በእንተ ርእስየ

Friday, October 27, 2017

ሕይወተ ወራዙት ክፍል 13/17- በአማርኛ



ክፍል አስራ ሦስት
ምዕራፍ ሰባት
መዝናናት እና መደሰት
መጽሐፍ ቅዱስ መዝናናት እና መደሰትን አይቃወምም፡፡ ዋናው ነገር መዝናናት እና መደሰት በምን መልኩ የሚለው ነው፡፡በአግባቡ መዝናናት እና መጫወት ከመንፈሳዊነት አንጻር ባይነቀፍም ነገር ግን ይህን ባያደርጉ የሚመከሩና ቢያደርጉ የሚገሠጹ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ካህናት፣ መነኮሳት፣ ሽማግሌዎችና ባልቴቶች ወዘተ ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ ሌሎች ግን በልክ እና በመልክ መዝናናትና መጫወት ይኖርባቸዋል፡፡ (ተግ.ዘዮሐ.አፈ. 7) ወጣቶች በልክ መዝናናት ተገቢ ነገር ቢሆንም ጫወታና ቀልድን ማዘወተር መልካም አይደለም፡፡ ‹‹ጫወታና ተድላ ደስታን ዘወትር የሚያደርግ ሰው በሥጋውም በነፍሱም ዘማዊ ነው›› (አረ.መን.ድር.1) እንዲሁም 2ጢሞ. 3፡4 ‹‹ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ›› የሚለውን የእግዚአብሔርን ፈጻሚ መሆንም አለ፡፡
እውነተኛ ደስታ ግን የመንፈስ ፍሬ ነው፤ ከመንፈስ ቅዱስ የሚገኝ ነው እንጂ ከሥጋ ጫወታ አይደለም፡፡ያዕ. 5፡13 ‹‹ደስ የሚለውም ማንም ቢኖር እርሱ ይዘምር›› መዝፈን አይገባም፡፡ ፊል. 4፡4 ላይም ‹‹በጌታ ደስ ይበላችሁ፡፡›› ማለቱ እውነተኛ ደስታ ከእግዚአብሔር እና ከእግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ከየትኛውም ዓይነት መዝናኛ በላይ ነገረ እግዚአብሔርን መጫወት እንዲሁም መዘመር እና መጸለይ የበለጠ ያዝናናል፡፡ ዘዳ. 11፡18-19 ልጆች የእግዚአብሔር ቃል አንዲጫወቱ የማስተማር የወለጆች ኃላፊነት ነው፡፡ 2ሳሙ. 6፡22 ያንብቡ፡፡
ሌሎች መዝናኛዎች
ጉብኝት፡- መዝናናት ከተቻለና ካስፈለገ ታሪካዊ ቦታዎችን እየተዘዋወሩ መጎብኘት ቀዳሚውን ስፍራ ሊይዝ ይችላል፡፡ ለሌላ ገንዘቦችንና ጊዜያችንን ከምናጠፋ የተለያዩ ቅዱሳን ቦታዎች እየሄዱ መዝናናት ይመረጣል፡፡ ምክንያቱም ከሥጋ ደስታ ይልቅ የነፍስ ደስታ ይገኛልና፡፡ ሐዋ. 8፡27-40 ላይ የኢትዮጵያ ጃንደረባ ያደረገውን ጉዞ ማስተዋል እና መለማመድ መልካም ነው፡፡ ወደ ታሪካዊ እና የበረከት ቦታዎች በደመ ነፍስ መጓዝ ሳይሆን መጀመሪያ ያለፈጣሪ ረድኤት እና ፈቃድ እንደማይቻል ማመን ያስፈልጋል፡፡ ዮሐ. 10፡40-42፡፡ ዛሬ በሀገራችን ብዙ የጉዞ ማስታወቂያዎች ተለጥፈው ታገኛላችሁ ነገር ግን የመጀመሪያ ዓለማቸው ይዘው ከሚሄዱት ሰዎች ገንዘብ ለመሰብሰብ አቅደው እንጂ ለሕዝቡ ብቻ ታስበው እንዳልሆነ የሚሄደው ሕዝብም መሠረታዊውን የገዳማት እና የአድባራትን ሥርዓት ጠብቀው ሳይሆን ለመዝናኛ ብቻ አስበው እንደሆነ ባሁኑ ጊዜ በቦታው ያለው የሥርዓት ጠፍቶ ማግኘታችን ለዚህ አማላካች ነው፡፡ እኛ ግን ወደ እነዚህ ቦታዎች ስንሄድ መጀመሪያ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንጠይቅ፤ ሰው ስለሄደ ብቻ አንሂድ ካልሆነ ለበረከት ሄደን መርገምን ይዘን እንመለሳለን፡፡
ድራማ፡- አስመስሎ መስራት፣ ማድረግ ነው፡፡ ለማዝናናት፣ ለማስተማር፣ ለተወሰነ ዓላማ ለማነሣሣት፣ ለማሳመንና እንዲሁም በሰው ላይ ስጋት ለማሳደር ሊሠራ ይችላል፡፡
(ሀ) መንፈሳዊ ተውኔት (ድራማ)፡- በሰንበት ትምህርት ቤቶች አካባቢ መንፈሳዊ መልእክቶችን በተውኔት መልክ ማስተላለፍ በስፋት የተለመደ ነው፡፡ ጥንቃቄ ግን ያስፈልጋል፡፡ ለማስተማር እንጂ ለፌዝ እና ሰዎችን ለማዝናናት መሆን የለበትም፡፡ ማዝናናት፣ ማሳቅና ማጫወት የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ አይደለምና፡፡ አሁን አሁን ግን መሠረታዊውን የወንጌል ትምህርት የተጋፋ ሆኗል፡፡ የወንጌል ሰዓት ተቀንሶ በተውኔት እስከመመደብ ወይም ትምህርቱን ጨርሶ እስከማስታጎል ይዘልቃል፡፡ ከትምህርተ ወንጌል በኋላ አንድ ተውኔት ዝግጅት የሚቀርብ ከሆነ አቅራቢዎቹ ቁጭ ብለው አይማሩም፤ታዳሚዎቹም እንዲሁ፡፡ በሰንበት ትምህርት ቤት መድረክ ላይ ከአዝናኝነቱ ይልቅ አስተማሪነቱ የሚያመዝን መሆን አለበት፡፡ የሚያስቅ መሆን የለበትም፡፡
ወጣቶች መንፈሳዊ ድራማ ሲሰሩ ማሳዘንም ዓይነት ሊኖረው ይገባል፡፡ መንፈሳዊ ተውኔት የሚጽፉ ሁሉ ነገረ ሃይማኖትና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በሚገባ የተማሩና ቋንቋና ዘይቤውን በሚገባ የተረዱ መሆን አለባቸው፡፡የዓለምን ነገር እንዳለ አምጥቶ የቤተ ክርስቲያን አውደ ምሕረት ላይ ማውጣት አይቻልም፡፡ የመናፍቃንን ትምህርት ያሳየን መስሎን በቤተ ክርስቲያን መድረክ ላይ ኑፋቄና ዘለፋ ማቅረብ አያስፈልግም፡፡ የመንፈሳዊ ተውኔት መመዘኛው መጽሐፍ ቅዱስ መሆን አለበት፡፡ ወጣቶችም በዚህ ዓይነት መርሐግብር ሲሳተፉ ጥንቃቄ አድርገው ካልቀረቡ መንፈሳዊ ስራ ሰራን እያሉ መቀሰፍ እንዳይሆን፡፡
(ለ) ዓለማዊ ተውኔት (ድራማ)፡-አንድ ሰው ተውኔትን እመለከታለሁ ካለ መራጭና አስተዋይ መሆን ይኖርበታል፡፡ ክርስቲያን የሆነ ተዋናይ ሃይማኖቱን የሚጻረር ገጸ ባሕርይ ተላብሶ መጫወት የለበትም፡፡ ሲጋራ በማጨስ፣ ጫት በመቃም፣ በመዳራትና በአደባባይ በመሳሳም ለመተወን መድፈር አይገባም፡፡ ከከርስቲያን የሚጠበቀው ክርስቲያን መሆን ብቻ አይደለም፡፡ ለክርስቲያን የታዘዘውን በሙሉ ሳናጓድል መፈጸምና የሚቻለንን አግልግሎት መስጠት ስንችል ነው፡፡ክፉ ክፉ ገጸ ባሕርይ ተላብሶ በመተወን ክፉ ሰው መሆን ብቻ ሳይሆን መምሰልም ያስጠይቃል፡፡ ሮሜ. 12፡2 ‹‹ይህን ዓለም አትምሰሉ0›› ይላልና፡፡ ክፉ ሆነህ በተደጋጋሚ ከሰራህ ያንተ ማንነት ወደ መሆን ሊለወጥ ይችላል፡፡ በኮምፒዩተር ቅንብር የሠራኸው ትወና አንተን ባይጎዳም ተመልካቹን ጎድቷል፡፡ ይህ ደግሞ ራስ ወዳድነት ነው፡፡ ከቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አስተምህሮ ጋር የማይጋጩና ከሃይማኖት ጋር የማይጻረሩ ተውኔቶችን እየመረጡ መስራት ኃጢአት አይደለም፡፡ ነገር ግን ዛሬ ወዴት እያመራ ነው እናስታውል፡፡
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መልካም ነገር ነው፡፡ የአካል ቅልጥፍና እንዲኖረን፣ ሰውነታችን እንደልብ እንዲታዘዝል ለማድረግ ጡንቻችን ብርታትና ጥንካሬያችን እንዲዳብር ይረዳል፡፡ በርግጥ ጤናን የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው፡፡ 1ጢሞ. 4፡8፣ 2ጢሞ. 4፡3 ላይ ‹‹ሰውነትን ለሥጋዊ ነገር ማስለመድ ለጥቂት ይጠቅማልና እግዚአብሔር መምሰል ግን የአሁኑና የሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው ነገር ሁሉ ይጠቅማል፡፡›› ዛሬ ዛሬ የአብዛኛዎች ስፖርታዊ ውድድሮች የደስታ መንፈስና መዝናኛነት እየተቀየረ በአመዛኙ የገንዘብ ምንጭነታቸው እየጎላ መጥቷል፡፡ ይበልጥ የሚያስደስተው ተመልካቹን ነው፡፡ ለዚህም ብዙ ወጣቶች ቆስለዋል፣ ጥርሳቸው ረግፏል፣ አጥንታቸው ተስብሯል፣ ጥቂት የማይባሉ ሞተዋል፡፡
ስፖርት ከራሳቸው ድክመት ጋራ ተደምሮ ከጾም፣ ከጸሎትና በሚገባ ለፈጣሪ ከመገዛት እንዲለዩ ምክንያት የሚሆንባቸው ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ በበጎ ጎኑ ከመጠጥ፣ ከጫት፣ ከስጋራና ዝሙት ከመሳሰሉት እንድንቆጠብ እንደሚያደርግ ሁሉ ለዝሙት ለትዕቢትና ለኩራት የሚያጋልጥበት ሁኔታም አለ፡፡ ‹‹ከንቱ ውዳሴን ዝሙት ይላካታል፤ ያገለግላታልና›› ይላል ማር. አን.ቀዳ. ምዕ. 4፡፡
ብረት የሚያነሡ ወጣቶች እንደ አካላቸው አንዲሁ ልባቸው እንደይደነድን መጠንቀቅ አለባቸው፡፡ ማን ይችለኛል! እያሉ በትዕቢት የሚነፉ ከሆነ ለሠይጣን እንደተገዙ እንኳን አያስተውሉም፡፡
በስፖርት ስም ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት እና ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ ከሚቀሩ ስፖርቱ ራሱ ቢቀር ይሻላል፡፡ ስፖርተኛ ሆነህ ትሕትና፣ ንጽሕና መልካም አስተሳሰብ ከምታጣ ስፖርተኝነት ቢቀር ይሻላል፡፡ የስፖርት አፍቃሪያን (ተመልካቾች) ደግሞ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ ለስፖርት ብለው ትምህርት፣ ስራን ቸል የሚሉ በስተዋል፡፡ ለመሆኑ ሳይሰሩ መብላት አለ እንዴ? ትምህርትን በስርዓቱ ሳይማሩ የሚፈልጉት ደረጃ አለ እንዴ? ለዚህ አይመስላችሁም ኩረጃ የበዛው፡፡ መኮረጅ ደግሞ ኃጢአት ነው፤ አትስረቅ፣ የባልንጀራህን ቤት አትመኝ የሚሉ ሕጎች አሉና፡፡ ሌሎች ደግሞ ለስፖርቱ ብለው የሚናደድ፣ ቁማር የሚጫወቱ፣ ብዙ መዋዕለ ንዋይ የሚያፈሱ ብዙ ናቸው፡፡
አጭር ምከር፡- ውድ ወጣት ስፖርት ለምን እንደምትሰራ በትክክል ንገረኝ! ለጤና ወይስ ጡንቻህን እና ደረትህን ነፍተህ በሰው መሀል ለመሄድ ወይስ ለምን? ብረት በማንሳት ባሳበጥከው ደረትህ አንድ ኃጢአት በየቀኑ እየሰራ እንደሆነ ታውቃለህ? (ርቱዓ ሃይማኖት አንብብ):: የተነፋው ደረትህን እያዩ በዝሙት የሚወድቁ ሴቶች እንዳሉ አስበህ ታውቃለህ?
ለመሆኑ የትኛው ስፖርት ዓይነት ደጋፊ ነህ እውነት በስፖርቱ መርሐግብር ነው ወይስ በራስህ መርሐግብር ነው የምትመራው? ግን ምን ተጠቀምክ? እዚያ ያጠፋሀቸውን ሰዓቶችስ፣ ከዚያ ወጥተህ ደግሞ ስለ ጫወታው ለማውራት ያጠፋኸውን ሰዓት አስብ፣ ምናለበት ያንን ዓለማዊ ትምህርት አንብበህበት እንደ ቅጣው እጅጉ ሀገር ብታስጠራበት፣ የቤተ ክርስቲያንን ችግር ብትደፍን፣ የብዙ ስፖርተኞችን ስም ከነ ክለባቸው፣ ደሞዛቸው፣ እድሜያቸው ማወቅን እንደ እውቀት ከምትቆጥር በሀገርህ ያሉ ቅዱሳንን ብታውቅ ምን አለበት? ይህ የሰይጣን ሴራ ነውን ተወው፡፡

No comments:

Post a Comment