እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር ሁለት
ጠባይ እንዲኖረው አድርጎ ነው ይህም እንሰሳዊ እና መልአካዊ፡፡ እንደ እንሰሳ ይበላል፣ ይጠጣል፣ ይተኛል፣ ይሞታል ወዘተ፡፡ እንደ
መልአክ ደግሞ ሕያው ነው፣ ያመሰግናል፣ ይነቃል፣ ባአጠቃላይ የነፍስን ፈቃድ እየተከተለ እግዚአብሔርን እንዴት እንደሚያስደስት
ያስባል ያደርጋልም፡፡ ነገር ግን የሰው ልጅ አብዛኛውን ጊዜ ስለ ስጋው ሲያስብ ይኖራል፣ ማለትም ስለ ሆዱ ማለት ነው፡፡ በዓለም
ላይ ብዙዎቻችን የምንዳክረው ስለ ሆዳችን ነው፡፡ ነገር ግን ከክርስቶስ ልበልጥብን አይገባም ምክንያቱም የዕለት ምግብ የሚሰጥ ራሱ
አምላካችን ነውና፡፡
ባሁኑ ጊዜ ግን በስመ ክርስቶስ ወይም በስመ ማኅበር ለገዛ ሆዳቸው
የሚሮጡ፣ የሚኖሩ፣የሚማሩ፣ የሚያገለግሉ፣ አንድ ክርስቲያን ያደርጋል ተብሎ የሚታሰበውን በሙሉ የሚያደርጉ እየመሰሉ ለገዛ ሆዳቸው
የሚመላለሱ እየጨመሩ መጥተዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለጊዜው የተናገረው ስለ ሐሰተኞች ነቢያት ማለት ስለ መናፍቃን ነበር ምክንያቱም
ጌታችን በስሜ ይመጣሉ እንዳለው ሁሉ ዓላማቸው ስለ ክርስቶስ ሳይሆን ለገዛ ሆዳቸው ነው እንጂ መስቀል ላይ የተከፈለውን የክርስቶስን
ዋጋ የሚሰብኩ አይደለም፤ ዓላማቸው ሆዳቸውን መሙላት ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ራሳቸውን ለለዩ ለመናፍቃን ነው፡፡ እኔ መጻፍ የፈለኩት
ግን ከውስጥ ሆነው ለክርስቶስ ወንጌል ጠላት የሆነውን፣ የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት እየጣሰ ያለውን የውስጥ ሆድ አደርን ነው፡፡
ሆድ አደር! ስለ ክርስቶስ የሚሰብክ ይመስላል ነገር ግን ዓላማቸው ገንዘብ ማግኘት ነው፡፡ ገና ስጀመር የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት
የተማሩትም ለገንዘብ፣ ወይም በልማድ ይሆናል፡፡ በእንዲህ ዓይነት የተማረ ሰው ነው የክርስቶስን ወንጌል ለዓለም የሚያዳርሰው! በፍጹም
አይታሰብም እንዲህ ዓይነት ሰው ወንጌሉ ወይም የሐዋርያዊ ስራ በሚፈልገው ልክ ሳይሆን በራሱ ልክ ነው የሚያስበው፣ የሚያደርገው፣
የሚናገረውም፡፡ ሕዝቡ ባለው ሳይሆን እሱ ባለው ይራመዳል፣ በሕዝቡ ማንነት ሳይሆን በራሱ ማንነት ይለካል፡፡ አውደ ምህረት ላይ
ለመውጣት ሕዝቡን ማወቅ ጉዳዩ አይደለም ሰሙ አልሰሙ፣ ተረዱ አልተረዱ ጉዳዩ አይደለም፡፡ የሕዝቡን ባህል፣ ቋንቋ፣ መልክእምድር፣
ዳራ ማወቅ አይፈልግም ግን የቤተክርስቲያናችን ሐዋርያዊ ስራ እንዲህ አይልም፤ ሕዝቡን ሳያውቁ ማስተማር የለማ፡፡
የክርስቶስ ወንጌል ሕዝቡ በሚሰማ ቋንቋ፣ በሚረዳው ባህል፣ ሕዝቡ ባለው
የሃይማኖት ዳራ፣ የእውቀት ደረጃ፣ ሥነ ልቡና እና ወዘተ መሰረት ያደረገው መሆን ነበረበት፡፡ ጌታችን ባረገ በአስረኛው ቀን መንፈስ
ቅዱስን ለሐዋርያት በሰደደ ጊዜ የክርስቶስን ወንጌል ለዓለም ለማዳረስ መንፈሳዊ መሳሪያ ይሆናቸው ዘንድ 72 ቋንቋ ገለጠላቸው፡፡
በሐዋርያት ስራ ታሪክ የሕዝብን ቋንቋ ባለማወቅ ያጋጠማቸው ችግር ሰምተን አናውቅም ምክንያቱም ሆድ አዳሮች አልነበሩም፣ የክርስቶስን
ወንጌል ለፍጥረት ሁሉ ለማዳረስ ነበር ዓላማቸው፡፡ ይህንን በታላቅ ትጋት ፈጸሙ ግን ሆድ አደሮች የሕዝብን ነገር ማወቅ ዓላማቸውም
አይደለም፡፡ ሕዝቡን ሳያውቁ ለወንጌል ይሰማራሉ፤ ቋንቋውን ሳያውቁ እናስተምርህ ይሉታል የሕዝቡን ትቶ በራሱ ቋንቋ ያስተምራል ግን
ሕዝቡ አይሰማም፡፡ ምን ያድርግ ሆዱ አልጎደለ፣ ደሞዙ አልተቋረጠ፤ ሊቋረጥ እንደሚችል እንኳን አለማሰቡ ገርሞኛል፡፡ ግን ሕዝቡ
ከሃይማኖቱ እየኮበለለ ነው በሆድ አደሮች፡፡በተለይ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በጠረፋማው የሀገሪቱ ክፍል፡፡ ሆድ አደሮች ቤተክርስቲያን
ውስጥ ለተስፋፋው ኃይለኛ ሙስና፣ዘረኝነት፣ተሀድሶ ና ሌሎች ግግሮች ምክንያቶች ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ልማት እየተባለ የሚወራውም
ለሙስና መደበቅያ እንጂ መንፈሳዊ ሊማት አይደለም፤ ምክንያቱም በቤተክርስቲያን ሊማት ማለት ሕዝብን በወንጌል ማለምለም ነው፡፡
የሆድ አደራች ሌላው መገለጫው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለ ሀሳባቸው ምድራዊ
ነው፡፡ የተሰጣቸው ፀጋ፣ ኃላፊነት፣ ክብር ሰማያዊ ቢሆንም የነሱ የዘወትር ጭንቀት ምድራዊ ነው፡፡ በስመ ወንጌል ወደማያውቁት ሕዝብ
ከሄዱ በኋላ ያንን ሕዝብ የሚያደክሙበትን፣ የሚበትኑበትን፣ ከሞላላቸውም ማጥፋት የዘወትር ተግባራቸው ነው፡፡ ተተኪ ማፍራት ካለው
ህብረተሰብ መሆኑ ቀርቶ በምድራዊ አጠራር ከዘራቸው ብቻ ያፈራሉ ሌላው በመካከላቸው እንዲገባ አይፈልጉም አይ መሸወድ ዋስትና የሌለው
ሕይወት፣ ቤተክርስቲያንን የሚሰረስር የውስጥ ወንበዴ፣ ያልተነቃበት የውስጥ መናፍቅ፣ የመስቀል እና የወንጌል ጠላት፡፡ የአከባቢው
ሕዝብ አገልግሎት ሲጠይቃቸው ዘረኞች ሆነው ዘረኞች እያሉ የሚደስኩሩ፡፡ ይህ እቅዳቸው በአካባቢው ያለው ሕዝብ ለቤተ ክርስቲያኒቱ
ባዳ እንዲሆን እና ሙሉ በሙሉ ትቶላቸው ሃይማኖቱን እንዲክድ ማድረግ ነው፤ እያደረጉም ነው በተለይ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ክልሎች በመረጃ
የተደገፈ ነው፡፡ የሆድ አደሮች ዓላማ ወንጌልን ማስፋፋት ሳይሆን ሆዳቸውን መሙላት፣ ባህላቸውን ማንጸባረቅ፣ ቋንቋቸውን ማሳደግ፡፡
ሃያ ዓመት ከሕዝቡ ጋር ኑረው የሕዝቡን ቋንቋ በመጥላት መልመድ እየቻሉ ወንጌልን ሳያስተምረው በአውደ ምህረት እየለፈለፉ ማንም
ሳይሰማቸው ስንቱ ትቶላቸው ሄደ? ሆዳቸውን እየሞሉ ለክርስቶስ ወንጌል ጠላት የሆኑ ቤት ይቁጠራቸው፡፡ ነገር ግን ብያውቁ ኖሮ እና
ትክክለኛ ሐዋርያ ቢሆኑ ኖሮ የሕዝቡን ቋንቋ ባወቁ ወይም ለማወቅ ጥረት ባደረጉ ነበር፡፡እዚህ አንድ አርቀው አሳቢ አባት የተናገሩትን
ልንገራችሁ ‹‹ከምያሳዝነኝ ውስጥ ይህን ያህል በዚህ ክልል ኖሬ የክልሉን ቋንቋ አለመቻሌ ነው፤ መማር ያለብኝን የቤተ ክርስቲያን
ትምህርት ተምሬያለው ግን ማስተማር አልቻልኩም ምክንያቱም ሕዝቡ እንደማይሰማ እየተነገረኝ ነው፤ ደግሞ ምድራዊ መንግሥት እንኳን
ከእኛ ተሽሎ የሚያስፈልጋቸውን ስጋዊ አገልግሎት እነሱ በሚሰሙት ቋንቋ እየሰጣቸው ይገኛል፡፡›› አሉኝ ግን እሷቸው ቁጭታቸውን እና
እውነታውን ነው የሚናገሩት፡፡ እውነትም ቀዳሚዋን ቤተክርሰቲያን ከምድራዊ
አሰራር ወደ ኋላ ያስቀሩ ሆድ አደሮች አይመስላችሁም?
የሆድ አደሮች መጨረሻ ምንፍቅና፣ ጥንቆላ፣ ተሀድሶ መናፍቅነት በመጨረሻም
ሰይጣን አምላኪዎች መሆን ነው፡፡ ስጀመር ዘረኝነት የሰይጣን መንፈስ ነው፡፡ የእውቀታቸው መለኪያ በሸመደዱዱት ልክ እንጂ ባመኑት
ልክ አይደለም፤ ያውቃሉ ግን አይምኑም፡፡ ከዚህ የተነሳ የቤተክርስቲናችን የክህነት መስፈርት በሸመደደው ልክ እንጂ ባመነ፣ በተመሰከረለት
መሆኑ ቀርቷል፡፡ ዛሬ ለተበላሸው የቤተክርስቲያናችን ሥርዓት ምንጩ ማን መሰላችሁ? ሆድ አደሮች አይደሉምን? የተማሩት ትምህርት
የክርስቶስን ወንጌል ለማስፋፋት ሳይሆን ለሆዳቸው ስለሆነ በጎደለባቸው ጊዜ ከውጭ መናፍቅ ጋር እየታጃለሱ ሥርዓቷን ማበላሸት፣ ዶግማዋን
መለወጥ ወዘተ፣ ስለ ገንዘብ ደግሞ የቤተክርስቲያንን ቅርስ መሸጥ፣ አብዛኛው በውጭ ሀገር ያለው በሺዎች የሚቆጠር የብራና መጻሕፍት
መቼም በሆድ አደሮች ካልሆነ በስተቀር በሀገሬው ሕዝብ ነው የተሸጠው እንዳትሉ፡፡
የቤተክርስቲያን ሀብት ምእመናን ናቸው፣ የገቢ ምንጯም ከእነሱ ውጭ
ማንም የላትም እንደ መናፍቃን ከውጭ የሚገባላት የላትም ነገር ግን ለዘመናት ገንዘብ በማጣት ወንጌል ከማስተማር ቦዝና አታውቅም
ነበር፡፡ ሐዋርያቶቿ ይህ አይበግራቸውም ነበር ነገር ግን ዛሬ በሆድ አደሮች ሐዋርያዊ ስራዋ የታገተ ይመስለኛል ይህም የሆነበት
ምክንያት ሕዝብን ያማከለ ሐዋርያዊ ስራ አልተካሄደም፡፡ ሰባኪ ከአድስ አበባ ማምጣት እንጂ ሕዝብ ማነው ይምለው ጥያቄ አይጠየቅም፤
ሰባኪውም ጠሪዎቹ በነገሩት ልክ ጮኾ ይሄዳል ለውጥ ግን የለም፡፡ በተለይ ኦሮሚያ ክልል ብዙ የሕዝብ ጉባኤ ይካሄድባታል ነገር ግን
ለውጥ የለም ሕዝቡ አሁንም እየጠፋ ነው፡፡ በሕዝቡ ቋንቋ ይሰጥ ሲባል ዘረኞች፣ ተሀድሶ፣ፖለቲከኝ... ወዘተ ይባላል፡፡ ለመሆኑ
ዘረኛው የትኛው ነው? በሕዝቡ ቋንቋ የማታስተምር ከሆነ ዝም ብለህ እንደምትጮኽ እንዴት አይገባህም? ሆድህ ካልጎደለ አይታወቅህም
አንድ ቀን እንደምጎድልህ ማወቅ ግን ነበረብህ፡፡ ይህን የሚያደርገው እኔ አይደለሁም የሐዋርያት ጌታ በሃምሰኛው ቀን የወረደ መንፈስ
ቅዱስ ነው፡፡ብልጥ እና ሐዋርያ ብትሆን ግን በሕዝቡ ቋንቋ፣ ባህል መሠረት ባስተማርክ ነበር፡፡ ዘረኛ ሆነህ ነው እንጂ ይህን ዓመት
ሁሉ በሕዝብ መሀል ኖረህ ቋንቋቻውን በለምድክ ነበር፣ ባህሉን በተረዳህ ነበር አንተ ግን የመጣህበትን ቋንቋ እና ባህል ስታራግብ
ኖርክ ቤተክርስቲያንን ስለማትወክል አይደንቀኝም፡፡ ግን ቅድስት ቤተክተርስቲያንን ከመናፍቃን ይበልጥ በአንተ ስለተጎዳች ዝም አልልም፡፡
ምክንያቱም የቤተክርስቲያን ጠላት አምራች አንተ ራስህ ስለሆንክ ማለት ነው፡፡
የሆድ አደሮች መገለጫው ሌላው ወንጌል ባለማስተማራቸው የሕዝብ ቁጥር
እየቀነሰ ሲሄድ የሚገባው ገንዘብ እንዳይጎድልባቸው በስመ ገቢ ማመንጫ እና በስመ ልማት ሕንጻ መገንባት፣ ማስገንባት ነው፡፡ ታቦተ
ሕጉ ቆሞ ወንጌል ከማስተማር የገንዘብ ልመና መርሐግብር መብዛቱ፣ ገንዘብ ለማግኘት ተብሎ ጽላቱ የሚከብርበትን ቀን እስከመቀየር
መድረስ፤ ለምሳሌ መስከረም 17 የመስቀል በዓል ስለሚከበር በዕለቱ ደግሞ ጉራጌዎች ወደ ተወለዱበት ስለሚንቀሳቀሱ ከእነሱ የሚገኘው
ገንዘብ እንዳይቀር ተብሎ በዚህን ቀን የሚታሰበው የቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ በዓል ወደ ጥር 17 መሸጋገሩ ከውስጤ አልወጣ
ያለ ክስተት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ በአንድ አስተዳደር ስር ያሉ ተመሳሳይ መታሰቢያ ያላቸው አብያተ ክርስቲያናት ሁለቱም አንድ ጊዜ
የሚነግሱ ከሆነ የሚገኘው ገንዘብ ስለሚጎድል የአንዱ ቤተክርስቲያን ጽላት እንዳይወጣ ተደርጎ የአንዱ ብቻ ሲወጣ ማየቴም አሳዝኖኛል፤
ለዚህ ነው ይህንን ጽሑፍ ለማውጣት የተገደድኩት፡፡ ባሁኑ ጊዜማ ሰለቸኝ ለስብከተ ወንጌል ማለትም የሥላሴ ሕንጻን ከማነጽ ይልቅ
ድንጋይ ለመከመር የሚለመነው ገንዘብ፣ የሚሠራው ስራ ልዩ ነው፡፡ ይህ ጥቅሙ በምድራዊ መንግሥት ዘንድ ለመወደድ እንጂ በሰማያዊው
ንጉስ ዘንድ እንደማያስከብር ይታወቃል፡፡ ሕዝቡ ኮብልሎ ስለሄደ፣ ወይም ስላልተማረ ምን አገባኝ በማለት ዝም ስላለ የሚጠይቃቸው
የለም በራሱ አከባቢ በስመ ቤተክርስቲያንን የፈለጉትን ይሆናሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ቤተክርስቲያንን ከዓላማዋ እና ከባሕርይዋ ውጭ
ስለሚያደርጋት ብያስቡበት መልካም ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ለሕዝብ ናት እንጂ ለተወሰኑ ሰዎች የስጋዊ የገቢ ምንጭ እንድትሆን አይደለም፡፡
ሆድ አደሮች የሚኖሩት ሆዳቸው ይሙላላቸው እንጂ ስለ ቤተክርስቲያን
ሥርዓት አይጨንቃቸውም፡፡ በቅዳሴ ሰዓት የሙዳይ ምጽዋት ፍተሻ እንጂ
በሕዝብ መሀል እየሄዱ የምእመናን ሕሊና መስረቃቸው ምናቸውም አይደለም፡፡ ይህ ዕለት ዕለት የማየውን ነው የምነግራችሁ፡፡ ይህንን
የሚያደርገው ደግሞ የቤተክርስቲያኒቱ ዘበኛ ነው፤ ዘበኛው ለወንጌል እና ለጸሎት የተሰቀሉ መብራቶች ለማጥፋት፣ የቤተክርስቲያን በር
ለመዝገት የሚቸኩል እንጂ የቤተክርስቲያኒቱ ዓላማ የገባው አይደለም፡፡ ከኋላው ደግሞ ሰበካ ጉባኤ አለ ዘበኛው በቅዳሴ ሰዓት እየዞረ
እንዲፈትሽ የታዘዘው፡፡ ሰባካውም ቢሆን የሙዳይ ገንዘብ የሚቆጥረው በሰንበተ ክርስቲያን እሑድ አይደለም እንዴ? ኧረ እንዲህ አይደለም!
ሕዝቡ የመረጣችሁ ሰንበት እንድትሽሩ ነው እንዴ? ሥርዓተ ቤተክርስቲያን እንድታፈርሱ ነው እንዴ? ወይስ ሙስናን ለመዋጋት ለግልጽነቱ
ብላችሁ ይሆን በሕዝብ ፊት የሙዳይ ገንዘብ የምትዘረግፉት?... ለመሆኑ ከቅዳሴ የሚበልጥ አለ እንዴ? ቅዳሴውስ የሰበካውን አባላት
አይመለከትም? የእነሱ ይቅር በዕለቱ ቅዳሴ ለማስቀደስ የቆመውን ወጣት ገንዘብ ቁጠር እያሉ ጸሎት ያሚያቋርጡ በብዙ አብያተ ክርስቲያን
ማየቴ ነው፡፡ ብነገራቸው አይሰሙም ሊማት ነዋ፣ ገንዘብ ብቻ! እስኪ መጀመሪያ ሕዝብ አስተምሩ አያንገብግባችሁ፡፡ ሕዝብ ካለ የምትንገበገቡለት
ገንዘብ ከእነሱ ይገኛልና፡፡ አሁን አሁንማ መርሐግብራቱ የሚዘረጉት ገንዘብ ለመሰብሰብ ብቻ የሆነ ይመስላል፡፡ በቤተክርስቲያን አውደ
ምህረት የሰዎች ሙገሳ፣ የገንዘብ ልመና፣ የሳይንስ እና የፖለቲካ መልእክት ማስተላለፍ የተለመደ ሆኗል፤ ነገር ግን መሆን የነበረበት
በፖለቲካ መድረክ ቤተክርስቲያን መልእክት ማስተላለፍ ነበረባት፡፡
ምን ይደረግ በዘረኞች እና በሆድ አደሮች ነገሩ ተቀያየረ እና ቤተክርስቲያን የበታች ኃላፊው ፖለቲካ ከበላይ ሆኖ መራት፡፡
ሌላው የሆድ አደሮች ስራ የሰንበት ትምህርት ቤት አወቃቀርን በእነሱ
ልክ ማድረግ ነው፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤቱ ከሕዝቡ የተውጣጣ ሲሆን ቤተክርስቲያን ሲሄድ ግን ሰንበት ትምህርት ቤቱን እንዲያስተምር
በተመደበው መምህር ልክ ይወሰናል፡፡ እሱን የማይመስሉ ቦታ የላቸውም ብሰበሰቡ እንኳን ይበተናሉ በመምህሩ፡፡ ተቀባይነት ለማግኘት
ግድ መምህሩ የምናገረውን ቋንቋ መናገር፣ እሱ ከሚያውቀው ባህል የወጣ መሆን አለበት፡፡ እንዲህ አይነቱ ዬት ዬት እንደሆነ መገመት
አያዳግታችሁም፡፡ በዚህ አይነት አመለካከት ያላችሁ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች አንድ ቀን በእናንተ ላይ መድረሱ ስለማይቀር እስኪ
ሁላችሁም ራሳችሁን ተመልከቱ፡፡ ዛሬ ዛሬማ የሰንበት ትምህርት ቤቱ አባላት ከሰበካ የተማሩትን ሥርዓተ ብልሹነት ይፋ እያወጡ ነው፡፡
በቅዳሴ ሰዓት ገንዘብ ማስገኛ ዕጣዎችን ማዞር፣ ባጠቃላይ ከዘረኝነት አንስቶ ሥርዓት አልበኝነት እየገነነ መምጣት አሳሳቢ የሆነ
የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ነው፡፡የቤተክርስቲያን አገልግሎት በአማርኛ ልክ የተሰራ ነው ሌላው ባእድ ነው፡፡ ግን መብቃት አለበት፡፡
ሌሎች ይቅሩ ከሀገሪቱ ክፍል የተወጣጡ ተማሪዎች የምስተናገዱባቸው በሀገራችን የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት እንኳን እንዴት ማሰብ
አቃታቸው? ምክንያቱም ዘረኞች እና ሆድ አደሮች ስለሆኑ ነው፡፡ ለማስመሰል ግን በሕዝብ ቋንቋ አያስተማርን ነው የሚሉ በስተዋል፣
ላሁኑ ይለፈኝና እውነታውን ግን አላስቀርም በተለይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለውን አገልግሎት ማስመሰሉ ቀርቶ በእውነት እስከሚሰራ፤
እንዳይማይፈለግ በማስረጃ የተደገፈ ስለሆነ ራሳችንን ብንመለከት፡፡ ሃይማኖታዊ መሆኑ ቀርቶ ፖለቲካዊ እንደሆነ ከተግባሩ ተረድተናል፣
የአገልግሎት ጥያቄ ሲጠየቅ ከፖለቲካ ጋር ማላከክ፤ማያያዝ፣ዘረኛ ማለት፣ ሊሰሟመቸው ለሚችሉ ሰዎች እና አካላት ጥያቄ አቅራቢዎቹን
ማቅረብ (መረጃው በእጄ ስላለ) ሌለውም ብለዋል ግን ለዚህ ለባለቤቱ ለቤተክርስቲያን አምላክ እንስጥ፡፡ ብዙ ጊዜ ደግሞ ትምህርታቸው
ስለ ተሀድሶ ነው ደግሞ ለራሳቸው ሳይጣን አምላኪዎች ሆነው፡፡ ዘረኝነት ሰይጣን ማምለክ ነውና፡፡ እስኪ መጀመሪያ ቤተክርስቲያኗ
ዬት እንዳለች እንወቅ፣ ልታደም የሚችለውንም ሕዝብ እንለይ (እንወቅ) ከዚያ ሁሉም ነገር ቀላል ይሆናል፡፡ የሐዋርያት አምላክ ሁሉን
ነገር ማስተካከሉ አይቀርም ነገር ግን በፍቅር እና በስምምነት ይሁን፤ የተስተካከለ ለት ግን የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፡፡ በመሠረቱ
ክርስቲያን ተዋደው የሚኖሩባት እንጂ ተቻችለው አይደለም፣ እንድንዋደድ እንድንደማመጥ ራሳችንን እናስተካክል፣ አመለካከታችንን እናስተካክል፡፡