ክፍል አስራ አንድ
ምዕራፍ ስድስት
ትውዝፍት (የምንዝር ጌጥ)
እግዚአብሔር የሰው ልጆች እንዲታረዙ አይፈልግም፡፡ ዘፍ. 3፡21 ‹‹የቁርበት ልብስ አለበሳቸው፡፡››፡፡ በልብስ የሚጠቀመው
ሥጋ ቢሆንም የልብስ አስፈላጊነቱ ግን ለነፍስ ነው፡፡ አንድ ሰው ነፍሱ ስትለየው አያፍርም፣ አይለብስምና፡፡ ጌታችን ለምትለብሱት
አትጨነቁ ብሏል ብዙዎቻችን ግን የምንጨነቀው የምንለብሰውን አጥተን ሳይሆን መምረጥ አቅቶን ነው፡፡ ለዚህ እኮ ነው ዛሬ ዓለም የትውልዱን
ስነ ልቡና ስለተረዳች በየጊዜ ፋሽኖችን የሚትለቅብን፡፡እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ልብሳቸው ሳያልቅ 40 ዓመት እንደመራቸው ለሌለው
መስጠት ይቻለዋል፡፡ ማቴ. 6፡28 መዝ. 22፡1፣ 1ጢሞ. 6፡8፡፡ የሰው ነፍስ ስለ አለባበስ በቂ ግንዛቤ አላት፡፡ አዳምና ሔዋን
ጸጋቸው በተገፈፈ ጊዜ ‹‹የበለስ ቅጠሎችን ቆርጠው ለእነርሱ ለራሳቸው ግልድም አደረጉ›› ዘፍ. 3፡7፡፡ እንዲሁም ነፍስ ልብስ
አስፈላጊ መሆኑን ብቻ ሳይሆን መልበስ ያለብንን የልብስ ዓይነትና በዋናነት መሸፈን የሚገባውን የአካል ክፍል ለይታ ማወቋ ነው፡፡
አዳምና ሔዋን እንሰሳትን አይተው እንደነሱ መልበስ የለብንም አላሉም ይልቅ ለራሳቸው አገለደሙ እንጂ፡፡ የሚገርመው ደግሞ
ሌሎች ዕፀዋት እያሉ በለስን መምረጣቸው ሳያንስ ያን ሰፍተው ማገልደማቸው ነው፡፡ የበለስ ቅጠል ሰፋፊ ነው በዚያ ላይ ደግሞ ተሰፍቶ፡፡
ብርድ ለመከላከል ብቻ አልነበረም፡፡ ቢሆን ኖሮ ሌላ አካላቸውን ጨምረው ባለበሱት ነበር፡፡ አዳምና ሔዋን ማገልደማቸው ብቻ በቂ
ባለመሆኑ እግዚአብሔር የቁርበት ልብስ አለበሳቸው ‹‹ግልድም ሰጣቸው›› አይልም፡፡ ዘፍ. 3፡21፡፡ ዛሬስ ምን ዓይነት ልብስ ነው
የለበስነው?
ከአዳምና ሔዋን ምን ዓይነት ልብስ መልበስ እንዳለብን እንረዳለን፡፡ ዛሬ ግን ብዙ ሴቶች ስሜታቸውን እንጂ የነፍሳቸውን
ፈቃድ አይከተሉም፡፡ለዚህ ማሳያው ነፍስ መሆን ያለበትን መጠቆሟን፣ መንፈስ ቅዱስም በማይገባ ልብስ ስንሸለም መውቀሱን ይታወቅ ዘንድ
ሲያፍሩ፣ አጠር ብለው የለበሱትን ሲጎትቱና ወይም በልዩ ልዩ ዘዴ የተራቆተውን የሰውነት ክፍል ለመሸፈን ሲሞክሩ ይታያሉ፡፡ በተለያዩ
የዓለም መድረኮች ዛሬ አልፎ አልፎ በቤተ ክርስቲያናችንም በስርዓቱ ሰውነት ላይ የማይቀመጠውን ልብስ እየለበሱ አስር ጊዜ እያስተካከሉ
የሰውን ሕሊና የሚሰርቁ ብዙ ናቸው፡፡ በዚህ ውስጥ ሰይጣን ብዙ ስራ ይሰራል የወጣቱን ትኩረት በመሳብ በዝሙት ፈቃድ እንዲወድቅ፣
በሰዓቱ የቆመበትን ዓላማ እንድዘነጋ ማድረግ፣ እሷ ደግሞ ለሌሎች ውድቀት ምክንያት እንድትሆን በማድረግ በአንድ ጊዜ ሁሉንም ይጥላል፡፡
ምክንያቱም ሰይጣን ድንጋይ ሲወረውር ከመታ በኋላ ተመልሶ ደግሞ ሌላውንም ሰው እንዲመታ ማድረግ ጥበቡ ነው፡፡ ዛሬ አጫጭርን ነጠላን
አስተውሉ፣ የቤተ ክርስቲያናችን አኮ አልነበሩም፤ የኛማ ረጅም፣ ወፍራም ሰውነት ያማያሳይ ነበር፡፡ የአሁኖቹ ደግሞ የሴቶችን ዳሌ
እና እራቁት የሚያሳዩ ወንዶችን ለፍትወት የሚያነሳሱ ናቸው፡፡ ለመሆኑ አስተውለን እናውቃለን? ይህ ክርስቲያኖችን ሕገ ወጥ ለማድረግ
የተሠራ የዓለም ሴራ ነውና እንወቅበት፡፡ እንደ ነጠላው ሌሎችንም አለባበስ እናስተውል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ሴቶች ክርስቲያኖች
ከፀጉራቸው ጀምሮ እስክ እግራቸው ድረስ ስለሚሸፋፈኑ የዓይን ዝሙት ለተጠናወታቸው ሰዎች ምቹ አይደለም፡፡ይህ አካላቸው እንዲጋለጥ
ቀጭን ነጠላ፣ የሰውነት ቅርጻቸው እንዲታይ ደግሞ የሚያጣብቅ ቲሸርት እና ሱሪ እንዲለብሱ የዓለም የዘወትር ተግባሯ ነው፡፡ እኛስ?
ለወንዶችም ሠለስቱ ምዕት በሃይማኖተ አበው ‹‹አለባበስህ በጥንቃቄ ይሁን፡፡››በማለት አዘዋል፡፡ የኖኅ መራቆት የልጅ
ልጁን ከነዓንን ለእርግማን ዳርጓል፡፡ ዘፍ. 8፡22፣ የቤርሳቤህ ከልብስ መረቆት ራሷንና ዳዊትን ለዝሙት ዳርጓል፡፡ በዘዳ.22፡5
ላይ ‹‹ወንድ የሴትን ልብስ አይልበስ ይህን የሚያደርግ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነውና፡፡››
ልብስ የጸጋ እና የክብር ምሳሌ ነው፡፡ አዳምና ሔዋንም የእግዚአብሔር ክብር እንደራቃቸው ያወቁት ልብሳቸው (የጸጋ ልብስ)
በመገፈፉ ነው፡፡ ልብስ የክብር ምልክት ነው፡፡ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን የሚገኙ ንዋያተ ቅድሳትንና ምስጢራትን በሙሉ በማኅፈዳት እና
በመንጦላዕት (በመጋረጃ) በመሸፈን እናከብራቸዋለን፡፡
የሚገባ ልብስ
በ1ጢሞ. 2፡10 ‹‹ሴቶች በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራስን ከመግዛት ጋር ሰውነታቸውን ይሸልሙ›› ይላል፡፡ የማይገባ
ልብስ ማለት አካልን ለእይታ የሚያጋልጥ ፀረ ክርስትና መልእክት ያለው ልብስ ሁሉ ነው፡፡ በላዩ ላይ የዝሙት መልእክት ያለው ሥዕልና
ጽሑፍ ያዘለ ከሆነ፣ ስስና ዘርዛራ ወይም ከገላ ጋር የሚጣበቅ ሆኖ ገላን የሚያሳይና ቅርጽን የሚያወጣ ከሆነ፡፡ በተለይ ባሁኑ ጊዜ
የአውሬው ምልክት እና መልእክቶች በሰፊው ልብሶች ላይ እየታተመ የሚወጣበት ጊዜ ላይ ስለሆን ፋሽን ከመከተል የኛን ማንነት የሚገልጸውን
ልብስ ዓይነት መልበሱ የተሻለ ነው፡፡
የማይገባ አለባበስ የሚባለው የሴቶች ሱሪ መልበስ ብቻ አይደለም፡፡ ቀሚስም የማይገባ ልብስ ሆኖ የሚይገኝበት ብዙ መንገድ
አለ፡፡ ለምሣሌ እጅግ ቢያጥር፣ ተሰንጥቆና ሳስቶ ሰውነትን ለእይታ ካጋለጠ የማይገባ ነው፡፡ አንዲት ልጃ ገረድ ለአቅመ ሔዋን ስትደርስ
በሰውነቷ ላይ የሚታይ ለውጥ ለአቅመ አዳም የደረሱ ወጣቶችን በኃይል የሚማርክ ይሆናል፡፡ ከወሊድ ጋር ተዛምዶ ያላቸውን የሰውነትሽን
ክፍሎች ለማሳየት ቁምጣና አጣብቂኝ የሆኑ ጉርድ ቀሚሶችን፣አጭር ቀሚስና ጠባብ ሹራቦችን፣ ስስና ዘርዛራ ልብስ፣ ጠባቃ ሱሪ መልበስ
ለምንዝር ጌጥ መጋለጥ ነው፡፡ በዚህ ከቀጠለ ደግሞ የተቃራኒ ጾታዎችን ፍትወተ ሥጋ የመቀስቀስ ሚና ይጫወታል፡፡ ለማሸነፍ ደግሞ
ምን ያህል በቁ ነሽ? አለባበስሽን አይቶ የመጣ ወንድ ደግሞ ከዝሙት በቀር ባልሽ ሊሆን አይችልም፡፡ስለዚህ አለባበስሽ ለምንዝር
ሆነ ማለት ነው፡፡
ባሎች የሚስቶቻቸውን አለባበስ በጥንቃቄ ይከታተላሉና ሚስቶች ሊጠነቀቁ ይገባል፡፡ምክንያቱም ባሎች ሌሎች ወንዶች ሚስቶቻቸውን
በዝሙት ዓይነት እንድመለከቷቸው አይፈልጉም፡፡ ያን ጊዜ በልቡ ይጠርጥርሻል ከዚያ ከእሱ የምታገኚውን ተድላ ታጫለሽ፣ትነቀፊያለሽ፣
ከባልሽም ተለይተሸ ትሄጃለሽ (ቅ/ዮሐንስ አፈወርቅ)፡፡
አንዳንድ ሴቶች ደግሞ ባላቸው ወደ ውጭ ውጭ እንዳይልባቸው ልብሰ ዘማ ይለብሳሉ፡፡ ይህ ግን ባልን የበለጠ ሴሰኛ ማድረግ
ነው፡፡ የተለበሱ ልብሶችን እያየ ከሚስቱ ጋር ወሲብ የሚፈጽም ባል ነገ ደግሞ ከሚስቱ አስበልጣ የምታጌጥ ሴት ካየ ሚስቱን ትቶ
መሄዱ አይቀሬ ነው፡፡ ይልቅ እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ማስተዋሉ ይሻላሉ፡፡ 1ጴጥ. 3፡1-6፡፡ እንዲሁም ‹‹ባልሽ ሴሰኛ
ከሆነ ግን ምንም በጌጦች ዓይነት ሁሉ ብታጌጪ ካንቺ ወደ ሌላ መሄዱ አይቀርም›› (ተግ.ዘዮሐ. 28)፡፡
ከወሊድ ጋር ተዛምዶ ያላቸውን አካላት የሚያጋልጥ ለብሶ ወደ ገበያ እና ሥራ ቦታ መሄድ ምን ለመሆን ነው? ለሥራ ነው
ካልን ለሥራም አይመችም በተለይ ለክርስቲያን የሚያሳፍር ነው፡፡ ከቤት ለአንድ ዓላማ ቢወጡም እግረ መንገድሽ ቤተ ክርስቲያን ሆነ
ሌላ ቦታ መድረስ ያስፈልግ ይሆናል፡፡ እንዲሁም በመኪና መሄድ አለ፣ ቢሮ ውስጥ መስራት አለ፣ አጎንብሶ የወደቀን ማንሳት አለ፣
ልብስ ማጠብ አለ፣ ወዘተ፡፡
ዘመኑ ከሚያመጣው ፋሽን ጋር ለመሄድ ተብሎ ራስን ለአደጋ ማጋለጥ አያስፈልግም፡፡ ለኩራት ብለው የሚለብሱ ደግሞ አሉ፡፡
‹‹ልብስ በሌላቸው ላይ ልትመኩ፣ በፈታቸው ልትታበዩ፣ ልቡናቸውን በቅንአት እንደ ሰም ልታቀልጡ፣ ሰውነታቸውን በቅንአት ልታሳምሙና
በኃዘናቸው ላይ ኃዘን ልታመጡባቸው እንጂ በሌላ ምክንያት አይደለም፡፡›› (ቅ/ዮሐንስ አፈወርቅ)፡፡
አለባበስ ስለ አንድ ሰው ማንነት ይናገራል
ውጫዊ ቁመና ከውስጥ ምን ዓይነት ሰው እንደሆኑ መቶ በመቶ ባያስረዳም የቀረበ ግምት ለመስጠት ይረዳል፡፡ ሴቶች እያደጉ
ሲመጡ ስለ ልብስ አመራረጥ፣ ስለ ፀጉር አያያዝ፣ በውስጣቸው ምን ዓይነት ሰው እንደሆኑ ይለያሉ፡፡በነገ. 1፡2-6 ንጉሥ አካዝያስ
መልእክተኞቹን ወደ ኤልያስ ልኮ የለበሰውን ልብስ ሲነግሩት ንጉሡ ኤልያስ መሆኑን አውቆ ነበር፡፡ የይሁዳ ምራት ትዕማርም አማቷ
ይሁዳ በዚያ መንገድ ሲያልፍ በለበሰችሁ ልብስ ጋለሞታ መሰለችው፡፡ (ዘፍ. 38፡13-15)፡፡እህቶች እና እናቶች ለብሳችሁ ያላችሁት
ልብስ ለመሆኑ ምን እንዳስመሰላችሁ ለራሳችሁ መልሱ፡፡ ዘማ? አሮጊቷን ወጣት?የውጭ ሰው?...
አጭር ምክር፡- የለበሳችሁት ልብስ ትክክል መሆኑን ለማወቅ ይህን ጥያቄ ጠይቁ፡፡ እኔ የለበስኩት ልብስ እግዚአብሔር ይደሰትበታል?
ለምን ዓላማ ነው የለበስኩት? የክርስቲያን ልብስ ነው? ሰዎች ይህን ለብሼ ስያዩ ምን ይሰማቸዋል? ስለ ለበስሽው ልብስ ሕሊናሽ
ምን አለ? በለበስሽው ልብስ ድንግል ማርያም ትደሰት ይሆን? ወዘተ ጠይቂና መልስ ስጪ፡፡ ከዚያ ነፍስሽ የነገረችሽን ተግብሪ፡፡
መልስ ከከበደሽ ደግሞ ጹሚ፣ ጸልዪ፣ ስገጂ፣ ከቻልሽ ደግሞ ወደ ገዳማት ሂጂና ከስፍራው እና ከቅዱሳን በረከት ቅመሺ ያን ጊዜ የምንዝር
ጌጥ በሽታ ለቆሽ ይሄዳል፡፡ በመጨረሻም ልብስ መቀያየርሽ በሰዎች ለመወደድ አይሁን በተለይ በወንዶች፤ በመልካም ስራሽ ይውደዱሽ
እንጂ በልብስሽ አይሁን፡፡ በልብስሽ የወደዱሽ ለዝሙት ካልሆነ በቀር ሚስታቸው እንድትሆኚ አይፈልጉም...፡፡
No comments:
Post a Comment