በእንተ ርእስየ

Thursday, November 17, 2016

የመጨረሻው ዘመን ሰው

ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሔር አምሳል ነው ይህም በነፍሱ እግዚአብሔርን ይመስላል፡፡ የተፈጠረውም ከሳበት ባህርይ ነው ይህም ከአራቱ ባህርያተ ስጋ እና ከሶስቱ በህርያተ ነፍስ ነው፡፡ አራቱ ባህርያት የሚባሉ መሬት፣እሳት፣ነፋስ እና ውሃ ሲሆኑ ባህርያተ ነፍስ የሚባሉ ደግሞ ነባቢት (መናገር)፣ሕያዊት (መኖር-መተንፈስ)፣ለባዊት (ልቦ-ማስተዋል፣ማሰብ) ናቸው፡፡ ነፍስ እና ስጋ ሁል ጊዜ ይጣላሉ፣ይቀዋወማሉ፣የበላይ መሆን ይፈልጋሉ ያሸነፈ እንደፈለገው ይነዳል፣ይገዛል፡፡ እንደ ሰው ለእግዚአብሔር የሚሆነው ስጋውን ለነፍሱ ካስገዛ ነው ስጋው የሚያሸንፈው ከሆነ ግን ለዚህ ዓለም ብቻ ይሆናል፣ስለዚህች ዓለም ብቻ ያስባል፣ስለ ነፍስ የሚያስበውንም ሆነ የሚያተምረውን አካልም ሆነ ማኅበር፣ድርጅትም ሆነ ተቋም ይቃወማል፡፡ መጨረሻ ላይ የዚህ ዓለም ገዢ ለሆነው ለሰይጣን ይገዛል፡፡
እንግዲህ ከዚህ የተነሳ የሰው ልጅ የራሱን ሀሳብ ማለትም ስለ ስጋ ብቻ በማሰቡ ጠባዩ በየጊዜው እየተቀያየረ መጥቷል፡፡ በህርይው ግን አልተቀየረም ምክንያቱም ባሕርይ አይቀየርም ባህርይው ሰው ነውና፡፡ አንዳንድ ጊዜ የባሕርይ ለውጥ እናምጣ ይላሉ የዓለም ሰዎች፡፡ እንደ ሃይማኖት አስተምህሮ ግን የባሕርይ ለውጥ ማምጣት አይቻልም ይህን ማድረግ የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ የባሕርይ ለውጥ ማለት ከሰው ወደ እንሰሳ ከእንሰሳ ወደ ሰውነት ወይም ወደ ሌላ መቀየር ማለት ነው፡፡ ይህን በመጽሀፍ ቅዱስ ተጽፎ የምናገኘው ነው፡፡ የሰው ልጅ ማምጣት የሚችለው የጠባይ ለውጥ ነው፡፡የመጨረሻ ዘመን ሰዎችም ጠባያቸው ይቀየራል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ከሰው የማይጠበቀውን ሀሳብ ሲያስቡ፣ሲሰሩ፣ስናገሩ ምን ሆነው ነው እንላለን ይህ ግን የመጨረሻ ዘመን ሶወች ስለ ሆኑ ነው፡፡ ሰዎች ስልጣኔ እየመሰላቸው ከሰው የምይጠበቀውን ነገር ሲያደርጉ እናያለን ግን አትደነቁ የመጨረሻ ዘመን ሰዎች ናቸው፡፡ ብዙ ማለት ይቻላል ግን ከዚህ ቀጥሎ የመጨረሻ ዘመን ሰዎች ምን አይነት ጠባይ እንደሚኖራቸው አነግራችኋለሁ ስሙኝ፡፡
ስለ መጨረሻ ዘመን ሳይንስ ከመላምት ውጪ ተጨባጭ ነገር የለውም ምክንያቱም የመጀመሪያውን መች እርግጠኛ ሆነና እኛ በሃይማኖት ዓይን የምናስብ ግን የዓለም መጀመሪያ እንዴት እንደ ሆነ እና መጨረሸዋም እንዴት እንደሚሆን እናምናለን እናውቃለን፡፡ የዓለም መጨረሻ ማለት ሰማይ (ታችኛው) እና ምድር (የምድር አካለትም ጨምሮ) እድሜያቸው የተገደበ ስለ ሆነ እነዚህ እና በውስጧ ያሉ አልፈው አድሱሲቷ ሰማይ የምትገለጥበት ማለት ነው፡፡ይህ ከመሆኑ አስቀድሞ ግን በዓለም መጨረሻው ዋዜማ ላይ የሚኖሩ ሰዎች የራሳቸው ጠባይ ይኖራቸዋል፡፡ ጌታችን ስለ መጨረሻው ዘመን የተናገራቸው ነገሮች አሉ ይህም በማቴዎች ወንጌል ምእራፍ 24 ነው፡፡ የዓለም መጨረሻ በዚህ ጽሑፍ ማንሳት ይከብዳል ምክንያቱም ስለምሰፋ ለአሁኑ ግን የመጨረሻ ዘመን ሰዎች ምን አይነት ጠባይ እንደሚኖራቸው ነው የምነግራችሁ ከዚያ ተነስተን እኛም ከነሱ እንድንለይ እና በሚሆኑ ነገሮች እንዳንደነቅ ለማሳሰብ ነው፡፡
የመጨረሻው ዘመን ከተፈጥሮ ውጪ ስለሚሆን የሚያስጨንቅ ነው የሚሆነው ነገሮች በሙሉ እንደተጠበቁት አይሆንም ለዚያ ዓለም የሚመቹ ደግሞ ሕገወጥ የሆኑ ነገሮች፣ሀሳቦች፣ንግግሮች እና ድርጊቶች ናቸው፡፡ ከዚያ ውጪ የሆነ ተቀባይነት አይኖረውም፣አይወደድም፣እንዳልሰለጠነ እና እንደ ኋለቀር ይፈረጃል፡፡ ነገሮች በሙሉ ፋሽን ይሆናሉ ፋሽን ማለት አድስ፣የማይቆይ፣ ቶሎ የሚጣል፣የጥንቱን የሚጥል (የሚያስቀር)፣በተለይ ደግሞ ባህል እና ሃይማኖትን የሚያጠፋ ነው፡፡ በዚህ መኃል የሰዎች መሠረታዊ አኗኗርም ሆነ ሌላው ነገር ስለሚለወጥ ሰዎች ይጨነቃሉ ምክንያቱም ከተፈጠሩበት ዓላማ ውጪ ለሆነው ነገር ይጋለጣሉና፡፡ የሰው ልጅ ደግሞ ይህን ማወቅ ይጠበቅበታል፡፡
የመጨረሻው ዘመን ከማስጨነቁም በላይ የሰዎች ጠባይ ክፉኛ ይቀየራል፡፡ ሰዎች ስለ ራሳቸው ጥቅም ብቻ ያስባሉ በቡድን ስራ መሃልም የሚያሳስባቸው የአብሮ ማደግ፣የሀገር እድገት ሳይሆን የሚያሳስባቸው የራሳቸው ጥቅም ብቻ ነው የሚሆነው ይህን ሲያደርጉ ልዩ ትኩረት የሚያደርጉት እውቀት፣ጥበብ፣መንፈሳዊ እድገት ላይ ሳይሆን ገንዘብ ብቻ ይሆናል፡፡ ገንዘብ የሚወዱ እና ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉ፡፡ እኔ፣የእኔ ማለትን ብቻ የሚወዱ ይሆናሉ አንድም ጊዜ የእኛ፣እኛ ማለትን አይወዱም፡፡ ሰው ገንዘብ የሚወድ ከሆነ ደግሞ ለሰውም አይደለም ለእግዚአበሔርም አይሆንም አምላኩ ገንዘቡ ስለ ሆነ ባልንጀራውን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፡፡ ገንዘብ ከመውደዳቸውም የተነሳ ከስራው ይልቅ ገንዘብን ብቻ ያስባሉ የገንዘብ ማግኛ መንገዶች የተባሉትን ሕገ ወጥ በሙሉ ስርቆትን፣ሙስናን፣ዝርፍያን፣ማጭበርበርን ወዘተ ይጠቀማሉ በውስጣቸውም በዚህ ምድር ለዘላለም የመኖር ያህል ይቆጥራሉ ግን አይኖሩም፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ባላቸው ነገር ይመካሉ የሌላቸውንም እንዳላቸው፣ የማያውቁትንም እንደሚያውቁት ነው አንድም ጊዜ አናውቅም አይሉም፡፡ የሚመካ ቢኖር በእግዚአበሔር ይመካ የሚለውን ወደ ጎን በመተው በገንዘብ፣በሀብት፣በዘመድ፣በራሰቸውም የሚመኩ ይሆናሉ፡፡ከትምክህትም አልፈው ትዕቢተኞች ይሆናሉ ያላቸውን በማየት የሌላቸውን ደግሞ እንዳለቸው በማድረግ ይተብታሉ፡፡ ትዕቢት ደግሞ ሳጥናኤልን ከሰማይ የጣለ ልዩ ኃጢአት ነው፡፡ ሰው ትዕቢተኛ መሆኑን አያውቅም ከባድ የሚያሰኘውም ይህ ነው የትዕቢት ጠባዩ መጣል ብቻ ነው፡፡ የመጨረሻ ዘመን ሰዎችም ገንዘብ የሚወዱ፣ራሰቸውን የሚወዱ፣ትምክህተኞች እና ትዕቢተኞች ይሆናሉ፡፡
ሌሌቹ የመጨረሻ ዘመን ሰዎች ደግሞ በራሳቸው ስለማይተማመኑ ይሳደባሉ፡፡ ስድባቸው ደግሞ ሰውን ብቻ አይደለም የማያውቁትን እግዚአበሔርን፣ቅዱሳንን በድፍረት ይሳደባሉ አንዴ ልቦናቸውን ስላጡ ምንም አይመስላቸውም አንደ ትልቅ ነገር ይቆጥሩና ስድባቸውን የቃላት አጠቃቀምን ጉዳቱን እያሰቡ ይዝናናሉ፡፡ ስድብ ነው የሚቀናቸው ለታላቃቸው ፣ለወላጆጃቸው እንኳን አይታዘዙም ከእግዚአብሐየርም ይሁን ከሰው ለሚደረግላቸው ነገር ማመስገን አይሆንላቸውም ማማረር፣አለመጥገብ ነው፡፡ አይ የመጨረሻ ዘመን ሰው፡፡
ሌሎቹ የመጨረሻ ዘመን ሶወች ቅድስና የላቸውም ድንግልናን እንደ ነውር ያዩታል በድንግልና የሚኖር ወንድ እና ሴት በነሱ ዘንድ እንደ ኋለ ቀር፣ ያልሰለጠነ፣ያልዘመነ ወዘተ ይታያል፡፡ በማንኛውም መልኩ የሚያስቡትም፣የሚያወሩት ሆነ የሚያደርጉት ከዝሙት ጋር የተገናኘ ነው፡፡ የሚመጣው ማንኛውም ፋሽንም ቢሆን ቅድስናን ከሚያጎድፍ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በመጨረሻው ዘመን ሰዎች ዘንድ ዝሙት እንደ ስልጣኔ ይቆጠራል ለዚህ እኮ ነው አደጉ የተባሉ እነ አሜሪካ እና ደቡብ አፍሪካ ግብረ ሰዶምን ያጸደቁት በሀገራችንም ቢሆን እኮ አሉ፡፡ በትዳር ላይ የሚባልግ ህዝብ የበዛበት ዘመን ላይ አይደለም እንዴ ትዳር ለዝሙት ብቻ የሆነበት ዘመን ላይ እኮ ነን ግን ጋብቻ እንዲህ አልነበረም፡፡ በዘመናችን ፍቺ ለምን እንደበዛ ያውቃሉ የጋብቻን ዓላማ ስለ ሳተ እኮ ነው፡፡ ቅድስና ስለ ሌላቸው ደግሞ በምንም መልኩ ፍቅር አይኖራቸውም፡፡ ቅድስና ሰው የተፈጠረበት ዓላማ ነው እንዲሁም ፍቅር፣ጥልን እንጂ ዕርቅን አይሰሙም ይህ ነው እግዲህ የመጨረሻ ዘመን ሰው፡፡
የመጨረሻው ዘመን ሶዎች ከስራ ይልቅ በማውራት፣በወሬ፣ሀሳብ በመስጠት፣ሀሳብ በማቅረብ ያምናሉ፡፡ ወሬ ለእነሱ ስራ ነው ለስራ ከተሰጠው ሰዓት ይልቅ ለስብሰባ የሚውለው ሰዓት ይበልጣል፡፡ በዚህ ቢያቆሙስ አብዛኛውን ጊዜያቸውን ስለ ሰው በማውራት ያሳልፋሉ- ሐሜት፡፡ ስለ ሰው ማውራት ደግሞ ስለ ራስ ካለማወቅ እና ካለመመልከት የተነሳ ነው፡፡ አንድም ሰውን ማማት ማለት ስጋውን ያላ ካራ ደሙን ያለ ዋንጫ መጠጣት ነው፡፡ የመጨረሻ ዘመን ሰው ደግሞ በዚህ ብቻ አያቆምም ድፍረቱ ከባድ ነው ልክ ሕዝበ እስራኤል በበረሃ እያሉ እግዚአብሔርን እንዳሙት እነሱም እግዚአበሔርን ያማሉ፡፡ እግዚአብሔር የሚችለውን አይችልም የሚሉ ሰዎች የበዙበት ዘመን፡፡ ይህ እግዚአብሔርን ማማት ነውና፡፡ ስለዚህ የመጨረሻ ዘመን ሰዎችም ብዚ ጊዜያቸውን ሲጠጡም፣ሲበሉም በሁሉም ቦታ ስለ ሰው በማውራት ያሳልፋሉ- ሐሜተኛች፡፡
በዚህ ብቻ መች ይበቃል የመጨረሻ ዘመን ሰው ጠባይ ራሳቸውን የማይገዙ ናቸው፡፡ ልባቸው የፈቀደውን በሙሉ ያደርጋሉ ኃጢአትም ይሁን ሌላም፡፡ ከዚህ የተነሳ ጨካኞች እና መልካም የሆነውን የማይወዱ ናቸው፡፡ ሰውን በጭካኔ መግደል፣በመርዝ መበረዝ፣ መቅናት፣የማይቆይ ፍቅር፣ ሰውንም ሆነ እግዚአብሔርን የሚክዱ፣ጠንቋይ እና አስጠንቋይ የሚሆኑ፣ለሚሰሩት ነገር የሚቸኩሉ፣በትዕቢት የተነፉ በአጠቃላይ መልካም የሆነውን በሙሉ የማይወዱ ሰዎች ናቸው፡፡
የሚገርመው ደግሞ የመጨረሻ ዘመን ሰዎች የእግዚአበሔርን ሕግ ከማክበር ይልቅ፣ፈቃዱን ከመፈጸም ይልቅ ተድላ ደስታ የሚወዱ ናቸው፡፡ መጨፈር፣መዝናናት፣መጠጣት፣መዝፈን፣ዝሙት መፈጸም ወዘተ ወይም ቅዱስ ጳውሎስ የተናገራቸውን የስጋ ፍሬዎችን የሚፈጽሙ ብቻ ይሆናሉ፡፡ እንዲሁም እነዚህ የመጨረሻ ዘመን ሰዎች መልክ እንጂ ምንም የላቸውም፡፡ ለምሳሌ ሃይማኖት አለን ይላሉ ነገር ግን የሃይማኖት ነገር አይሰሩም፣ ክርስቲያን ሆነው ይዘሙታሉ፣በዘር ይከፋፋላሉ፣ሙስና ይሰራሉ ወዘተ በአጠቃላይ መሆን የሌለባቸውን ሆነው የሚገኙ ሰዎች የሚበዙበት ዘመን ነው የመጨረሻው ዘመን፡፡
ለብዙዎቻችን የሰው ጠባይ ሲቀየር፣ሲለዋወጥ እና ከሰው የማንጠብቀውን ነገር ስንመለከት ሊገርመን ይችላል ነገር ገን ይህ ሁሉ ቀድሞ ስለ ተነገረን ማድነቅ ወይም ግራ መጋባት አያስፈልግም ይልቁን ቅዱስ ጳውሎስ ስለ መጨረሻው ዘመን ሰዎች ጠባይ ከዘረዘረ በኋላ የነገረንን ምክር እና ትምህርት መስማት ብቻ ነው የሚያዋጣው፡፡ ይህም ከነሱ መራቅ፣መለየት፣ህብረት አለመፍጠር፣አለመተባበር ነው (2ጢሞ.3፡1-10)፡፡ በመጨረሻም ተጨንቀው ምድርን ከምያስጨንቁ ከመጨረሻው ዘመን ሰዎች እግዚአብሔር አምላክ ያድነን አሜን፡፡  
ህዳር 2009 ዓ.ም

Wednesday, August 3, 2016

ዘረኝነት እና ዘረኞች

ባሁኑ ጊዜ ያለው የዘረኝነት አባዜ ከፖለቲካው አልፎ በመንፈሳዊ ቦታዎችም መስፋፋቱ ነው ይህንን የሚያራምዱ ሰዎች ደግሞ ለእግዚአብሔር እንደቀኑ አድርገው ማሰባቸው ያሳዝናል፡፡በዓለም ያሉ ደግሞ ያው ባሁኑ ጊዜ ዓለምን እንቆጣጠራታለን ብለው የሚያስቡ የእነ ኢሉሚናቲ እና መሰሎች የዘረኞች ስብስብ ድርጅት ተገዢዎች ስለ ሆኑ አይፈረድባቸውም ከእግዚአብሔር ይልቅ ሰይጣንን ስለመረጡ መጨረሻቸውም ከአጋንንት ጋር ስለሆነ ዘረኝነትን አጥብቀው ያራግቡታል ምክንያቱም ሰው ከእግዚአብሔር የሚለየው አንዱ በዘረኝነት ነውና፡፡ አመናችሁም አላመናቹሁም ዘረኞች የእግዚአብሔርን መንግስት አይወርሱም(ገላ. 5) ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን እና ቅዱሳን ቦታዎች ስፍራቸው ስላልሆነች ለክርስቶሳሳውያን ለምን አይለቁም?? ለመሆኑ ዘረኛ ማነው?? ሰውን ዘረኛ ከማለትህ በፊት ራስህን ተመልክተህ ታውቃለህ?? ይህን ካልለየህ ያልገባህ ነገር አለ ማለት ነው ወይም የዘረኝነት ምስጥሩ አልገባህም ማለት ነው፡፡ በአንተ አእምሮህ ውስጥ ሰው ሁሉ እኩል መሆኑን ካላወክ፣ሁሉንም ካልወደድክ፣የሁሉም መዳን የማያስደስትህ ከሆነ፣የሰፈርህ ሰዎች ብቻ ሰው መስለው የሚታዩህ ከሆነ፣የኔ እኔ ብቻ የምትል ከሆነ አትጠራጠር ዘረኛ ነህ፤ክርስቲያን አይደለህም፤ኢትዮጵያዊም አይደለህም፤የበግ ለምድ የለበስህ ተኩላ ነህ፡፡ ያልገባህ ምስጢር ቢኖር ትዕቢት፣ዘረኝነት እና ወዘተ የመሳሰሉ የሰው ጠባያት ለባለቤቱ የማይታወቁ መሆናቸው ነው፡፡ ለዚህ እኮ ነው ለዘረኞች የሚያስቡትም ሆነ የሚያደርጉት ነገር በሙሉ ትክክል መስሎ የሚታያቸው መቼም ቢሆን አይገባቸውም ቀኑ ከእግዚአብሔር ጋር ተቆርጣ ስትመጣ ብቻ ነው የሚገባቸው፡፡ ዘረኝነትን መዋጋት ከአጋንንት ጋር እንደ መዋጋት ስለ ሆነ ዘረኞችን መዋጋት ሐጢአት አይደለም፡፡ ምክንያቱም የዘረኞች መሪ ሰይጣን ስለ ሆነ ነው፤የሚገዙት ለሰይጣን እንጂ ለፈጣሪ አይደለምና፡፡ቅድስት ቤተ ክርስቲያንንም ሆነ ሀገርን ለዘረኞችም መስጠት ለሰይጣን እንደማስረከብ ይቆጣራልና፡፡ ባሁኑ ጊዜ ይህን ህዝብ ለመረከብ እያኮበኮበ ያለው የሰይጣን ማኅበር እንዳለ መቼም ታውቃለህ ምክንያቱም ከእውነት ይልቅ ለወሬ ቦታ ስለምትሰጥ፣ከክርስትናው ይልቅ ፖለቲካው ስለማረከህ፤ አእምሮህን ስለ ተቆጣጠረ እንዲህ አይነቱ አያመልጥህም ግን ምን ዋጋ አለው እነኚን ጊዜ ይገድባቸዋል አንተም የክርስቶስ ልጅ ሆነህ በጊዜ መገደብህ ከዚህ የሚበልጥ ኪሳራ አለ ብለ ታስባለህ??ያሳዝናል፡፡ ከሰማህ መፍትሔውን ልንገርህ?? ክርስቲያን ሁን፣ተጠመቅ፣ንስሀ ግባ፣ክርስቶስን በትክክል እወቀው፣ቅዱሳንን ምሰል (ቅዱሳን ዘረኞች አይደሉምና)፣ጸልይ፣ወደ ክርስቶስ ስጋ እና ደም ቅረብ ያን ጊዜ ውጤቱን ታየዋለህና... ወልዶ ያሳደገኝ አባቴ ይህን ነበር ያስተማረኝ ‹‹ከሁሉም ጋር በፍቅር ኑሩ ሰው በመሆኑ ብቻ ውደደው ቅረበው›› እያለ(ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ካልሆነ በኔም በአባቴም ፍረዱ)

Monday, June 20, 2016

የሳጥናኤል ደብዳቤ (ማመልከቻ) ለእግዚአብሔር



ቀን፡- 22/01/7509
ቁጥር፡-666
ሁሉን ለፈጠረ ጽርሐ አርያም ለሚኖር ለእግዚአብሔር
ጽርሐ አርያም
ጉዳዩ፡- ውክልና ስለመስጠት ይሆናል
ይድረስ ለፈጣሪዬ ለእግዚአብሔር የሁሉ አስገኚ ከላይ ርዕሱ ላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት እኔ ሳጥናኤል  ከመላእክት ወገን የነበርኩ በስራዬ ምክንያት ይህም በትዕቢት አምላክ ነኝ በማለቴ አንተም ይቅር ልትለኝ እስከ ረቡዕ ድረስ ሰማይ ላይ እንዳቆየኸኝ ታስታውሳለህ፡፡ከዚያ በኋላ ለሶስት ነገድ ተከፍዬ አጋንንት፣ሰይጣን እና የአየር ጋኔን ተብዬ በትዕቢት የተነፋው ፍጡር በመሆኔ እምቢ በማለቴ ከሰማይ ጣልከኝ፡፡ በተለይ የማልረሳው በኔ ቦታ የተሾመው ሚካኤል (አቤት ስሙ ስያቃጥል ኡሁ) እሱማ ተጫወተብኝ፤ልኬን ነበር ያሳየኝ ይኸው እስከ ዛሬ ድረስ በየቀኑ እኔ የምበርዘውን ውኃ እየባረከ ህዝቡን ይጠብቃል፡፡ ከውስጤ ስለማይጠፋ ነው ከርዕሴ የሚያወጣኝ አሁን ወደ ደብዳቤዬ ኣላማ ልመልስህ፡፡ ልክ ከሰማይ እንደወደኩ ያደረኩትን መቼም አንተ ታውቃለህ አዳምን ከዚያች ገነት እንድኮበልል አደረኩ፣አንተ ላይ እንድነሳሳ፣አንተን እንዲያሳዝን፣አመጸኛ እና ወዘተ አደረኩት፡፡ ልክ እሱም እንደ እኔ ከገነት ወደ ምድር ሲመጣልኝ ጢባጥቤ ተጫወትኩበት እሱ ደግሞ ሲበዛ የዋህ ነው፡፡ ሔዋንንማ ተዋት ከባድ ናት፤ፈጣን ናት አዳም ምክሬን አልሰማ ቢል በሔዋን በኩል ስሄድበት አልቆየም ፈቃዴን ፈጸመልኝ እርቃናቸውን መሆናቸውን ገለጥኩባቸው ዕፀበለስን በልቶ ወደ እኔ ወደ ምድር መጣልኝ፣ ስምንተኛ ማዕረግ ላይ የነበረው አዳም ወደ ዜሮ መጣልኛ አቤት ደስ ስል፡፡ ከሁሉም ፍጥረት ጋር ተጣላልኝ ከመላእክት፣ከእንሰሳት (የዱር እና የቤት)፣ከአራዊት (የቤት እና የዱር)፣ከምድር ኧረ ዘርዝሬ አልጨርሰውም ቢቀር ይሻላል፡፡ የሆነበትን አንተ ታውቀው የለ እሱም ያቀዋል፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው አንተ መጥተህ አዳንከው፣ከእጄ ማረክ፣ዋይ ዋይ ተዋረድኩ፣ተሸነፍኩ፣ጥበቤ፣ሴራዬ ባዶ ሆነ፡፡ እኔ በእባብ ስጋ ተሰውሬ ብመጣ አንተም ከድንግል ማርያም (ኡፍ! አልቻልኩም) ስጋን ነስተህ ሰው ሆነህ አዳንከው፣ወደ ቀደመ ክብሩም መለስከው ወይኔ! ወይኔ! እንደዚህ አይነት መዋረድ የለም፡፡ ሰላሳ ሶስት ዓመት በዚህ ምድር ላይ ስትመላለስ መቼ አወኩ፣ መቼ ተረዳሁህ፣ መቼ ገባኝ፣ እኔ እኮ ተራ ሰው መስለኸኝ ነበር፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው አንተ በምታደርጋቸው ነገሮች ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የሰው አንዳንድ ጊዜ የአምላክ ስራ ትሰራለህ ለማንኛውም ሰራህልኝ፡፡ነፍሳትን በሙሉ ማረክ ኀይሌም ደከመ፡፡
እኔም ይህን ያደረከውን ሳስብ በጣም ይቆጨኛል፡፡ ለጊዜው በዚህ ምድር ላይ ስጋ ለብስህ የተገለጥክ ጊዜ ስለምጠራጠር አንተን እንድያስወግዱ አደርግ ነበር አንዴም በሄሮድስ፣ከዝያም በደቀመዝሙርህ ልቡና (አስቆሮቱ ይሁዳ)፣በመጨራሻም በአይሁድ አሰቀልኩህ፡፡ ግን ባሰብኝ እንጂ መከራው አልቀለለልኝም፡፡ ከማኅፀን ጀምሮ እቆራኝ የነበረውን ዛሬ አልቻልኩም ይህማ ቆየ እንተ ወደዚህ ምድር ሳትመጣ ራሱ አቅቶኝ ነበር ይህም እናትህ ስትጸነስ፣ስትወለድ ከኔ ተሰውሮ የለም ወይ፡፡ ያንተንም ብተው እና ዝም ብል ይሻላል ያለወንድ ዘር በዝያ ላይ ደግሞ በድንግልና ተጸንሰህ በድንግልና ተወለድክ ኧረ ይቅር ምን እዚህ ውስጥ ከተተኝ ደግሞ፡፡ ሆኖም ግን አንተ ያደረከውን ስራ፣ያን ጊዜ የነበረኝን ስልጣን ለመመለስ ሁል ጊዜ በእቅድ እየሰራሁ ይኸው ዛሬ 2009 ዓመት ሆኖኛል፡፡ ፈጽሞ እንቅልፍ በአይኔ አይመጣም ሌሊት እና ቀን ነው የምሰራው የራሴ ኮሌጅ አለኝ በስሩ ደግሞ ብዙ ዲፓርትመንቶች (ትምህርት ክፍሎች) አሉ፡፡ ትምህርት ክፍሎች ግን በጣም ብዙ ናቸው ለምሳሌ ምንፍቅና፣ተሀዲሶ፣አህዛብነት፣አስማት፣ሟርት፣ጥንቆላ፣ዝሙት፣ዘፈን፣…. ኧረ ይቅር ብዛቱን እኔ ራሴ ዘርዝሬ አልጨርሰውም፡፡ለአዳም ልጆች ይህ ሁሉ የተለያየ ይመስላቸዋል ነገር ግን የሁሉም ዲፓርትመንቶች ዲናቸው እኔ ነኝ ሁሉንም እቆጣጠራቸዋለሁ የማይሰራውን ሰነፍ ሰራዊት በጭካኔ መንፈስ እቀጠቃለሁ ስልጣን ሰጥተኸኝ የለ፡፡ ህዝቡን ለማወናበድ ስል ትምህርት ክፍሎችን የተለያዩ አስመስላቸዋለሁ ዓላማቸው ግን አንተ እንደሚታውቀው የአዳምን ልጆች ካንተ እጅ አውጥቶ በሲዖል ማኖር ከዚያም በኋለኛው ዘመን ለገሃነም ማሰረከብ ነው፡፡ ዛሬ ዛሬማ የራሴ ቤተመቅደስ እንዳለኝ አንተ ታውቃለህ አንተን የማያውቁ በእውቀት ብቻ የሚነዱ፣ እንጅነር ቅጣው እጅጉ ከተለያትማ ራስዋን የሳተች አሜሪካ እኮ ናት ቤተ መቅደሴን የሰራችልኝ፡፡ አንዱ አዋቂ ነኝ ባይ አንቶንሌቪ በሳንፍራንሲስኮ ውስጥ የራሴ ቤተመቅደስ ሰርቶልኛል፡፡ ስጋ ባይኖረኝም ስጋዬን ይበላሉ፣ደም ባይኖረኝም ደሜን ይጠጣሉ ልክ ያንተ ትክክለኛው ስጋ እና ደም እንደሚበላ እና እንደሚጠጣ፡፡ በየጊዜው መስዋዕት ይሳውልኛል የሚሰዋው ደግሞ የሕጻናት ደም ነው ያን ጊዜ በስጋ ወደዚህች ዓለም መጥተህ የነበረ ጊዜ ገና በስጋ የሁለት ዓመት ሕጻን ሆነህ ሳለህ በሄሮድስ አድሬ ላሰገድልህ ነበር ምክንያቱም አምላክ መሆንህ መች አውቄ እኔ የመሰለኝ ታላቅ ነብይ፣ንጉስ ወይም በዝያን ጊዜ ካሉት ነገስታት ያለቅህ እንደምትሆን ብቻ ነበር እንዲህ አስቤ ነው ያን ጊዜ እነኛን ሁሉ ሕጻናት ያስገደልኩት፡፡ ዛሬም የሐጻናት ደም በየቦታው ይፈሳል በተለይ በመቅደሴ እና በማኅበሬ ዘወትር የሰው ደም ይፈሳል በተለይ የሕጻናት፡፡ አንተ ንጹህ መስዋዕት ትወድ የለ እኔም የንጹሐን ሕጻናትን ደም እወዳለሁ፡፡ ትልቅ ማኅበር እንዳለኝም ታውቃለህ ይህም ኢሉሚናቲ ይባላል፡፡ በጣም የምኮራበት ማኅበር ነው ምክንያቱም የማይገባበት ቦታ የለም ገንዘብ ላይ፣ህክምና ውስጥ፣ባሕል ውስጥ፣ ኧረ አሁንማ በቤትህም ገብቷል ልክ አንተ ዮሐንስ ባለ ራዕዩን እንዳናገርከው በራዕይ ዮሐንስ ምዕራፍ 12፣13 ሌላም፡፡ ተሀድሶ እያሉ ቤትህን ያውካሉ፣ጥርጣሬን፣ክህደትን እና አመጽ በቤትህ ሞልተዋል፡፡ ስለ እኔ ማንነት የሚያጋልጡ መጻሕፍትን ስያጣጥሉ እያየኻቸው ነው አይደል ለምሳሌ መጽሐፈ ሄኖክ- የኔ ማንነት እኮ የተጋለጠው በሱ ነው፡፡ ዛሬ ያሉ መናፍቃን እና ተሀዲሶዎች በአደባባይ የሚቃወሙት ይህን መጽሐፍ ነው ብልጦቹ የኔ ወደጆች እንደ አሜሪካ፣እንግሊዝ-እንግላንድ (አንጀል ላንድ)፣ሌሎችም ሀገሮች መጽሀፉን በተለየ መልኩ ይፈልጉታል፡፡ ምክንያቱም እኔን ስለሚከተሉ ሌሎች ሰዎችም ወደነሱ እንዲመጡ ከዚያ የኔ እንዲሆኑ ይፈልጋሉ፡፡ ያቺን ሀገር ማለቴ ኢትዮጵያ ዛሬ የዘረኞች መነኻሪያ የሆነች መልኳን የቀየረች ምድር እንኳን የመጽሐፈ ሄኖክ መገኛ የነበረች ሀገር ዛሬ መጽሐፉን አጥብቃ ትቃወማለች ምክንያቱም ካንተ ይልቅ እኔን መስማት ጀምራለችና ካንተ በረከት ይልቅ የኔን የጥንቆላ ስራ፣አስማት እና ሴራዎች ላይ የሚደገፉ ሰዎች የበዙባት ሀገር ሆናለች፡፡ ይገርመሃል የኔ ወደጅ የነበረች የእንግሊዝ ንግስት የነበረች ንግስት ኤልሳቤጥ ጄምስ ብሩስ የሚባለውን ሰው ወደ ኢትዮጵያ ልካ አስራ ሰባት ዓመት በዝያች ሀገር እንዲኖር አድርጋ፣ የሀገሩን ቋንቋ ተምሮ፣ ከባህሉ ጋር ተለማምዶ የሀገሩ ህዝብ ደግሞ ሞኝ አትለው የዋህ እንግዳ መቀበል በሚባል አባዜ ከውጪ የሚመጡ እንግዶችን ማንነታቸውን ሳያጠኑ እስከ ቤታቸው ድረስ ያዘልቃሉና ይህ ሰውም ጎንደር በሚገኘው ሙዚየም ከገዢው አካል ጋር በመወዳጀት፣በመቅረብ፣በመላመድ መጽሐፈ ሄኖክን ሰረቆላት ሄዶ አስረከባት፡፡ ይህን ያደረገችበት ምክንያት የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለኔ እንዳያውቅ እና በመጨረሻው ዘመን የኔ አምላኪ እንዲሆን ነበር፡፡ ይህ እውነትም አንተ ለሀገሪቱ ያለህ ቃል ኪዳን፣የቅዱሳን ምልጃ፣የእናትህ ጸሎት እና የአንዳንድ በጎ ሰዎች ጸሎት ነው የሚያቃጥለኝ እንጂ ተሳክቷል ማለት እችላለሁ፡፡ ብዙዎች የዚህ መጽሐፍ ተቃዋሚ ሆነዋል፡፡ የሚገርመው ግን አለ ማስተዋላቸው ነው መጽሀፈ ሄኖክ ስለ እኔ ብቻ አይደለም የኔን ትምህርትም የሚያጋልጥ ነው ይህም የሳይንስን ትምህርት የሚያዋርድ ስለ ሆነ እኔ የሚፈልገው ወደጆቼም የሚፈልጉት ሰው ከሃይማኖት ትምህርት ይልቅ የሳይንስን እንዲቀበል ለማድረግ ነው፡፡ በአጠቃላይ መጽሐፈ ሄኖክን አጥብቄ ስለሚጠላው ነገርኩህ እንጂ ዛሬ መናፍቃንም ሆኑ አስመሳዮቹ ተሀዲሶች የሚቃወሙት መጻሕፍት ሁሉም ያንተን መንገድ የሚያሳዩ የኔን መንገድ የሚያጋልጡ ስለ ሆኑ የኔ ወደጆች አይፈልጉትም፡፡ ዛሬ በቤትህ ተጣብቀው ያሉ ተሀድሶ መዥገሮች መጨረሻቻው አኔን ወደ ማምለክ ነው ምንም ማረጋገጫ አያስፈልግም ልክ በውጪ ያሉ መናፍቃን እንድሚያደርጉት ናቸው ልዩነታቸው ውስጥ በመሆናቸው ብቻ ነው፡፡ እንግዲህ እንዳልኩህ ይህ ኢሉሚናቲ ትልቅ ስራ እየሰራ ነው ብዙ ዓመት የስራ ልምድ አለው፡፡ብዙ አገልግሎት እየሰጠ ነው ከዚህም ውስጥ አልባሳትን፣መድኃኒቶችን፣ምግቦችን፣መጠጦችን ወዘተ ለዓለም ያከፋፍላል፡፡ በምርቱ ላይ ደግሞ የኔን ዓላማ ያራምዳል አሳረፈኝ እያልኩህ! ይህን ማኅበር ብዙዎቹ ቶሎ አይረዱትም፣የተረዱት ደግሞ ቶሎ ይገደላሉ፡፡ እንዳልነግርህ አንተ ሁሉን አዋቂ ነህ፡፡ ከዚህ ማኅበር ወጥተው፣ተለይተው፣ተቃውመው ላንተ የሰገዱ ይገደላሉ ባጠቃላይ አንተን የሚያመልኩ ክርስቲያኖች በዚህ ማኅበር አይወደዱም እደ እንቅፋት ይቆጠራሉ ሁል ጊዜ ይታረዳሉ፣ይገደላሉ ቦታም የላቸውም፡፡ይህን ማኅበር የተቀላቀሉ ደግሞ በዓለም ላይ ልዩ ትኩረት የተሰጣቸው ባለስልጣናት፣ባለሀብቶች፣ዘፋኞች፣የካቶሊክ እምነት ጳጳስንም ጨምሮ ሌሎችም የዚጅ ማኅበር አባል ናቸው፡፡ወነኛው የዚህ ማኅበር ምልክት ደግሞ 666 ነው ለዚህ ነው ለደብዳቤዬ ልዩ ቁጥሩ 666 ያደረኩት፡፡ እስቲ በዓለም ላይ ያሉ ዓለም ዐቀፍ አርማዎችን ተመልከት በተለይ አደግን የሚሉ ሀገሮችን እያንዳንዳቸው ከኔ ዓላማ ጋር የተገናኙ ናቸው ማላቴ ኩራቴ የሆነው የኢሉሚናቲ ማኅበር አርማ ማለቴ ነው፡፡ አሁንማ ይባስ ብለው የኔ መንፈስ የሚሰርጽበትን ቴክኖሎጂ አሰርቻለሁ ይህም ማይክሮ ቺፕ ነው፡፡ አንተ ግን ቀድመህ ዮሐንስ በራዕይ እንዲመለከት አደረግህ ይም በምዕራፍ 13 ላይ ያለው፡፡ ለማደናበር ያህል ቴክኖሎጂው ያስፈለገበት ምክንያት የዓለም አሸባሪዎችን ለመቆጣጠር እና ለሰው ደኅንነት ነው ብዬ አስለፍፋለሁ፡፡ ለመሆኑ አሸባሪዎች እና የሰውን ደኅንነት የነሱ ማናቸው ራሰቸው አይደሉም እንዴ፡፡ አንዳንዴ እኔ ከማሰራቸው ውጪ እኔ የሚያስቡት ተንኮል እና ክፋት ይገርመኛል ወይ የአዳም ልጆች!
ለመግለጽ እንደሞከርኩት አሁን ስራዬን የሚሰራልኝ ዓለም ራሱ ነው፡፡በሕግህ የተከለከለውን ያደርጋሉ፣ያን ጊዜ የሰዶም እና የጋሞራ ሕዝብ አጥፍተህ ሎጥ እና ቤተሰቦቹን ብቻ እንዳዳንክ እያወቁ ዛሬ ላይ ሰዎች ደግሞ ይፈቀድልን እያሉ እኮ ነው፡፡እውነት ይህ እኔን ራሱ ያስቀኛል ምክንያቱም ሰዶም እና ጋሞራ የጠፉበትን ተግባር እና ድርጊት ይፈቀድልን ብሎ መነሳት ምንኛ ጥፋት፣ሞኝነት፣አለዋቂነት እና ድንቁርና ነው የሚገርመው ደግሞ በዚህ ምድራዊ እውቀት የመጠቁ ናቸው ይህን ስራ የጀመሩት፡፡ ምን ያድርጉ እውቀት እንጂ መች ጥበብ አላቸውና፡፡ ዳንኤል በትንቢቱ በምእራፍ 12 ‹‹በመጨረሻው ዘመን እውቀት ይበዛል›› ስለሚል ይህ ይፈጸም ዘንድ ሆኖአል፡፡ ዳንኤልም እውቀት ይበዛል አለ እንጂ ጥበብ ይበዛል አላለም፡፡ ጥበብ ቢሆንማ ኖሮ አንተን በፈሩ፣ባከበሩ፣በተገዙልህ፣ባመለኩ፣ባወቁህ ነበር፡፡ አሁንማ ሳየው እኔ ያልሰራሁትን ስራ እየሰሩ ናቸው፡፡ ከኔ የሚበልጥ ጥበብ ያለቸው እስኪመስለኝ ድረስ፡፡
በአሁኑ ጊዜ ያለው ጭካኔ ይገርማል መለያየቱ፤ዘረኝነቱ፣መገዳደሉ፣ጠቡ፣ክርክሩ፣ትዕቢቱ፣ክፋቱ፣ሙስናው፣የሀገር ፍቅር ማጣት፣አለባበሱ፣ ኧረ ስንቱን ልንገርህ በቃ ምን ልበልህ ጰውሎስ ለጢሞተተዎስ በሁለተኛ መልእክቱ የጻፈው በምዕራፍ ሦስት ከቁጥር አንድ እስከ አስር ድረስ ያለውን በሙሉ የሚፈጽም ሰው ነው ያለው፡፡ ያን ቃል እንድፈጽሙ እኔ የተወሰነ ነገር ነው የምሰራው ራሳቸው ናቸው የሚገፋፉኝ፣የሚነካኩኝ፣እኔ ያላሰብኩትን ሀሳብ እያሳሰቡኝ የኔን ቦታ ወስደው በራሳቸው ሰይጣን ሆነዋል ፡፡ ጠዋት ቤትህ ይመጣሉ ሌሊት ደግሞ ርኩስ መንፈስን በወደጆቹ የሚልኩ የሚያስልኩ ሰዎች የበዙበት ጊዜ እኮ ነው እኔ ደግሞ እነዚህን የተላኩ መናፍስት ስራቸውን መስራታቸውን እና አለመስራታቸውን ለመቆጣጠር ብዙ ጊዜ ይወስድብኛል፡፡ ሰራዊቴ ተግባራቸው በትክክል ካልተወጡ እነሱን እየቀጣሁ በሰራዊቴ ዘንድ ጨካኝ ተብያለሁ፡፡ እና ያሉት ያደጉ ሀገሮች የሚባሉት እኮ ላንተ የተገዙ ሳይሆን ለኔ የተገዙ ናቸው፡፡ አሜሪካን ተመልክተሃታል መላ ሁኔታዋ እኮ የኔ፣ለኔ ናት፡፡ እስኪ የአሜሪካን ዋና ከተማ ዋሽንግተን ዲሲን ከላይ ሁነህ ተመልከታት በድሮ ዘመን ትመለክ የነበረችዋን ወፍ እኮ ነው የምትመስለው፡፡ በዶላራቸው ላይ ተመልከት እሺ እኔ ምን ላድርግ በዚህ እኔ መጠየቅ አለብኝ በፍጹም አይሆንም፡፡ ከላይ በገለጥኩት ትምህርት ክፍሎች ስር በሰፊው እየሰራ፣ብዙ ተማሪ እየተቀበለ ያለው የዘፈን ትምህርት ክፍል ነው፡፡ አሁን በቅርቡ ባቀረበልኝ ማመልከቻ መሠረት እራሴን ችዬ ኮሌጅ ወይም እንስትቲዩት ካልሆንኩ ብሏል፡፡ በርግጥ እየሰፋ በመምጣቱ እንደ ዝሙት እራሱን ችሎ መገንጠሉ አይቀርም በቅርቡ የትምህርት መመሪያውን (ካርኩለም) ልኮልኛል፡፡ ስመለከተው የሚያስኬድ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም በሁሉም ሀገሮች ይህ የሙዚቃ እንዱስትሪ እየሰፋ መጥቷል ያቺ ሀገር ቃል የገባህላት ሀገር ኢትዮጵያ ሳትቀር ይህን እንዱስትሪ በስፋት እያስፋፋች ነው፡፡ በቅርቡ እንኩዋን ታለንት ሾው እያለች ልጆችዋን ታወዳድራለች፤ህዝቡዋ ደግሞ የዋህ ስለሆነ እንጄራ የወጣለቸው ስለሚመስላቸው ይቦንሱታል፣መልካቸውን አጥተዋል፣ባሪያ ሆነዋል፤ወይ የድንግል ማርያም ልጆች፣የቅዱስ ያሬድ ልጆች፣ኧረ ስንቱን ልንገርህ ዛሬ ያሉ የኢትዮጵያ ልጆች ግን የኤርምያስን ቃል (ትንቢት) የጣሱ ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያን ያነሳውልህ በጣም ስለምታቃጥለኝ ነው ጸሎት እኮ አይቋረጥባትም በገዳም ብትሄድ ሁል ጊዜ ጸሎት ነው ዛሬ ዛሬ ግን መስለው የሚገቡ ቢኖሩም እንጂ፣ ጠዋት ኪዳን ከዝያም ቅዳሴ አይቋረጥባትም  ይህ ነው የሚያንገበግበኝ፡፡እና ይህ የሙዚቃ እንዱስትሪ በመስፋፋቱ የተነሳ ባሉ ክልሎች፣ባሉ ቋንቋዎች በሙሉ የራሳቸው የውድድር መድረክ አላቸው፡፡ ለምሳሌ በአማራ ክልል ባላገሩ፣በአሮሚያ ክልል ደደራሮ ወይም ታለንት ሾው በሚል ያወዳድራሉ ከዚያም ተወዳዳሪዎቹ በዓለም ዘንድ ታዋቂ ይሆናሉ፡፡ ከዚህ የተነሳ በዚያች ሀገርም ሆነ በዓም አቀፍ የሙዚቃ ቤቶች የበዙበት፣ዳንስ ቤቶች፣የማታ ክበብ (ናይት ክለብ) እያሉ የብዙ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል በተለይ የወጣት ሴቶች እና ወንዶች የተበላሸበት ዘመን ነው፡፡ እነኚ የሙዚቃ እና ዘፈን ቤቶች ደግሞ ብቻቸውን አይደሉም በመጠጥ ይታጀባሉ ከዚያ በኋላ የሚመጣውን ታውቃለህ ዝሙት፣በሽታ - ክፉ ኃጢአታ ከዚያ ካንተ መለየት ይሆናል፡፡ እስኪ የሚለጠፉ ትላልቅ ማስታወቂያዎችን ተመልከት በዚያች ሀገርም ሆነ በሌላው ዓለም የመጠጥ ማስታወቂያ፣የፋሽን እና ከሀገሪቱ ማንነት ጋር የማይሄድ ነገር ነው፡፡አንተ ታውቀዋለህ ዛሬ የዓለም ዕውቅና ለማግኘት ያንተ መሆን ሳይሆን የኔ መሆን ብቻ ነው የሚያዋጣው፡፡ ሙዚቀኞችን አይተሃቸዋል የኔ እኮ ናቸው ብዙዎች ነፍሳቸውን ለኔ ሽጠዋል፡፡ ከዚያ የሚፈልጉትን ብር፣ገንዘብ እሰጣቸዋለሁ፡፡ ገንዘብ ካገኙ ደግሞ አንተን አይፈልጉም፡፡ በቃ ምን ልበልህ የኔን ስራ እየሰሩልኝ ስለ ሆነ፣እኔ የማስበውን ሳይሆን እኔ ያላሰብኩትን ስለሚያስቡ፣እኔ ያለደረኩትን ስለሚያደርጉ ከአሁን በኋላ መጠየቅ የለብኝም ራሳቸው ይጠየቁ እንጂ፡፡ ብዙውን ለማውራት በጣም ጊዜ ያጥረኛል ምክንያቱም የፈጠርካቸው ሰዎች የሚሰሩትን ስራ፣የሚያስቡትን ሀሳብ፣የሚተገብሩትን ተግባር፣ ወዘተ ኦዲት ስለማደርግ ነው የሄደው፡፡ በፊት ስራዬን ላሰራቸው ነበር የምሄደው አሁን ግን ስራቸውን ኦዲት ለማድረግ፣ በክብር መዝገብ ለመመዝገብ፣ስራቸውን ለማድነቅ እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ስለዚህ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በእኔ ቦታ ሆነው አኔ እስከምነግርህ ድረስ እንዲሰሩ የወከልኳቸው መሆኔን አሳስባለሁ፡፡እንግዲህ ፈጣሪዬ ይህን ደብዳቤ መጻፍ የቻልኩት ስራቸው ስለሚገርመኝ ነው ባንተ ዘንድ አይደለም በሰራዊቴ ዘንድ የሚጠሉ ሰዎች የበዙበት ዘመን ነው፡፡ እንኚ የውሸት አጥማቂዎች የሚሰሩትን ትርዒት ተመልክተሃል እነዚ ሰይጣንን ወደ ሰው የሚልኩ እና የሚያስልኩ እኮ በኔ ዘንድ እንጂ በሰራዊቴ ዘንድ አይወደዱም እናም ብዙ ነገሮችን ስመለከት ይህን ደብዳቤ ለመጻፍ አነሳሳኝ፡፡ ሌላ ደብዳቤ ጽፌ ወይም በአካል በሌላ ክስ እስከሚመጣ ድረስ...፡፡
setan symbol.jpgየሀሳት አባ~
666
ሳጥናኤል ከምድረ ሲዖል

Thursday, May 12, 2016

ለምን ይሆን?

አስታውሳለሁ ብዙም ያልቆየ ነበር ባደኩበት ብዙ ብሔር ብሔረሰብ ያለበት እንዲሁም ክርስቲያን (ኦርቶዶክስ) እና እስልምና ተከባብሮ የሚኖርባት ነበረች የትውልድ አካባቢዬ፡፡ ሁሉም በፍቅር ነበር በሀዘን ጊዜም ይሁን በደስታ ጊዜ ሁሉም እግዚአብሔርን የሚፈራ ነበር፡፡ ክፋት ማሰብ የለም ወይ አብሮ መኖር! ሃይማኖታችን የተለያየ ቢሆንም ፍቅሩ ነበር፡፡ አንድ የትልቅ እድር አባል ነበርን ሁላችንም ማለቴ ከሙስሊሞች ጋር ክርስቲያን ሲሞት ይቀብራሉ ሙስሊም ሲሞቱ ሄደን እንቀብራለን ነገር ግን ያ ዛሬ የለም ለምን ይሆን? አስቡበት፡፡ይህን ያነሳሁት አሁን በሀራችን እየሆነ ወዳለው የዝናም አደጋ ለመምጣት ነው፡፡ የሆነው ከእግዚአብሔር እንደሆነ አይደለም አኛ አእምሮ ያለን ሰዎች ሌሎች ፍጥረታትም ያውቃሉ፡፡ በታሪክ እንደምናውቀው ህዝበ እስራኤል እግዚአብሔርን በበደሉ ጊዜ መቅሰፍት ያመጣባቸው ነበር ሲመለሱ ግን ይቅር ይላቸውና በበረከት ይጎበኛቸው ነበር፡፡ በሀገራችን ቢሆንስ በረከት አልነበረም ወይ? ወቅቱን የጠበቀ እንደሚዘንብስ በእድሜያችን አላየንም ወይ? ዛሬስ ያ ዬት ሄደ?ሰሞኑን በድርቅ ምክንያት ብዙ ወገኖች፣እንሰሳት አጥተናል፤ እያጣንም ነው ዛሬ ደግሞ በተለየ መልኩ በጎርፍ የብዙ ሰው፣ሀብት ንብረት፣እንሰሳት፣ሊማት እየጠፋ ነው ለምን ይሆን?ሳይንሱ የሚለውን ይላል፣የአየር መዛባት ነው፡፡ ይበለው፡፡ ለመሆኑ ለሰው ወሳኝ የሆኑ ነገሮች በሰው እጅ እንዳልገቡ እናውቃለን? ለምሳሌ አየር፣ዝናም፣ውኃ፣ነፋስ፣የፀሐይ ብርሃን እና ሙቀት፣ወዘተ:: እነዚህ በሙሉ ላይ የሰው ልጅ ስልጣን የለውም ሁሉም በእግዚብሔር እና ከእግዚአብሔር ብቻ ናቸው፡፡ በሰው እጅ ቢሆኑ ኖሮማ የሰው ልጅ ለአንድ ደቂቃ እንካን ባልተረፈ ነበር፡፡እግዚአብሔርም ይህንን አውቆ በሰው እጅ እንዲገቡ አላደረገም፡፡ እሱ በፈቀደ ጊዜ ብቻ ያደርጋቸዋል፤ለመዓትም ለመህረትም ይጠቀምባችሃል ይሆናሉም አንድም ቀን ከተሰጣቸው ትእዛዝ ዝንፍ ብለው አያውቁም፡፡ ሰውስ?በዘመናችን እግዚአብሔርን መፍራት ይኖር ይሆን? ከመከፋፈል ውጪ ተባብሮ ማደግን፣ ሀገርን ማሳደግ፣በፍቅር መኖር፣ለሀገር መቆም አለን? እውነት ዛሬ ለሀገር የሚቆም ሰው ይኖር ይሆን? ሙስና ለምን በዛ? መተማመኑስ ለምን ጠፋ? መለያየት ለምን ሰፈነ?ነው፡፡እዚህ ላይ መጋቤ ሐዲስ እሴቱ የተናገሩት ነበር ስለ አሁኑ ሰው ‹‹እግዚአብሔር ጦርነት አያምጣና ዛሬ ጦርነት ቢሆን ዘራፍ ብሎ የሚነሳ ሰው ያለ አይመስለኝም›› እንዲሁም አክለው ‹‹ዛሬ ኢትዮጵያ ቲሸጥ ቢባል ስንት ታወጣለች ብሎ ያስባል እንጂ ለምን ትሸጣለች ብሎ አያስብም›› ብለዋል፡፡  ምክንያቱም የእግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ስለ ሌለ ምክንያቱም ቅዱስ ዳዊት ‹‹እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው እንዲ ይባረካል›› መዝ. 128፡4 ይላል፡፡ በረከት ደግሞ የሰማይ እና የምድር ነው፡፡ ዝናም በረከት ነው፣ሰላም በረከት ነው፣ፍቅር በረካት ነው... እግዚአብሔርን ካልፈራን ግን ለበረከት የተፈጠሩ ለጥፋት ይታዘዙብናል ልክ እንደ ኖኅ ዘመን ውኃ፡፡አንድ ታሪክ ነው የሚነግራችሁ የዛሬ 15 ዓመት ያኔ መጀመሪያ ላይ የጠቀስካቸው በእምነት የሚለያዩ ሰዎች በፍቅር በሚኖሩበት ጊዜ በአንድ ወቅት ዝናም ጠፋ ድርቅ ሆነ ይገርማል ሁሉም በሃይማኖት በብሔር ሳይለያይ ቤተክርስቲያን ተሰባሰቡ (ሁሉም የአንድ እድር አባል ስለ ነበሩ - ቅድስት ማርያም እድር) ወደ ፈጣሪያቸው ለመኑ፡፡ ማታ ወደ ቤታቸው ሲመጡ የፈለጉት ዝናም በሚፈልጉት ጊዜ በሚፈልጉት መጠን ዘነመላቸው፡፡ ዛሬስ እውነት ይህ አለ? በዚህ ሁኔታ እያሉ ነበር በሰው አእምሮ ፍልስፍና ገባ ይህም በዓላትን መሻር፡፡ ቅዱስ ዳዊት እንዳለ ‹‹አንድ ሆነው በልባቸው በየሕዝባቸው፡፡ ኑ የእግዚአብሔርን በዓሎች ከምድር እንሻር አሉ›› መዝ. 74፡8 የኛዎቹም ማለት ጀመሩ፡፡ በፊት ቅዳሜ እና አሁድ፣ የእመቤታችን ዕለት፣የቅዱስ ሚካኤል ቀን እና የበዓለ ወልድ በትክክል ያከብሩ ነበርና፡፡ ከዚያ ወዲህ ግን በቅዳሜ እና እሁድ ማረስ፣ማጨድ፣መቆፈር ጀመሩ የተስማሙበትን አፈረሱ ከእድሩም ሙስሊሞች ተለዩ ክርስቲያኑም የእድር ዕለት ዳቦ እና ጠላ ለመጠጣት ይሄዳል እንጂ ቀኑን የእሜታችንን አያከብርም፡፡ ከዚህ ቀኖች ውጪ ባሉ ቀናት በመጠጥ ቤቱ እየዞረ፣እየተደባደቡ መገዳደል በዛ፣ሰው ሰውን ገድሎ የማያውቅባት ሀገር በየቀኑ፣በየሳምንቱ መሬት የሰውን ደም መጠጣት ጀመረች፤የሰው ደም መጠጣት ስትጀምር ዝናም ተለያት፣በረከት ተለያት፣ጊዜን ያልጠበቀ ዝናም ያስቸግራት ጀመር፣ያልታሰበ ድርቅ ይመታት ጀመር፣ገበሬው በሰራው ስራ መተማመኑ ጠፋ፣ከእግዚአብሔር ይልቅ ሳይንስ ላይ መደገፍ ጀመረ - የሚለውን ሞከረ ግን በመቅሰፍት ቀን አላዳነውም፡፡ እግዚአብሔር ‹‹ያለኔ ምንም ልታደረጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል›› ዮሐ. 15፡5 ይል የለም ወይ?ዛሬስ ምክንያቱስ ምን ይሆን እንደዚህ የሆነው? ሰሞኑን ስለ ድርቅ ስናወራ ዛሬ ደግሞ በወላይታ የመሬት ናዳ፣በባሌ እና በሌሎች ያልተጠበቀ ጎርፍ መከሰቱ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር እንመለስ፡፡ በክህደት መንገድ ያለን ወደ እምነት፣ለሱስ የተገዛን ከባርነት እንውጣ፣ ዘረኝነት በሽታ የተያዝን እንታከም ያን ጊዜ ምህራት፣ቸርነት፣ሰላም፣ፍቅር፣በረከት ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‹‹ሁላችሁ እናንተ ከክፉ መንገዳችሁና ከሥራችሁ ክፋት ተመለሱ፤እግዚአብሔርም ከዘላለም ወደ ዘላለም ለእናንተና ለአባቶቻችሁ በሳጣችሁ ምድር ተቀመጡ›› ት.ኤር. 25፡5፡፡ እኛም ወደ አባቶቻችን መንገድ እንመለስ፡፡