተክህነት ራሷ ፖለቲካን ወይም ምድራዊውን መንግሥት ብቸኛ መፍትሔ አድርጋ እንድትወስድ ማድረግ ቤተክርስቲያን ከጥንት ጀምሮ ይሰራ እንደነበር አሁንም ለአውሬው ለማስረከብ እየተሰራ ያለ ሴራ ነው፡፡ ምንም እንኳን እግዚአብሔር ስለተመረጡት አባቶች ባያሳካውም ቤተክርስቲያን እውቅና ሰጪ ሳትሆን እውቅና ጠያቂ ለመሆን እንድትሄድ የሚያደርግ አካሄድ እየተስተዋለ ነው፤ ይህ ደግሞ ለመጪው አውሬ ምቹ ይሆንለታል፡፡  

 ሰኔ 16/2010